ከጠላት ጋር ተባብራችኋል በሚል በእስር የሚገኙት የትግራይ ቴሌቭዥን ጋዜጠኞች እንዲለቀቁ ሲፒጄ ጠየቀ
የሲፒጄ የአፍሪካ ተወካይ ሙቶኪ ሙሞ “ጋዜጠኞች ስጋት ሳያድርባቸው በነጻነት ለመኖርና መስራት ሊፈቀድላቸው ይገባል” ብለዋል
ከአንድ ወር በፊት በትግራይ ክልለ መቀል ከተማ በቁጥጥር ስር የዋሉትና በእስር የሚገኚት የትግራይ ቴሌቭዥን ጋዜጠኞች እንዲለቀቁ ኮሚቲ ቱ ፕሮቴክት ጆርናሊስት (ሲፒጄ) ጠየቀ፡፡
አል-ዐይን አማርኛ ከምንጮቹ ለማረጋገጥ እንደቻለው ከ”ጠላት” ጋር ተባብራችኋል ተብለው ለእስር የተዳረጉት የትግራይ ጋዜጠኞች ምስግና ስዩም፣ ሐበን ሃለፎም፣ ሃይለሚካኤል ገሰሰ፣ ተሾመ ጠማለው እና ዳዊት መኮንን ናቸው፡፡
በተመሳሳይ ምክንያት መታሰራቸው ከቤተሶቦቻቸውና ባልደረቦቻቸው ማረጋገጥ እንደቻለ የገለጸው ሲፒጄ፤ በክልሉ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ በፕሮፓጋንዳ፣ በመገናኛ ብዙኃን፣ ወይም ማንኛውንም አይነት ግንኙነት ማድረግን ጨምሮ በየትኛውም ጊዜ “ከጠላት ጋር መተባበር” እንደሚያስጠይቅና በእድሜ ልክ ወይም በሞት ሊያስቀጣ እንደሚችል ገልጿል።
አል-ዐይን አማርኛ ከሳምንታት በፊት አምስቱ የትግራይ ቲቪ ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙና ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡
ይሁን እንጅ ከአምስቱ ጋዜጠኞች መካከል በሶስቱ ላይ “ከጠላት ጋር መተባበር” የሚል ክስ እንደሚመሰረትባቸው ዐቃቤ ህግ መግለጹንና ከቀናት በፊትም ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸው መታየት መጀመሩ አል-ዐይን ከምንጮቹ ለማወቅ ችሏል፡፡
የሲፒጄ ከሰሃራ በታች አፍሪካ ተወካይ የሆኑት ሙቶኪ ሙሞ “ትግራይ ውስጥ ያሉ ጋዜጠኞች ፖለቲካዊ በሆኑ ጉዳዮች ምክንያት ኢላማ እንደረጋለን ብለው ስጋት ሳያድርባቸው በነጻነት ለመኖርና መስራት ሊፈቀድላቸው ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል።
በአስር ላይ የሚገኙት አምስቱ ጋዜጠኞች በክልሉ ጦርነቱን ተከትሎ የፌደራል መንግስት ትግራይን በተቆጣጠረበት ወቅት በተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ስር ስራዎች ሲያከናውኑ የነበሩ ናቸው፡፡
ለመታሰራቸው ዋና ምክንያት ለአጭር ጊዜ ከቆየው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ስር በትግራይ ቴሌቪዥን ውስጥ መስራታቸው ሊሆን እንደሚችልና እንሚያምኑ ያነጋገርኩዋቸው ሰዎች ነግረውኛል ብሏል ሲፒጄ በሪፖርቱ፡፡
የሐበን ሃለፎም ጠበቃ አቶ መስፍን አርአያ ከአንድ ወር በፊት ከቪኦኤ ጋር በነበራቸው ቆይታ “ጠላት” የሚለው ክስ ግልጽ ባይሆንም ከብልጽግና ጋር ተባብራቿኋል የሚል ሊሆን ይችላል” ማለታቸው አይዘነጋም፡፡
“ጋዜጠኞቹ የታሰሩበት ስፍራ ንጽህና የሚጎድለው ነው፤ የነሱ መታሰር ለጋዜጠኝነት ሙያ የሚጎዳ ነው” ሲሉም ነበር በወቅቱ የተናገሩት አቶ መስፍን፡፡
በወቅቱ ለጉዳዩ ምላሽ የሰጡት የመቀሌ ከተማ ዓቃቤ ህግ አዲስ ገ/ስላሴ በበኩላቻው ”ጋዜጠኞቹ የታሰሩት በሙያቸው ሳይሆን በሌላ ወንጀል ነው፤ ለዚህም አስፈላጊውን የማጣራት ሂደት እያደረግን ነው” ብለው ነበር፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉት ጋዜጠኞች ምስግና ስዩም እና ተሾመ ጠማለው በቁጥጥር ስር እስከዋለበት ድረስ በተቋሙ ውስጥ ሲያገለግል የቆየ ሲሆን፤ ሐበን ሃለፎም፣ ሃይለሚካኤል ገሰሰ እና ዳዊት መኮንን ደግሞ ቀደም ሲል በተቋሙ የተካሄደውን “ግምገማ” ተከትሎ ከስራ ታግደው የቆዩ መሆናቸው አል-ዐይን ከምንጮቹ አረጋግጧል፡፡
ጋዜጠኛ ሐበን ሃለፎም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ክልሉን በሚያስተዳድርበት ወቅትም ቢሆን ከሳምንት በላይ ለሚሆኑ ጊዜያት ታስሮ የነበረ ነው፡፡
በቅርቡ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ይፋ በተደረገ ሪፖርት መሰረት ምስግናን፣ ሐበንን፣ ተሾመን እና ኃይለሚካኤልን ጨምሮ በአጠቃላይ 15 ጋዜጠኞች ትግራይ ውስጥ በእስር ላይ እንደሚገኙ መግለጹ ይታወሳል፡፡