>

የአዲስ አበባ ከንቲባ ያለመከሰስ መብት ተነስቶ ለህግ እንዲቀርቡ ስለማሳሰብ (የባልደራስ ወቅታዊ መግለጫ)

የባልደራስ ወቅታዊ መግለጫ!!

ጉዳዩ፡-

1. የአዲስ አበባ ከንቲባ ያለመከሰስ መብት ተነስቶ ለህግ እንዲቀርቡ ስለማሳሰ

   2. የኦሮሚያ ሰንደቅ ዓላማ እና መዝሙር በአ./አ ት/ቤቶች እንዳይይሰቀል እና እንዳይዘመር ስለማሳሰብ 

የኢትዮጵያ ሕዝብ በገዥው ፓርቲ እየተፈጸሙበት ያሉት የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውሶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፉ በመሄድ ላይ ይገኛሉ። አዲስ አበባ ከተማም የኦሕዴድ መራሹ ብልጽግና የጥፋት ክንዱን ካሳረፈባት የአገራችን ክፍሎች ዋናዋ ናት፡፡

 

የከንቲባ አዳነች አበቤ የሥልጣን ዘመን ከተማዋን ከገጠሟት አስከፊና ብልሹ አስተዳደሮች መካከል ግንባር ቀደሙ ከመሆኑም ባሻገር፣ ለሕዝቡ ማንነት ባለው የጠላትነት መንፈስ ከተማዋንም ሆነ አገሪቷን ወደ ቀውስ በፍጥነት እና  በጥልቀት እየገፋት ይገኛል፡፡ ከፍተኛ ሙስና ውስጥ እንደተዘፈቀም ሰሞኑን የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለባለ እድለኞች ለመስጠት በወጣው የተጭበረበረ ዕጣ ወለል ብሎ ታይቷል፡፡ በዚህ ሂደት፣ ወ/ሮ አዳነች አበቤ በከንቲባነታቸው ካለባቸው ሓላፊነት ባሻገር፣ በድርጊቱ መሪ ተዋናይ እንደነበሩ በርካታ መረጃዎች ተገኝቶባቸዋል፡፡

ከእነዚህ መካከል፥ የተጭበረበረው ዕጣ ከመውጣቱ ጥቂት ሰዓታት በፊት፣ በከንቲባዋ የተላከ አንድ ግለሰብ የታሸገውን ኮምፒዩተር ከፍቶ ሲነካካ እንደነበር እና መልዕክተኛው ምን ይሠራ እንደነበር የሚከታተል ሌላ ሰው በአጠገቡ ያልነበረ መሆኑ አንዱ መረጃ ነው፡፡ ይህ መረጃ፣ ከንቲባዋ በፖሊስ ለመጠየቅ የሚያበቃቸው መሆኑ የአገራችንን የቆየ የፍትህ ሥርዓት በርቀት እንኳን ለሚያውቀው የተሰወረ አይደለም፡፡

ከንቲባዋ የወቅቱ ቱባ ተረኛ ባለሥልጣን በመሆናቸው ግን ተጠያቂ እንዳይሆኑ ተደርገዋል።

ከዚህ በተጨማሪም፣ ከንቲባዋ የዕጣውን መረጃ የያዘ ፍላሽ፣ ከመንግሥት አሠራር ውጭ በግል መውሰዳቸውም ታውቋል፡፡ ከዚህ ቀደም ብሎ፣ እሳቸው በሚመሩት እና በሚቆጣጠሩት የከተማው አስተዳዳር የተሰራው የዕጣ ማውጫ ሶፍትዌር ለማጭበርበር እንደሚያመች ከፌድራሉ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በደብዳቤ እንዲያውቁት ተደርጎ፣ ምንም እርምጃ  እንዳልወሰዱ ከመረጃም ባሻገር በማስረጃ ተረጋግጦባቸዋል፡፡

በዚህ አውድ፣ ከንቲባዋን ትቶ ሌሎች የአዲስ አበባ አስተዳዳር ባለሥልጣናት እና ሙያተኞች ላይ እርምጃ መወሰዱ የፍትህ ሥርዓቱን ባዶነት እና አድሎኝነት አጋልጧል፡፡ ሁሉም ዜጎች በህግ ፊት እኩል ናቸው ከተባለ፣ የከንቲባዋ ያለመከሰስ መብት ተነስቶ በተነሱት ጥያቄዎች ላይ ለፖሊስ ቃላቸውን መስጠት ይገባቸዋል፡፡

ከንቲባዋ በህግ ሊያስጠይቋቸው የሚችሉ በርካታ ጉዳዮች እያሉ፣ በሥልጣን ላይ ያሉት ተረኞች ከለላ ሰጥተዋቸው የሚገኙት በአዲስ አበባ ማንነት፣ አስተዳደራዊ ነፃነት እና ስነ-ልቦና ላይ ከተከፈተው ሁለ-ገብ ጦርነት ጋር ካላቸው ቁርኝት አኳያ እንደሆነም የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በከተማዋ ላይ የተከፈተው ድምጽ አልባ ወረራ፣ በዚህ ሳምንት የመጨረሻው ከፍታ ላይ ደርሶ የኦሮሚያ ክልል ህገ መንግሥት በከተማዋ ተግባራዊ እንደሚሆን፣ እንዲሁም፣ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የኦሮሚያ ክልል መዝሙር እንደሚዘመር እና ባንዲራውም እንደሚሰቀል  ከከንቲባዋ አንደበት ተደምጧል፡፡

በመሆኑም፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ መንግሥት አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ ያሳስባል። እነዚህም፥

1. ከተጭበረበረው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ጋር በተያያዘ፣ የከንቲባዋ ያለመከሰስ መብት ተነስቶ ለህግ እንዲቀርቡ፣

2.  የኦሮሚያ ክልል ህገ መንግሥት በአዲስ አበባ ከተማ ተግባራዊ እንዳይሆን፣

3. የኦሮሚያ ክልል ባንዲራና መዝሙር በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች እንዳይሰቀል እና እንዳይዘመር በጥብቅ እናሳስባለን፡፡

 

  ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ—-ሐምሌ 13/2014 ዓ.ም.

Filed in: Amharic