>

ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር አብረዋቸው ሊጓዙ የነበሩ "ሕገ ወጥ ቅርሶች ተያዙ" በማለት የሚነዛው አሉባልታ መሰረተ ቢስ መሆኑ ተገለፀ !!!

ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር አብረዋቸው ሊጓዙ የነበሩ “ሕገ ወጥ ቅርሶች ተያዙ” በማለት የሚነዛው አሉባልታ መሰረተ ቢስ መሆኑ ተገለፀ !!!

ሐምሌ 19 ቀን 2014 ዓ.ም (ተ.ሚ.ማ/አዲስ አበባ)


ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ለሕክምና ወደ ሰሜን አሜሪካ እንደሚሄዱ መገለፁን ተከትሎ ትናንት ምሽት ቅዱስነታቸው የአሜሪካ ጉዟቸውን መጀመራቸው ተገልጿል።

ቅዱስነታቸው ለሕክምና የሚሄዱ ቢሆንም በአዲስ አበባ ኤርፖርት በተገኙበት ወቅት ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እና ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት ተፈቅደው በአድራሻ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የተጻፈ ሕጋዊ ደብዳቤ እያለ እና ሂደቱ ትክክለኛ ሆኖ ሳለ አንዳንድ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ተጠቃሚዎች “ከቅዱስነታቸው ጋር ሕገ ወጥ ቅርስ ከሀገር ሊሸሽ ሲል ተያዘ” እያሉ የሚነዙት አሉባልታ መሠረተ ቢስ መሆኑ ነው የተገለፀው።

ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ተ.ሚ.ማ ያነጋገራቸው እማኞች ስለሂደቱ ሕጋዊነት በመግለፅ የሰነድ ማስረጃም ጭምር እንዳለ ነው የገለፁት።

ቅዱስነታቸው ሁለት ጽላቶችን ፣ 3 የወርቅ የእጅ መስቀሎችን (የግል ንብረታቸውንና ስማቸው የተፃፈባቸውን) ፣ 5 አዲስ እትም የግእዝ መጽሐፍ ቅዱስ እና አንድ ሊትር ቅብዓ ሜሮን ይዘው ለመሄድ ለቦሌ ኤርፖርት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በተጻፈ ደብዳቤ ጥያቄ መቅረቡንም ተ.ሚ.ማ አረጋግጧል።

ተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል ከታማኝ ምንጮች ባገኘው መረጃ መሰረት በተለያዩ ማኅበራዊ ድኅረ ገጾች በሰበር ዜና እየተላለፈ የሚገኘው  “በአባቶች ሻንጣ ውስጥ ተደብቀው የነበሩ ቅርሶች ተያዙ” የሚሉ መረጃዎች መሰረተ ቢስ መሆናቸውንና ቅዱስ ፓትርያርኩ ለአገልግሎት ይዘዋቸው የሚጓዙ ንዋያተ ቅድሳት መሆናቸውንና ህጋዊ ሰነዶች የተዘጋጁላቸው መሆናቸውም ተገልጿል ፤ መላው ኦርቶዶክሳውያን ካልተረጋገጠ መረጃ እና ፍፁም ሀሰት ከሆነ ማናቸውም የመረጃ ሂደቶች ራሳቸውን እንዲጠብቁ መልዕክታችን ነው።

 

 

Tewahedo_Media_Center

#TMC_Addia_Ababa

ተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል

እውነተኛ የተዋሕዶ ድምፅ

Filed in: Amharic