ሦስት የተጣረሱ ዜናዎች፤ ማንን እንመን???? ” ድርቅ አለ!”፣ ” ድርቅ የለም!” “አለ!”
ያሬድ ሀይለማርያም
1ኛ/ ከዩክሬን የተነሳ መርከብ ከፍተኛ የስንዴ ክምችት ጭኖ ወደ ኢትዬጲያ እየመጣ ነው። ለዚህም ምክንያቱ ኢትዬጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ድርቅ በመከሰቱ የሚሊዮኖች ህይወት አደጋ ላይ ወድቋል። ይህን ዘገባ አለም አቀፍ ሚዲያዎች የዘገቡት ሲሆን በDW አማሪኛ ዘገባ ደግሞ የUSAID እና የአለም የምግብ ድርጅት በዋቢነት ተጠቅሰዋል።
2ኛ/ ጠ/ሚ አብይ በበኩላቸው ትላንት ድሬዳዋ ላይ ባደረጉት ንግግር ከዩክሬን ወደ ኢትዬጲያ ስንዴ ተጭኖ እየመጣ ነው የተባለው ውሸት መሆኑን፣ ኢትዬጲያ ስንዴ እንዳልገዛች እና እንደውም ኢትዮጵያ በቅርብ ወራት ከፍተኛ ስንዴ አምርታ ለውጭ ገበያ ልታቀርብ መሆኑን የሰሙ ምቀኞች ስማችንን ሊያጠፉ ያወሩት የሀሰት ወሬ ነው ብለዋል። አክለውም ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁን ሰዓት ድርቅ የለም፣ በድርቅም የተጠቃ ሕዝብ የለም ብለዋል።
3ኛ/ DW አማሪኛ ፕሮግራም ሰሞኑን በተከታታይ እና ዛሬም ባቀረበው ዘገባ በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን የተለያዩ ወረዳዎች በተከሰተ ከፍተኛ ድርቅ ርሃብ መከሰቱን፣ ብዙ ሺዎች መራባቸውን እና በምግብ እጥረት የሞቱ ሰዎች እንዳሉም የአካባቢውን ባለስልጣናት ዋቢ አድርጎ ዘግቧል። የአካባቢው የወረዳና የዞን ሹሞች ድርቅ መከሰቱን እና የምግብ እጥረት መፈጠሩንም በድምጽ አረጋግጠዋል።
እውነት ከወዴት ትሆን? ለማንኛውም ርሃብ ጊዜ ስለማይሰጥ የወረዳዎቹ ሹሞች ያቀረቧቸው የድረሱልን ጥሪ ትኩረት ቢሰጠው፤ ቀሪው እዳው ገብስ ነው ወይም የገጽታ ጉዳይ ነው።