>

እልልታ የዋጠው እሪታ ....!!! (አሳዬ ደርቤ)

እልልታ የዋጠው እሪታ ….!!!

አሳዬ ደርቤ

*.. የሰኔ 15ቱም ግድብ እንዲህ ተከትቧል!!

……ከእልህ አስጨራሽ ሕዝባዊ ተጋድሎ በኋላም “የአማራ ሕዝብ ገዳይ ህው፥ሓት መሆን አለበት” የሚለው የእነ በረከት ቡድን ተሸንፎ “አማራን የሚያጠፋው ኦነግ ነው” ብሎ የሚያምነው ኃይል ሥልጣኑን ተቆጣጠረ፡፡ ይሄም በሆነ ማግስት ብአዴን “ብልጽግና” በሚል ሥም ወደ ተላላኪነት ስፍራው የሚመለስበትንና ከበላይ አካል የተላከለትን የሰኔ አስራ አምስቱን ጥቃት አቀናበረ፡፡ ይሄውም ጥቃት በዝርዝር ሲታይ እንደሚከተለው ነበረ፡፡

ለውጡ በመጣ ማግስት ዶክተር አምባቸው መኮነን የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ሆኖ ሲሾም፣ ከእስር ቤት የተፈታው ብ/ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ደግሞ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ ሆነ፡፡ ኃላፊነቱን ተቀብሎ ወደ ሥራ ከገባ በኋላም የቤተሰብ ደህንነትና ምቾት በሚረጋገጥበት የሥልጣን ወንበር ላይ ሆኖ ስለ ሕዝብ ሲያስብ ወገኑ በጠላት መከበቡን አመነ፡፡

 

ወደ ትግራይ ሲቃኝ ትሕነግ “አሀዳዊው ሥርዓት አይመለስም” እያለ ኮማንዶ እና ጉጅሌውን ያሰለጥናል፡፡ ወደ ወሎ ሲመለከት ኦነግ ከሚሴ ገብቶ አማራን የሚያተራምስ የሽብር ቡድን ያደራጃል፡፡ ወደ መተከል አድማስ ዐይኑን ሲወረውር የጉምዝ ታጣቂ ቀስቱን ይፈቀፍቃል፡፡

ጄኔራሉም ይሄን ሁኔታ ከተረዳበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ወጣት ወደ ማሰልጠኛ ጣቢያ አስገብቶ ልዩ ሃይሉን እያሰለጠነ፣ ጎን በጎን ደግሞ “በጠላት ተከብበኻል” በሚል የማንቂያ ደወል ሕዝቡን መቀስቀስ ጀመረ፡፡ ዛሬ ላይ የአማራ ሕዝብ ያጋጠመውን የሕልውና አደጋ አስቀድሞ መረዳት የቻለው የፖለቲካ ነቢይ “ባለፉት ሦስት መቶ ዓመታት ባልታየ መልኩ የአማራ ሕዝብ በሁሉም አቅጣጫ በጠላት ተከብቧል” በማለት በተለያዩ መድረኮች ላይ መናገሩን ቀጠለ፡፡ በዚያን ሰሞንም ዶክተር አምባቸው ወደ ወሎ አምርቶ “የንግሥቴ እርሻ የጠብ መነሻ” በሚል ርዕስ የሚከተለውን አለ፡፡

“…ስለ አዲስ አበባ ደግመን ደጋግመን የምናረጋግጥላችሁ የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ፣ የብሔር ብሔረሰቦች መቀመጫ ፣ የአፍሪካ መዲና ጭምር ናት፡፡ የኦሮሚያ ክልል የሚያገኘውም በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠለት ልዩ ጥቅም ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ከሕገ-መንግሥቱ ፈቅ የሚል አንዳች ነገር የለም…”

ይሄውም ንግግር ለወቅቱ መሪዎች እንደ ኮሶ የሚመር ቢሆንም በእነ ዶክተር አምባቸውና በእነ ጄኔራል አሳምነው ጽጌ መሃከል ግን የአካሄድ እንጂ የሐሳብ ልዩነት አለመኖሩን የሚገልጽ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ የሐሳብ ልዩነቱ ደግሞ በሒስና ግለ ሒስ ሊስተካከል የሚችል እንጂ እስከ ተኩስና ደም መፋሰስ የሚያደርስ አልነበረም፡፡

በሌላ መልኩ ግን በዚያኑ ሰሞን ደሴ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር “የምንልከው በጀት ለሕዝብ ልማት መዋል ሲገባው የሚኒሻ ቀለብ እየሆነ ነው” በሚል ወቀሳ የጄኔራል አሳምነው ጽጌን ንግግር እና ተግባር እንዳልወደዱት መግለጻቸው አልቀረም፡፡ በተመሳሳይ መልኩም ጄኔራሉ ሁለትና ሦስት ዓመታት ወደፊት ተሻግሮ መጪውን የአደጋ ጊዜ ከተነበየ በኋላ መፍትሔውን ሲቀምር አብረውት የነበሩት ጓዶች በለውጡ መንግሥት የእሱን ያህል ተስፋ ባለመቁረጣቸው የተነሳ ጀብደኝነቱ እና ግልጸኝነቱ አልተመቻቸውም፡፡

ነፍሳቸውን ይማረውና እነ ዶክተር አምባቸውም በሕዝባቸው ላይ ያንዣበበውን አደጋ መረዳት ቢችሉም፣ ያንን አደጋ ለመቅረፍ ግን ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንጂ የአሳምነውን በኃይል ላይ የተመሰረተ ትግል አልተጋሩትም ነበር፡፡

በተመሳሳይ መልኩም የአማራ አክቲቪስቶችና ሙሕራኖች በብልጽግና መንግሥት ንግግር የደነዘዙበት ጊዜ ስለነበር የጄኔራሉን የትግል ስልት አብን እንደተባለው ድርጅት እንዳልወደዱት ሲገልጹ ተሰምተዋል፡፡

የአሳምነው ጽጌ ጭንቀት ግን “በሥልጣኔ ላይ መቆየት የምችለው እንዴት ነው” የሚል ሳይሆን “የአማራን ሕዝብ መታደግ የምችለው በምን አይነት መልኩ ነው” የሚል በመሆኑ ጫጫታው ግድ አልሰጠውም፡፡ ሥልጣኑን የተቀበለው ሕዝብን እንጂ የበላይ አካልን ለማገልገል ባለመሆኑ ማንንም የሚሰማ አልሆነም፡፡

ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በአማራ ላይ የተደገሰው የጥፋት ድግስ ጀግንነትን በመላበስ እንጂ በመቅለስለስና በመልፈስፈስ የሚመለስ አይደለም ብሎ በማመኑ ሲሆን ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ከጥቂት ጓዶቹ ጋር ልዩ ሃይሉን አዝምቶ በከሚሴ ዙሪያ ሲቀፈቀፍ የነበረውን የኦነግ ሠራዊት የማጽዳት ተግባር ፈጸመ፡፡

በዚያም እርምጃው ወገኑን ከጠላት ጥርስ ካወጣ በኋላ እራሱን ከዘንዶው አፍ ወረወረ፡፡ ግምገማ የሚል ሥም የተሰጠው ሤራ በተጠነሰሰበት ምሽትም የዶክተር አምባቸው መኮንን፣ የአቶ እዘዝ ዋሴና የአቶ ምግባሩ ከበደ ምድራዊ ሕይወት ተደመደመ፡፡ ባሕር ዳር ላይ አሳዛኝ ደም መፋሰስ በተከሰተ ቅጽበትም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚኖሩትን ኢታማዦር እና ጓዳቸውን ሕይወት የሚነጥቅ የጥይት እሩምታ ተደገመ፡፡

በማግስቱም ብ/ጄኔራል አሳምነው ጽጌ “ተከክበኻል” እያለ ሲቀሰቅሰው ከነበረው ሕዝብ መሃከል ተከብቦ ዘንዘልማ አካባቢ ሕይወት አለፈ፡፡

በክብር መነሳት የሚገባው የጄኔራሉ አስከሬንም በካሜራ ተነስቶ በገደለው ኃይል አማካኝነት ሶሻል ሚዲያ ላይ ተለጠፈ፡፡ በኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ጥይት ትንሣኤውን ያበሰረው የአማራ ትግልም ወደኋላ ከሚመልሰው አሮንቃ ውስጥ ገብቶ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም እራሱን ደበደበ፡፡ በዚያም ጥልፍልፍ ሤራ ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ የነበረው ብአዴን ቁልፍ ቁልፍ አመራሩን ወደ መቃብር ቤት፣ በርካታ የጦር መሪዎችን ደግሞ ወደ እስር ቤት ካስገባ በኋላ የባሕር ዳሩ እና የሸገሩ አሳዛኝ ጥቃት አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት “መፈንቅለ መንግሥት” የሚል ሥያሜ ተሰጥቶት እንዲህ የሚል ዜና ተነበበ፡፡

“መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ የተጠነሰሰው ሤራ ሰላሳ ደቂቃ ባልሞላ ኦፕሬሽን መቆጣጠር ተችሏል”

Filed in: Amharic