>

በታዴዎስ ታንቱ እና በተመስገን ደሳለኝ የዋስትና መብት ላይ ለመበየን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ለሃምሌ 21 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ (ጌጥዬ ያለው)

በታዴዎስ ታንቱ እና በተመስገን ደሳለኝ የዋስትና መብት ላይ ለመበየን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ለሃምሌ 21 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ

ጌጥዬ ያለው

የአዛዎንቱ ጋዜጠኛና የታሪክ ጸሐፊ እንዲሁም የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን በገንዘብ ዋስትና ከእስር የመፈታት ብይን ለመሻር ወይም ለማጽናት የዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለፊታችን ሀምሌ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ረፋድ 3:00 ሰዓት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ጋሽ ታዴዎስ ታንቱ በ15 ሺህ ብር፣ ተመስገን ደሳለኝ ደግሞ በመቶ ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ተፈተው በተመሰረተባቸው ክስ ላይ እንዲከራከሩ የእስር ፍርድ ቤቶች ማለትም በቅደም ተከተል የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የጸረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት እና የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ወስነው ነበር። ሆኖም ዐቃቤ ሕግ በተለያየ መዝገብና ፍርድ ቤት የከሰሳቸው ታዴዎስ እና ተመስገን ከእስር እንዳይፈቱ በመቃዎም ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ መጠየቁን ተከትሎ ነው ክርክር እየተደረገ ይገኛል። በዚህም ተከሳሾች ባቀረቡት መከራከሪያ ላይ ዐቃቤ ሕግ በቢሮ በኩል ዘግይቶ የመልስ መልስ አቅርቧል። ዛሬ ረቡዕ ሀምሌ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ተከሳሾችና ጠበቆቻቸው በተገኙበት የተሰየመው ችሎቱ ብይን ለመስጠት የ8 ቀናት ተጨማሪ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፍሬ ነገር ክርክሩን ለመቀጠል ጋሽ ታዴዎስ ታንቱ ሀምሌ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. እንዲቀርቡ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የጸረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ቀጥሯል። በዚሁ ዕለት የክስ መቃወሚያቸውን እንደሚያቀርቡ ይጠቃል።

በሌላ በኩል ተመስገን ደሳለኝ ሀምሌ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. ለፍሬ ነገር ክርክር እንዲቀርብ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ቀጥሯል። ተመስገን ባለፈው ችሎት ባቀረበው የክስ መቃወሚያ ላይ በቢሮ በኩል መልስ እንዲያቀርብ ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ለሀምሌ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ሌላ ቀጠሮ ተይዟል።

ሀምሌ 26 በሚሰየመው ችሎት የእስር ፍርድ ቤቱ የክስ መቃወሚያውን በተመለከተ ብይን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

Filed in: Amharic