>

ለዲያቆን ዳኒ አይነቱ የምስጋና ጥያቄ የአለቃ ገብረ ሐና መልስ...!!! (አሳዬ ደርቤ)

ለዲያቆን ዳኒ አይነቱ የምስጋና ጥያቄ የአለቃ ገብረ ሐና መልስ…!!!

አሳዬ ደርቤ

* …. ባዶ ሞሰብ ታቅፈው፣ በመንግሥት አልባ ምድር ላይ በጠላት መሀከል ቆመው፣ የሚሰማቸውን እውነተኛ የአደጋ ስሜት እርሱ በፈጠረው ልብ ውስጥ ሸሽገው… ‹‹ስለሰጠኸን ሰላምና ጸጋ እናመሰግንኻለን›› እያሉ ከሚደልሉት ተዋንያን ይልቅ በመቅሰፍቱ ዘመን እሪታቸውን፣ በመናው ዘመን እልልታቸውን ለሚያቀርቡ ፍጡራን ምላሽ ይሰጣል፡፡

አለቃ ገብረ ሐና አጼ ቴዎድሮስን የሚያስቆጣ ሤራ ውስጥ ይሳተፋሉ። ይሄውም ሤራ ከንጉሡ ጆሮ መድረሱን በሰሙ ጊዜ ሸሽተው ወደ ዘጌ ገዳም ያመራሉ።

በገዳም ቆይታቸውም ርሐብ ባገሩ ይገባና ይቸገራሉ፡፡ አንድ ቀን ታዲያ ለወስፋት ማስታገሻ የምትሆን ቁራሽ ዳቦ ከአገልጋያቸው ጋር ተካፍለው ከበሉ በኋላ ዲያቆኑ ከመቀመጫው ተነስቶ ‹‹ጌታዬ ስብሐት ብዬ ምስጋና ላቅርብ?›› ብሎ ሲጠይቃቸው አለቃ የሰጡት መልስ እንዲህ የሚል ነበረ፡፡

“ተው ልጄ ቀለዳችሁብኝ ብሎ ይቆጣል፡፡”

ምን ለማለት ፈልጌ ነው?

የእኛ ፈጣሪ ከነፍስ የሚፈልቅን እውነተኛ ስሜት መጋራት የሚወድ እንጂ እንደ ብልጽግና መሪ ከምላስ በሚመነጭ ተራ ውዳሴና አድናቆት የሚፈነድቅ ባለመሆኑ…የአልጋ ቁራኛ ሆነው ሳለ ‹‹ጤናየን ሰጠኸኝ›› እያሉ ከሚሸነግሉት አስመሳዮች ይልቅ ‹‹ፈውስህን ላክልኝ›› የሚሉትን መጎብኘት ይመርጣል፡፡

ባዶ ሞሰብ ታቅፈው፣ በመንግሥት አልባ ምድር ላይ በጠላት መሀከል ቆመው፣ የሚሰማቸውን እውነተኛ የአደጋ ስሜት እርሱ በፈጠረው ልብ ውስጥ ሸሽገው… ‹‹ስለሰጠኸን ሰላምና ጸጋ እናመሰግንኻለን›› እያሉ ከሚደልሉት ተዋንያን ይልቅ በመቅሰፍቱ ዘመን እሪታቸውን፣ በመናው ዘመን እልልታቸውን ለሚያቀርቡ ፍጡራን ምላሽ ይሰጣል፡፡

እናስ ወንድም ዳኒ፦  በሁለት ሳምንት ውስጥ ከሁለት ሺህ በላይ ወገኑን በጅምላ የቀበረ፣ አገሩ ጠፍቶት የተደናገረ፣ የእለት ጉርስ አጥቶ የተቸገረ ሕዝብ፣ በልቡ የታቆረውንና ‹‹አፍነህ ያዘው›› ብሎ መንግሥት የከለከለውን ዋይታውን ትቶ በመመሪያ የወረደውንና በልቡ የሌለውን እልልታ ቢያቀልጥ “አሾፋችሁብኝ” ብሎ አይቆጣም ወይ?

 ትናንት ‹‹ማዕቀብ ሊጣልብህ ነው›› የሚል መረጃ ሲሰማ ‹‹የምዕራቡ ዓለም መሪዎች በመንግሥታችን ላይ የሚያደርጉትን ጫና እንቃወማለን›› እያልን የምንጮህበትን እድል ያመቻቸልን መንግሥት፣ ዛሬ ደግሞ “የሰማዩ ጌታ ተቆጥቶብኻል›› የሚል ትንቢት የተነገረው በሚመስል መልኩ  ያዘጋጀውን የእልልታ መርሐ ግብር ተቀብለን  ‹‹ይሄን የመሰለ መንግሥትና ሕይወት የሰጠኸን አምላክ ሆይ እናመሰግንኻለን›› ስንል ቢሰማን “ማንን ነው የምታታልሉት?” ብሎ በመብረቅ አይመታንም ወይ?

Filed in: Amharic