እስክንድር ነጋ ለምንና እንዴት ከመሰረተው ፓርቲ – ባልደራስ እራሱን ሊያገል ቻለ… ?
ወንድወሰን ተክሉ
*…. የታላቁ እስክንድር ነጋ እርምጃ የይስሙላውን ሰላማዊ ትግል ህልፈተ ህይወት ማሳየቱና በአጠቃላይ በሀገረ ኢትዮጲያ ፖለቲካ ላይ ያለው እድምታ-!!!
እስክንድር ለምን እራሱን አገለለ??
ለቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሚሊዮን ኢትዮጲያዊያን አስጨናቂና ብሎም እንቆቅልሽ ሆኖ የሰነበተው የታላቁ እስክንድር የውሃ ሽታ ሆኖ መሰወር ቢያንስ ዛሬ በከፊልም ቢሆን መልስ ያገኘ መስሏል። እስክንድር በሰሜን አሜሪካ ባልደራስ ተወካይ ሙሉጌታ በኩል ሐምሌ 16 ቀን 2014 ጽፎ ለፓርቲው ስራ አስፈጻሚ አመራር፣ለአጠቃላይ የባልደራስ ፓርቲ፣ለደጋፊዎቹና ለመላው የኢትዮጲያ ሕዝብ በጻፈው ደብዳቤ እራሱን ከባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ መሪነትና ብሎም ተራ አባልነት ያነሳ መሆኑን በመግለጽ ከእይታ የተሰወረበትን መንስኤን ገልጿል።
የእስክንድር ፊርማ ባለበት አንድ ገጽ ደብዳቤ ላይ ለምን እና እንዴት “ሀ” ብሎ ጸንሶ በመውለድ የፈጠረውን የባልደራስ ለእውነተኛ ዴምክራሲ ፓርቲን እንደለቀቀ ሲገልጽ «… በመንግስት ጫና በአባልነትም ሆነ በአመራርነት መስራት የማልችልበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ …» ያለበትን ሲገልጽ «…ተረኛው ጨቋኝ መንግስት በባልደራስም ሆነ በሃገር አቀፍ ደረጃ በፈጠረው የለየለት አምባገነናዊ ጫና ሳቢያ፣ በአባልነትም ሆነ በአመራርነት መስራት የማልችልበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ….» በማለት ለምን እና እንዴት እራሱን ሊያገል ቻለ ለሚለው ጥያቄያችን በአጭር ገልጾ ሲያልፈው እናያለን።
በእስክንድር ነጋ አንድ ገጽ የመሰናበቻ ደብዳቤ ላይ ተረኛው ጨቌኝ መንግስት ህይወቱን ለከፍተኛ አደጋ አጋልጦ የመሰረተውንና እየመራ ያለውን የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲን ፓርቲ ጥሎ እንዲወጣ ያስገደደው መሆኑን ሲገልጽ ይህ ስርዓት በሀገሪቱ ውስጥ የሚካሄዱ ሰላማዊ ትግሎችን ሙሉ በሙሉ ጨፍልቆና ደፍጥጦ ማገዱን ያሳየናል።
ይህ ሀሰት ነው የምንልና ዛሬም መብታቸው ተከብሮላቸው በሰላማዊ ትግል መንገድ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች አሉ የሚሉ ድምጾች ካሉ አዎን እንደነ በለጠ ሞላ ጣሂር ኢብራሂም ብርሃኑ ነጋ ግርማ ሰይፉ ….ወዘተ መሰሎች የስልጣን ተቌዳሽ ሆነህ ጨቌኙንና ተረኛውን ጨፍጫፊ ስርዓት እያወደስክ ማገልገል የምትፈቅድ ከሆነ እራስህን ተቌዋሚ እያልክ ግን እቃወማለሁ የምትለውን ስርዓት እያገለገልክ … ፍትሃዊ ዴሞክራሲያዊነቱን እየሰበክ …. በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች በግፍና በአሰቃቂ ሁኔታ በየእለቱ በሚጨፈጨፉበት ስርዓት አንተ ግን የሕግ የበላይነት ተረጋግጦና ፍትሕ ሰፍኖ ያለበት መሆኑን እየደሰኮርክ አሳምረህ ተቃዋሚ ሆነህ መንቀሳቀስ ትችላለህ- ያ ተቃዋሚነት ከሆነ።
አሊያም ለድርጅቶቹ ሞራል ስንል ስማቸውን የማንጠቅሳቸው ለስርዓቱ ያላደሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ድርጅታዊ አቅማቸው በሕዝብና በሀገር አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ተሰሚነት ተጽ እኖ ፈጣሪነትና ያነገቡት ዓላማ ተመዝኖና ተለክቶ … “የትም የማይደርሱና ምንም የማያመጡ” ደረጃ ላይ የምትገኝ ከሆነ አሁንም እንድትንቀሳቀስ ይፈቅድልሃል።
ነገር ግን እንደ እስክንድር አይነት በገንዘብ እማትገዛው፣ በስልጣን ሹመትና በግል ቁሳዊ ጥቅማ ጥቅም እማትደልለውና እንደ የአዲስ አበባን ጉዳይ የመታገያህ አጀንዳ አድርገህ ስትነሳ ..My friend የገሀነብ ደጆች ተከፍተው እርኩሳን መናፍስቶቹ የተለቀቁብህ ይመስል ቁምስቅልህን የሚያሳዩህ ኋይሎች ተፈተው ይለቀቁብሃል።
ለምሳሌ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ጽህፈት ቤት፣ የእስክንድር ነጋ መኖሪያ ቤትና አጠቃላይ እንቅስቃሴን 24/7 ሰዓት የሚከታተሉ ታርጋቸው ኦሮ (ኦሮሚያ) የሚል የለጠፉ የደህንነት መኪኖች በቌሚነት ማለት በሚያስችል መልኩ ይከታተሏቸዋል። ከመቶ በላይ የባልደራስ አመራሮችና ወሳኝ ግንባር ቀደም ተንቀሳቃሽ አባላት ስልክና ላፕቶፕ እየተነጠቁ ተወስደዋል። ልክ እንደ ቢግ ብራዘር ሲሲቲቪ ካሜራ ወይም እንደ የራስህ ጨለማ ጥላ እስክንድርን በገባበትና በወጣበት ሁሉ ይከተሉታል። እሱ እቤቱ ገብቶ ጋደም ሲል እነሱ እደጁ ባቌሟት ኦሮ ታርጋ የቤት መኪና እየተቀያየሩ ይጠብቁታል። ጧት ነግቶ ወደ ቢሮው ሲያመራ እስኬው በእግሩ ቢጋዝ አሊያም በአውቶቢስ በታክሲ ይጔዝ አሊያም በቤት መኪና እየተፈራረቁ … ማለትም በእግር ሲጔዝ ከመኪናዋ ውስጥ ሁለት ወይም አንድ ሰው እንዲወጣ ተደርጎ እንዲከተሉት ሲደረግ መኪናዋ ደግሞ ፍጥነትና አቅጣጫ እየቀያየረች አንዳንዴ በማለፍ አንዳንዴ ቆማ በማሳለፍ ትከተላቸዋለች።
ጥያቄው ይህንን አይነቱን እንደ የThom and Jerry ካርቱን (የአይጥና ድመት)ድብብቆሽና ክትትሎሽ ለምን አስፈለገ?? እንዲህ አይነቱንስ 24/7 ክትትሎሽን በሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ ያደርጋሉ?? ይህ ሁሉ ሰላምና እረፍት የመንሳት ማሳደድ ዓላማው ምንድነው? መቆሚያውስ መቼና እንዴት ነው ብለህ ስትጠይቅ የምታገኘው መልስ የእስክንድርን ውሳኔ መንስኤና ምንጭ ፍንትው ብሎ የታየህ ትሆናለህ።
እስክንድር አሜሪካ በነበረበት ቆይታ ወደ ሀገር ቤት እንዳይገባ … ቢያንስ ይዘግይ ብለው ዘመቻ ከከፈቱት ጋር ብዙ ግዜ ተሟግቻለሁ። የእስክንድርን ዓላማና ውሳኔን ያላከበረ ሀሳብ አምጥታችሁ እንዴት ዘመቻ ትከፍታላችሁ ብዬ ስሞግት እነዚህ ወገኖች ለእስክንድር ህልውና እጅግ ከመሳሳትና ከማሰብ እንደሆነ መረዳት አቅቶኝና እኔ በእስክንድር ላይ ጨክኜ ሳይሆን የዓላማውና የውሳኔዎቹ ፍጹም አክባሪ በመሆን ነው። ሆኖም እሱም ወደ ሀገርህ እንዳትመለስን ዘመቻ በፍጹም አልቀበልም – በማለት እቅጩን ተናግሮ በሚወዳት ውድ ሀገሩና በሚታገልለት ሕዝብ መሀል ሆኖ እራሱን ከብልጽግና የማግለሉን ውሳኔ ሲወስን የምንረዳው ነገር ቢኖር እስክንድር ፈርቶ ለግል ደህንነቱ ሰግቶና ተጨንቆ ሳይሆን አዲስ አበባ አሁን ካለችበት መቶ በመቶ የመሰልቀጥን ሂደትን ሊያስቆም የሚችል ድርጅታዊ ትግል ማድረግ እየፈለገና ማድረግም እያለበት ግን በዘረኛውና በተረኛው ፋሺስታዊው ጨቌኝ ስርት አፈና እና እገዳ ምክንያት ትግሉን ማካሄድ እንዳልቻለ በመረዳቱ የተነሳ ለትግሉ ካለው ከፍተኛ ዋጋ አንጻር ለትግሉ ብሎ እራሱን ሊያገል መገደዱን መረዳት እንችላለን እንጂ እስክንድር ለአንድ ግለህይወታዊ ደህንነቱ ሰግቶና ፈርቶ እራሱን ያሚያገል ቢሆን ኖሮ እግሩን ከአሜሪካን ሳያነሳ ከሚያፈቅሩት ባለቤቱና ልጁ ከሞቀ ቤቱ ባለበት ሆኖ ነበር «በቃኝ ደከመኝ ይቅናችሁ» ብሎ ሲሰናበት የምናየው።
ይህ አልሆነም። ዳያስፖራም ሆነ በሀገር ውስጥ ያለው ደጋፊ የእስክንድርን ወደ ሀገር ቤት መመለስን በሚቃወምበት ሁኔታ እሱ ግን ሳይስማማ ፓርቲው ቶሎ ድረስልን ብሎ ጥሪ ሲያደርግለት ምንም ሳያመነታ ወደ ሀገሩ ተመልሶ እራሱን ከፈጠረው ፓርቲ የማግለሉን ውሳኔ ስትሰማ .., ውሃ ብርቁ ሆኖ እንዳረረበት የሰሀራ በረሃ አንተም እውቀትና ማስተዋል ብርቅ ሆኖብህ ያረረብህ የ7ኛ ጨ ሽፍታ ካልሆንክ በስተቀር እስክንድር የአዲስ አበባ ሁኔታና አጠቃላይ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ ብሎ ይህንን ውሳኔ መወሰኑን ትረዳለህ። ግን እውቀትና ማስተዋል ያረረብህ የ7ኛ ጨ ሽፍታ ከሆንክ ለአንተ የሚታይህ ተቃራኒውን ነውና ልደግምልህ አልሻም።
እዚህ ላይ አንድ ነገር አንባቢና አድማጭ ልብ እንድትልልኝ የምፈልገው መሰረታዊ ነጥብ እስክንድርና ድርጅቱ ባልደራስ በዚህ በ30ዓመቱ የኢህአዴግ ብልጽግና ዘመን ከተፈጠሩት እውነተኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች … ለምሳሌ መአህድ፣ቅንጅት፣አንድነት፣ሰማያዊ፣አዴፓ….
፠ የእስክንድር እራሱን ከባልደራስ ያገለለበት ውሳኔ እድምታስ ምንድነው??
የታላቁ እስክንድር ታላቅ ዋጋ የከፈለለትን እና እራሱ የፈጠረውን ድርጅት በስርዓቱ ጭቆና አፈና እና ማሳደድ ምክንያት እራሱን የማግለሉ ውሳኔ በኢትዮጲያ የሰላማዊ ትግል ህልፈተ ህይወትን የሚያውጅ መሰረታዊ የሆነ የትግል አሰላለፍን የሚለውጥ ውሳኔ ሆኖ ነው የታየኝ።
የአብኑ ክርስቲያን ታደለ የእስክንድርን ውሳኔ «የጽናት መልኴ አንተ ነህ» በማለት ይጀምርና « የሚታገለውንና የሚታገልለትን በውል ባላወቀ መሀል ለሕዝብ ፍላጎት ነጻነትና ሀቀኛ ዴሞክራሲ መስፈን ስትል ሁለንተናህን ሰጥተህናል። ለዚህም ከፍለን እማንጨርሰው ውለታህ አለብን። ላሳየህን ጽናት ለትግል መታመንና ሰላማዊ ተጋድሎ እጅጉን እናመሰግናለን» በማለት በምስጋና ይደመድማል።
እጅግ ከባድ ዋጋ አስከፋዩን እና ምንም ጠብ የማይል ውጤት የለሹን የኢትዮጲያን ሰላማዊ ትግል ሜዳ ኴስ አልባ ባዶ ሜዳ መሆኑን ከዛሬው የታላቁ እስክንድር ውሳኔ በፊት በዚህ ሰላሳ ዓመታት ውስጥ ከእነ ዶ/ር ታዬ ወልደሰማያት እነ ፕ/ር አስራት ወልደየስ ፣ኢንጂ ኋይሉ ሻውል፣ወ/ት ብርቱኴን ሚዲቅሳ፣አንዷለም አራጌ፣ብርሃኑ ነጋ(በቅንጅት ግዜ) ልደቱ አያሌው (በአቢይ ግዜ) … ወዘተ ተዘርዝሮ እማያልቅ እስከ የህወት ዋጋ እየከፈሉ የከፈሉለት ዓላማ ግን አንዲት ስንዝር እንኴን ፈቀቅ ሳይል በአንጻሩም እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ የተመለሰበትን ሁኔታ ከሀገራችን የሰላማዊ ትግል ሂደት የምናየው።
የእስክንድር የዚህን የሰላማዊ ትግሉን ጎራ ለአራት ተከታታይ አመታት በግንባር ቀደም መሪነት ፊት ለፊት ተጋፍጦ ለእስርና ለእንግልትም ተዳርጎ ግን የሚታገልለትን ዓላማ ሊታገልለት በሚገባው ትግል መጠን መታገል እንዳልቻለ አረጋግጦ መውጣት መለት በዚህ የትግል መስክ ውስጥ ለሕዝባችን ታግለን ለውጥ እናመጣለን ብለው የሚያስቡና የሚያምኑትን የዋህ ፖለቲከኞችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ትግል ያለ ኋይል – ኋይል ደግሞ ያለትጥቅ ፈጽሞ ሊናበቡ የማይችሉ ትዩዩ ሀሳቦች መሆናቸውን በመረዳት ሁለንተናዊ የትግል አቅጣጫቸውን የስልጣን እና የለውጥ ምንጭ ወደ ሆነው ሁለንተናዊ የትጥቅ ትግል ላይ እንዲያነጣጥሩ የጥናት ውጤት ሆኖ ያገለግላል።
እዚህ ላይ አድማጭና አንባቢ ግርር እንዳይለው እስክንድር ነጋ ወደ ትጥቅ ትግል ይገባል እያልኩህ ሳይሆን እሱ ዋጋ የከፈለለት ሰላማዊ ትግል ውጤት መክሸፉና ከሰላማዊ ትግሉ እንዲወጣ መገደዱ ሌሎችን ዳር ሆነው ፈራ ተባ እያሉ የምንታገለው ሰላማዊ ትግል ነው የሚሉትን የትግላቸውን ውሎ አድሮ ጥሬነትን እና ብሎም ባዶነትን በተጨባጭ በማሳየቱ ወሳኙን የትጥቅ ትግል መርጠው እንዲቀላቀሉ ያደርጋል እያልኩህ ነው። የእስክንድርን ቀጣይ የፖለቲካ ትግል ምን እንደሚመስል እኔ አልነግርህም። ከራሱ አንደበት የምትሰማው ነው እንጂ። እኔ ዛሬ የምነግርህ በእስክንድር ደብዳቤ ላይ የተገለጸውን እራሱን ከባልደራስ ያገለለ ታጋይ መሪ መሆኑን እንጂ እራሱን ከፖለቲካው ትግል ያላገለለ መሆኑን ነው በእርግጠኝነት የምነግርህ። ቀጣዩን ግን እኔም ሆንኩ እኔን መሰል ከምንነግርህ አንተም ብትሆን ከባለቤቱ አንደበት መስማትን እንድትመርጥ ነው የምተውልህ።
ከአራት ዓመት በፊት በኢትዮጱያ ሕዝብ ትግል ለውጥን አመጣለሁ ብሎ ለስልጣን የበቃው ተረኛው የአቢይ ፋሺስት ቡድን አፓርታይዳዊ በሆነ አሰራር አዲስ አበባ እየሸነሸነ ወደ ኦሮሚያ እያካለለ ባለበት፣ የአማራን ሕዝብ በማንነቱ መጠነ ሰፊ የጭፍጨፋ ዘመቻን ከፍቶ እያስጨፈጨ ባለበት፣የአማራን ሕዝብ ከራሱ ከተማ አዲስ አበባ አትገባም ብሎ ባገደበት፣የታላቌን ኦሮሚያን ግንባታ እውን ለማድረግ መጠነ ሰፊ የወረራና የስልቀጣ ዘመቻን ፖሊሲው ባደረገበት ይህንን ስርዓታዊ ማን አለብኝነትን ለማስቆም የሚታገል በሙሉ ያለውና የቀረው ብቸኛው ግን ትክክለኛው የትግል መስመር የትጥቅ ትግል ብቻ መሆኑን የዚህ ስርዓት ግፈኝነትና አረመኔነት በግልጽ ከመናገሩም በላይ ይህንን ሀቅ ገሀድ አውጥቶ በማሳየት ረገድ የእስክንድር ነጋ እራሱን ከራሱ የፖለቲካ ድርጅት ለማግለል የተገደደበትን ሁኔታ ማየት ብቻ ከበቂ በላይ አስረጂ ነው።