>
5:33 pm - Thursday December 6, 2564

ገዥዎች ሕዝብ አንቅሮ ሲተፋቸው የሚወስዷቸው ርምጃዎች፦ (ጌጥዬ ያለው)

ገዥዎች ሕዝብ አንቅሮ ሲተፋቸው የሚወስዷቸው ርምጃዎች፦

ጌጥዬ ያለው


ሀ. ከመካከላቸው አንዳንድ ነፃ አውጭ መሳዮችን መፍጠር

እነኝህ ነፃ አውጭ መሳይ ግለሰቦች በዚያ ሰሞን በሚዲያ እንዲያቅራሩ ይጋበዛሉ። ከድርጅታቸው ሰርቀው መረጃ አውጭ ይሆናሉ። ሕዝቡም በቅቤ ውስጥ ሙዝ ተጨምሮ ሲሸጥለት ለማወቅ የሚቸገረውን ያህል የእነኝህን ሰዎች እውነተኛ አቋም ለማወቅም ሲቸገር ይስተዋላል።  Media illiteracy ታላቁ በሽታችን ነው።

ለ. በራሳቸው መካከል መከፋፈል እንዳለ ማስመሰል

በዚህም ሕዝቡን የሚያደርሱበትን በደል ሁሉ የአንዳንድ የፖለቲካ አመራሮች እንጂ የድርጅቶች አቋም እንዳልሆነ አድርጎ እንዲረዳው ይወተውታሉ። አስፈላጊ ከሆነ ከፊል አመራሮቻቸውን ያባርራሉ። ይገድላሉም። ከፊሉ ሕዝብ በየዋህነት ያምናቸዋል። ከፊሉ እምቢ ብሎ እንዳይታገል ሀሞቱ ፈሶ እውነቱን እያወቀ እንዳላወቀ ይሆናል። ራሱን ለገዥዎች ባርነት አሳልፎ ይሰጣል።

ሐ. ታመምን፣ ሞትን፣ መፈንቅለ መንግሥት ተሞከረብን፣ የግድያ ሙከራ ተደረገብን . . . እያሉ በሀሰት ማስወራት

እዚህ ላይ ከእነርሱ ውጭ ሌላ ገዥ ቢመጣ ኢትዮጵያ እንደምትበተን። ሕዝቡ፣ እነርሱና ሀገሪቱ  እንደ አማራ ጅምላ ጭፍጨፋ በአንድ ጉድጓድ እንደሚቀበሩ አስመስለው ይሰብካሉ።

መ. የውጭ ጠላት ፍለጋ መቀላወጥ

ሊያጣላ የሚችል ጉዳይ ቢጠፋ እንኳን በየኢምባሲው አንኳኩተው ይጣሉና ሕዝቡ የውስጥ ፖለቲካውን እንዲረሳው ይገፋፋሉ።

በመሆኑም ገዥዎችን መገምገም ያለብን በያዙት ድርጅታዊ ርዕዮተ ዓለምና በተግባር እየታየ ካለው እውነት አንፃር ነው። ከዝንጀሮ መንጋ ቆንጆ ለማግኘት መዳከር የለብንም። ከገዥዎች ውስጥ ነፃ አውጭ መጠበቅም ገዥው ፓርቲ እየተተካካ ለዘላለም እንዲኖር ከማድረግ የዘለለ ፋይዳ የለውም። ሲሳይ መንግሥቴም ሆነ ታዬ ደንድአ፤ ዮኃንስ ቧ ያለውም ሆነ አንካሳ ቅብጢሳ በተቃጠለ አምፖል የተወከለ ሁሉ ያው አምፖል ነው። ሀሉ ነገ በወንጀል የምንጠይቃቸው ደመኞቻችን እንጂ ነፃ አውጭዎቻችን አይደሉም። ወደ እነርሱ የሚከፈት የተስፋ ዓይን፣ ጆሮና አንደበት የለንም።

Filed in: Amharic