>

ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ሕብረት የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ፤

ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ሕብረት የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ፤

“’ትሻልን ትቼ ትብስን አገባሁ’- የጠሚው አይን ያወጣ፣ የመጅሊስ ስልቀጣ!”

(July 28, 2022)

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ማህበረሰብ እስልምና ኢትዮጵያ ውስጥ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ለ1400 ዓመታት በሱፍያ ኡለማዎች ይመራ ነበር። ሰሞኑን ግን የማህበረሰቡን አመራር ጠ/ሚንስትር አብይ አህመድ የዘረኝነት ፖለቲካን እሳቤ ውስጥ በማስገባት ከሱፊያው ነጥቆ በሃገራችን 40 ዓመት ላልሞላው  ለመጤው የሰለፊ/ወሃቢያ ቡድን በጉልበት አሳልፎ ሰጥቶታል። ጠ/ሚንስትሩ ይህንን ሲፋጽም ለችግራችን ሁሉ መንሥኤ የሆነውን ሆኖም ሃይማኖትና መንግሥትን የሚለያየውን የሃገሪቱን ሕገመንግሥት በመጣስ ነው። ይህም ጠ/ሚንስትሩ እነጀዋር ሙሃመድን ከእሥር ቤት ከመልቀቁ በፊት ከነሱ ጋር ያደረገው ስምምነት ውጤት ቢሆንም፣ ይህ ማለት ግን ውሳኔው በሱ ላይ ተጭኖበታል ማለት አይደለም። በኬኛ ፖለቲካ የሰከረው አብይ አህመድ መጅሊሱን ዘግይቶም ቢሆን ነገሮች ሲመቻቹለት ብዙ የኦሮሞ ብሄርተኞች ላካተተው ለሰለፊ/ዋህብያው ቡድን አሳልፎ እንደሚሰጠው የሚያመላክቱ ፍንጮች ነበሩ።

አብይ አህመድ የፌደራሉን መጅሊስ ለሰለፊ/ወሃቢያው ቡድን እንደስጦታ ከማቅረቡ በፊት በአረፋ በዓል ዋዜማ የሱፊዩንና የሰለፊ/ዋህብያውን ተጠሪዎች ሰብስቦ መሠረታዊ የቀኖና ልዩነት ያላቸው መሆኑን የሆነኝ ብሎ በመድፈቅ የምትጣሉት በቪ8 ነው በማለት ካዋረዳቸው በኋላ ይህንንም ለሕዝቡ እነግርባችኋለሁ ባለው መሠረት ሰሞኑን የስብሰባው ቪድዮ እንዲለቀቅ አድርጓል። ይህንንም ያደረገው ስብሰባው በቪድዮ አይቀረጽም ብሎ ኡለማዎቹን ካታለላቸው በኋላ ሲሆን፣ የሱፊዩ ወገን በስብሰባው ላይ ያነሱትን ወሳኝ ጥያቄዎች በቪድዮው ውስጥ እንዳይካተቱ ካፈነ በኋላ ነው። በጣም የሚያሳዝነው የመጅሊሱ ሹም ሽር የተካሄደው በአብሮነት የሚያምነውና በሙፍቲ ኡመር እንድሪስ የሚመራው የሱፊያው ወገን በሌለበት ከመሆኑም በላይ በአብይ አህመድ ትእዛዝ እነአደም ፋራህ ተገኝተው የአብይን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም ያገናዘበ አቅጣጫ ካስቀመጡ በኋላ ነው። በዚህም አብይ አህመድ መጥኖ በደቆሰው ሸፍጥ የኦሮሙማ ፖለቲካዊ የፌደራል መጅሊስ ወረራ ተጠናቋል ማለት ይቻላል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከገባ 40 ዓመት እንኳን ያላስቆጠረው የሰለፊ/ዋህብያ ቡድን መጅሊሱን ለመቆጣጠር ሕገወጥ ጉባኤ በመጥራት በተደጋጋሚ ሙከራ ማድረጉ ይታወሳል። ቡድኑ ከሁለት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ መጅሊስ አጋፋሪነትና በኦሮሚያ ክልል መጅሊስ መሪነት ከአንዳንድ ክልሎች አጫፋሪዎቹን ጋብዞ ሕገወጥ ጉባኤ በማካሄድ የኦሮሞ ሙስሊም በቁጥር ብዛት ስላለው ከ50% በላይ የሚሆነውን የፌደራል መጅሊሱን መቀመጫ መያዝ አለበት የሚል መግለጫ ከማውጣቱም በላይ የትም ሃገር ተደርጎ የማያውቀውን ለ34 የኦሮሞ ሰለፊ/ዋሃቢ ሸሆች የሙፍቲነት ማዕረግ አድሎ ነበር።ከዛም ወዲህ በአዲስ አበባ ተከታታይ ሕገወጥ ጉባኤዎች በማድረግ የሕጋዊውን የፌደራል መጅሊስ ሥራ በማደናቀፍ ከቆየ በኋላ ሰሞኑን በለስ ቀንቶት ቡድኑን ከነአህመዲን ጀበል ጋር በመሆን ይመሩት የነበሩት ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ በአብይ አህመድ ሕገወጥ ድጋፍ የፌደራል መጅሊሱ ፕሬዚደንት ሆነው ተሹመውለታል።

“ፍየል ከመድረሷ ቅጠል መበጠሷ” እንዲሉ ይህ በዘር ፖለቲካ የጠነዛው አዲሱ የፌደራል መጅሊስ አመራር የመጀመሪያ ሥራው ያደረገው የሙፍቲ ኡመርን ደጋፊዎች በተለይም ወጣት ሱፊዮችን በአብይ አህመድ ደህንነትና በአዳነች አበቤ ፖሊሶች አማካይነት ማሳደድና ማሳሠር ሆኗል።በሙፍቲ ኡመር እንድሪስ ሥር የሕጋዊው ፌደራል መጅሊስ ዋና ጸሃፊ የነበሩት ሸህ ቃሲም ታጀዲንንና የሸሪአ ፍ/ቤት ዳኛ የሆኑት ሸህ ኡመር ኮቦልሻ በአዲሱ አመራር ግፊት ታሥረው ከተንገላቱ በኋላ በዋስ ተለቀዋል።በተጨማሪም አዲሱ አመራር ከሱፊያው ጎን የቆሙ የሙስሊም ሚድያዎችና ጋዜጠኞች ላይ የአፈና ሥራ እንዲካሄድ እያደረገ ነው። በሌላ አነጋገር ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ የሚመሩት መጅሊስ መንግሥትን ኮፒ እያደረገ የመንግሥትን የፖለቲካ ሥራ እየሠራ ነው። አዲሱ አመራር  በዚህ ዓይነት አካሄድ ከቀጠለ ነገ በተለይ የሱፊያውና በአጠቃላይ የሃገራችን ቅርስ የሆነውን ሶፍ ኡመርንና ሌሎችንም የሱፍያው ታሪካዊ ሃሪማዎችን (ማእከሎች) እንደማያስፈርስ ዋስትና መስጠት የሚችል ያለ አይመስለንም። ሐጂ እብራሂም ቱፋ ባለፈው 2 ዓመት በሽመልስ አብዲሳ ድጋፍ በኦሮሚያ ክልል የሱፊ ኢማሞችን አንድ በአንድ በማሰናበት በሰለፊ/ወሃቢ ኢማሞች መተካታቸው የማይካድ ሃቅ ነው። እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ  በአማራ ላይ በመፈጸም ላይ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ልክ እንደአብይ አህመድ አንድም ቀን አውግዘው አያውቁም። በሌላ አነጋገር ዘረኝነት ተጎትቶ መጅሊስ ውስጥ መግባቱ የማይታየው ካለ አውቆ የተኛ ብቻ ነው።ከሳምንታት በፊት በፌደራል መጅሊሱ ላይ ያንዣበበው አደጋ ዕረፍት ስለነሳቸው ተወዳጁ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር እንድሪስ ለእምነት ተቋሞቻችን፣ እንዲሁም ለሃገራችን ሰላምና አንድነት ሁላችንም፣ ሙስሊሙም፣ ክርስቲያኑም በጋራ እንድንቆም ጥሪ ያደረጉት ያለምክንያት አልነበረም።

ውድ ለፍትህና ለሰላም የቆማችሁ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሆይ! በአብሮነት የሚያምነው ነባሩ ሱፊዩ ሙስሊም በዚህ አስከፊ ሰዓት ብቻ ሳይሆን ምንጊዜም ከሌላው አገር ወዳድ ወገኑ የተለየ አጀንዳ ኖሮት አያውቅም።የፌደራል መጅሊሱ የተወረረው የዘረኛውን ኦሮሙማን የበላይነት ለማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ለዘመናት የክርስትናና የእስልምና እምነት ተከታዮች እሴት የሆነውን አብሮነትንም ለማፈን ጭምር ነው።ይህ አደጋ ለሁላችን ግልጽ ሊሆንልን ይገባል።ስለዚህ የመጅሊሱ ጉዳይ ከሃገር ጉዳይ ተነጥሎ መታየት የለለበት ሁላችንንም የሚያገባን ጉዳይ ነው። ስለሆነም በታሪክ ተወቃሾች እንዳንሆንና የማህበረሰባችንንም ህልውና ለማስቀጠል ስንል ከምንጊዜውም በበለጠ በጋራ መቆም ግድ ይለናል።

እንዳለመታደል ሆኖ የኛ ነገር “ትሻልን ትቼ ትብስን አገባሁ” ሆኖብናል። ኦሮሙማ ቀጥሎ የሚሰለቅጠው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ተቋም እንደሆነ በተለይ በዚህ ሁለት ቀን በዲያቆን ዳንኤል ክብረት ፊታውራሪነት በፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ ላይ የከፈተውን አሳፋሪ ዘመቻ ማየት ብቻ ይበቃል። ከሁለት ዓመት በፊት አንድ የኦሮሞ ጥንፈኛ ዲያቆን እንደዛተው ከደብረ ሊባኖስ ገዳም አማራ መነኮሳት በማንነታቸው ተመርጠው የሚባረሩበት ጊዜ እሩቅ አይደለም።ይህ አይሆንም ብሎ የሚጠራጠር ካለ ባለፈው አራት ዓመት በአብይ አህመድ አመራር ሥር ወገናችን ላይ የደረሰውን ፍዳ ሸምጥጦ የሚክድ ብቻ መሆን አለበት። ከፊታችን የተጋረጠብን እረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድና ከፍተኛ መስዋዕትነት ሊያስከፍል የሚችል የትግል ጎዳና ቢሆንም ከአሁን ቀደም በጋራ ታግለን ሕወሃትን ከአራት ኪሎ እንዳስወጣነው አንርሳ! ዛሬ የትናንቱን ልምዳችንን አቀናጅተን የሕወሃትን ዕጣ ፋንታ በአብይ አህመድ ላይ የማንደግምበት ምክንያት አይታየንም።ስለሆነ በስሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ሕብረት ለዚህ ለተቀደሰ ተግባር እንድንሽቀዳደም ለሁሉም ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ጥሪውን ያቀርብላችኋል!

አላሁ አክበር!

በስሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ሕብረት

Filed in: Amharic