>

ወይ አአዲስ አበባ ... ግራ የተጋባው ሕገ መንግስትና ግራ የተጋቡ ፖለቲከኞች፤ ግራ ያጋቧት መዲና...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ወይ አአዲስ አበባ … ግራ የተጋባው ሕገ መንግስትና ግራ የተጋቡ ፖለቲከኞች፤ ግራ ያጋቧት መዲና…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም


እኔ በልጅነቴ የማውቃት አዲስ አበባ ዛሬ የለችም። የዛሬዋ አዲስ አበባ በሁለት ምክንያቶች እኔ ከማቃት ከተማ ትለያለች። አንደኛው ምክንያት የከተማዋ ስፋት ነው። ከተማዋ እጅግ ተለጥጣ ብዙዎቹን አዳዲስ መንደሮች በስምም፣ በሥፍራም አላውቃቸውም። ሁለተኛው መለያ ደግሞ በከተማዋ ላይ የፈሰሰው ሃብትና መዋለ ንዋይ ነው። አዲስ አበባ በረዣዥም ሕንጻዎችና እጅግ ውድ በሆኑ ቪላዎች ተሞልታለች።

እነዚህ ሁለት ለከተማዋ መለወጥ መገለጫ የሆኑ ነገሮች  አዲስ አበባ ላይ ከፍተኛ የማህበራዊ ጫና እና የፖለቲካ መዘዝም አምጥተውባታል።

አንደኛው መዘዝ የከተማዋ መስፋፋት በዙሪያዋ በነበሩ የኦሮሞ ገበሬዎች ኪሳራ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነው። የዛሬዎቹ አዳዲስ የአዲስ አበባ ቅጥያ መንደሮች እኔ እስከማውቀው ድረስ የገበሬዎች የሰፋፊ እርሻ መሬቶች ነበሩ። የድሀ ገበሬዎችን መሬት ያለበቂ ካሳ እና ጥናት እየነጠቀ ከህውሃት ጋር ሆኖ ለከበርቴዎች ሲቸበችብ የነበረው ደግሞ ዛሬ የአገሪቱን የሥልጣን  መዘውር የያወውና ለኦሮሞ ሕዝብ ጥቅም ቆሚያለሁ የሚለው የኦፒዲዮው ብልጽግና ነበር።

ሁለተኛው መዘዝ አዲስ አበባ የአገሪቱ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ህይወት ማጠጠኛ ማዕከል በመሆኗ የተነሳ የውጭ ብቻ ሳይሆን የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ምህልቃቸውን የጣሉትና ቅሪታቸውንም አሟጠው የሚያራግፉት አዲስ አበባ ላይ ነው። ይህ ደግሞ አገሪቱ አማራጭና ተወዳዳሪ ከተሞች እንዳይኖሯት ከማድረጉም በላይ ከተማዋ ከምትሸከመው በላይ የባለሀብቶች የመሬት ቅርምት ውስጥ እንድትገባ አርጓታል።

የአፋርን ጨው፣ የጎጃምን ጤፍና ቅቤ፣ የጋምቤላንና የዶዶላን ወርቅ፣ የጅማን ቡና፣ የሐረርን ጫት እና ሰንጋ፣ የሁመራን ጥጥ እና ሰሊጥ፣ የደቡብን ብና እና ፍራፍሬ በመቸብቸብ ሀብት ያግበሰበሰ ባለሀብት ሁሉ ከነገንዘብ የሚከትመው ሸገር ነው። ከሁሉም ክልል በሰበሰበው ሀብት ሕንጻ የሚሰራው፣ ንብረት የሚያፈራው፣ ትላልቅ የንግድ ማዕከል የሚገነባው እና ገንዘቡን የሚያከማቸው አዲስ አበባ ነው። ሌሎቹ የክልል ከተሞች እንደቆረቆዙና በሀብት ንጽጽርም ከአዲስ አበባ ጋር የሰማይና የምድር እርቀት ላይ እንዲገኙ ያደረጋቸውም ዋነኛው ምክንያት ይሄ ነው። አንጡራ ሃብታቸው እየተጫነ ወደ መሃል አገር በመምጣቱ የቆረቆዙት የክልል ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው በቂ የሆነ የኑሮ ዋስትና መፍጠር ስለማይችሉ ሕዝቡም ከመላ አገሪቱ ለሥራ ፍለጋ፣ ለተሻለ የጤና እክምና እና ለትምህርት ወደ መዲናዋ በከፍተኛ ቁጥር በመፍለስ ላይ ይገኛል። የክልል ከተሞች በተጓዳኝ የማደግ እድል ቢኖራቸው ኖሮ ነዋሪውን እዛው የመያዝ አቅም ያበጁ ነበር። ከደጃፉ የተነጠቀውን ሃብት ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ የሚፈልሰው ሕዝብ ከተማዋን ከአቅሟ በላይ እንዲትጨናነቅና ግዛቷንም ያለ ቅጥ እንድታሰፋ ምክንያት ሆኗል። ለኑሮ ውድነት እና ለወንጀሎችም መበራከት ዋነና መክንያት ሆኗል።

ይህ ችግር በባለሀብቶች ብቻ ሳይሆን በመንግስት ሹሞችና በክልል መንግስታትም ደረጃ አፍጦ የሚታይ አንዱ የክሽፈት መገለጫ ነው። ለዚህም ከአዲስ አበባ ናዝሬት ወይም ደብረ ብርሃን ደርሶ እና ግራ ቀኙን ቃኝቶ መመለስ በቂ ነው። በተፈጥሮ አቀማመጧ የታደለችውን ውቧን ደብረ ዘይት (ቢሸፍቱን) ማየት ይቻላል። ከአዲስ አበባ 61ኪሜ እርቀት ላይ የምትገኘው ቢሸፍቱ ከተማ ምንም ጎልቶ የሚታይ እድገትና ለውጥ የማይታይባት የቆረቆዘች ከተማ ነች። ይሁንና የክልሉ መንግስት ቢሸፍቱን ከማልማትና ትልቅ አማራጭ ከተማ እንድትሆን ከማድረግ ይልቅ በብዙ ሚሊዮኖች በጅቶ አዲስ አበባ ላይ ከባለሃብቶች ጋር እየተጋፋ ሕንጻዎች ሲገነባ ታገኙታላችሁ። ይህ የክልሉ አካሄድ አገርን ከማልማት ሳይሆን ከጠባብ የፖለቲካ ስሌት የመነጨ ስለመሆኑ ብዙማ ማብራራት አያስፈልገውም።

ባጭሩ አዲስ አበባ በዙሪያዋ ባሉ የኦሮሞ ገበሬዎች መገፋት እና በመላ አገሪቷ ባሉ የቆረቆዙ ከተሞችና ክልሎች ኪሳራ የሰፉችና ሽቅብም ያደገች ከተማ ነች። ይህ የጤናማ ያልሆነ የመንግስት አስተዳደር አንዱ መገለጫ ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ ከተማዋ የብዙ ሃይሎች አይን ማረፊያ እና የጥቅም ግጭቶች መራኮቻ እንድትሆን አድርጓታል። በላዩ ላይ ግራ የገባው ሕገ መንግስት የከተማዋን የባለቤትነትና በዙሪያዋ ያሉ ሕዝቦችን ጥቅምና መብት በግልጽና በማያሻማ መልኩ ዘርዝሮ አለማስቀመጡ ግራ ለተጋቡ ፖለቲከኞችም ከተማዋን እንዳሻቸው እንዲፈነጩባት እድል ፈጥሯል።

በአዲስ አበባ ጉዳይ አሁንም አወዛጋቢ የሆኑና ምላሽ የማፈልጉት በርካታ ነገሮች አሉ። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፤

1ኛ/ የከተማዋ የባለቤትነት ጥያቄ ነው። ይህ ጉዳይ አንገብጋቢ የሆነው ከባለቤትነቱ ጥያቄ ጀርባ ያሉ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጉዳዬች ስላሉ ነው። አዲስ አበባ በዋነኝነት የነዋሪዎቿ ስትሆን በመቀጠል ግን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀብት ነች። ከዚያም ሲያልፍ የአፍሪቃ መዲና ነች። ማንም ክልል ለብቻው የባለቤትነት ጥያቄ ሊያቀርብባት አይችልም። በባለቤትነት ደረጃ ሁሉም ክልሎች አዲስ አበባ ላይ እኩል መብት እና ጥቅም አላቸው። ይህ ግን በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ዞኖችን አይጨምርም። እነሱ በጂኦግራፊ አቀማመጣቸው ምክንያት ከከተማዋ ጋር ያላቸው ልዩ ትስስር እና ከተማዋ በነሱ ኪሳሬ እንድትሰፋ መደረጉ የልዩ መብት ተጠቃሚነትን ያጎናጽፋቸዋል። ለደረሰባቸውም ጠቅላላ ጉዳት መንግስት ሥርዓት ባለው መንገድ ሊክሳቸውም ይገባል። ገበሬዎቹን በመካስ ስም ግን በደሉን ሲፈጽሙባቸው የቆዩት ሹማምንት መልሰው የፖለቲካም ሆነ የኢሞኖሚ ትርፍ ማጋበሻ ሊነግዱበት አይገባም። በተፈናቃይ ገበሬዎች ስም የሚሰሩ በርካታ ጥፋቶች መንግስትን ወዳላስፈላጊ ችግር ውስጥ ከመዶሉም በላይ ዘርፈ ብዙ መዘዞችም ይኖሩታል።

2ኛ/ ሌላው ወሳኝ ነገር ከሁሉም የአገሪቱ ክፍል በተሰበሰበ ሃብት የተገነባቸው አዲስ አበባ ላይ ሁሉም ክልሎች ያላቸውን ጥቅምና መብት በግልጽ የሚያስቀምጥ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩ የሚያስከትለው መዘዝ ነው። አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል የተከበበች ራስ ገዝ ከተማ ብትሆንም ለከተማዋ እድገት ግን ሁሉም ክልሎች እና ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል አስተዋጽኦ አበርክተዋል። አዲስ አበቤዎች በነዋሪነታቸው፣ በዙሪያዋ የሚገኙ ገበሬዎች በተጎራባችነታቸው ከሚኖራቸው ልዩ ጥቅም ባለፈ አዲስ አበባ አንዲ ጅማ የሚኖርን ኦሮሞ፣ አንድ ጎንደር የሚኖርን አማራ፣ አንድ አሳይታ የሚኖርን አፋር፣ አንድ ጂጂጋ የሚኖርን ሶማሌ፣ አንድ መቀሌ የሚኖርን ትግሬ፣ አንድ ጋምቤላ የሚኖርን አኙዋክ ወይም ኑዌር፣ አንድ ሸዋ ውስጥ ያለን ጉራጌ፣ አንድ አርባ ምንጭ ያለን ጋሙ እና ሌሎቹንም የአገሪቱን ሕዝቦች እኮል መብት እና ጥቅም የሚያስጠብቅ የዋና ከተማ ገጽታ መላበስ አለባት። ትላንት አንድ የመቀሌ ነዋሪ የሆነ ሰው በህውሃት የሙስና አሰራር ተጠቅሞ አዲስ አበባ ላይ የኮንደሚኒየም ባለበት ሆነ ተብሎ በተወገዘ ማግስት አንድ የባሌ ተወላጅ እንዲሁ በተመሳሳይ ሁኔታ አዲስ አበባ ላይ ተመሳሳይ እድል የሚሰጠው ከሆነ ነገሩ አልሸሹም ዞር አሉ ነው። ያ ዕድል ለሁሉም፤ አሳይታ ላለው አፋር፣ ጋምቤላ ላለው ኑዌር፣ ጎጃም ላለው አማራ፣ ሶዶ ላለው ወላይታ በተመሳሳይ ሁኔታ ይሰጣል ወይ? የሚለው መልስ ይፈልጋል።

3ኛ/ አዲስ አበባ ከሕዝብ ቁርሯ መጨመር፣ ከአገሪቱ ኢኮኖሚ ማቆልቆል እና ሌሎች በርካታ ምክንያቶችን ታክለው ክፉኛ በኑሮ ውድነት እየማቀቀች ያለች ከተማ ነች። ጠዋት የገዙትን ዕቃ ማምሻውን በመቶ እና ሁለት መቶ እጥፍ ጨምሮ የሚጋኝባት ጉደኛም፣ አስደንጋጭም ከተማ ከሆነች ውሎ አድሯል። ከፍተኛ የመሬት ችብቸባ የሚካሄድባት፣ የቤቶች ዋጋ ከኒዮርክና ከብራስልስ በሚያስንቅ ዋጋ የጨመረባት፣ የቤት ኪራይ በአንዴ እስከ ሁለት መቶ ፕርሰንት የሚንርባት፤ ባጭሩ በደላሎች ምርኮ ስር የወደቀች ከተማ ትመስላለች። ደላሎቹ የመንግስት ደሞዝ የሚበሉ የመንግስት ሠራተኞች ጭምር መሆናቸው ደግሞ ችግሩን ይበልጥ የከፋ እንዲሆን ያደረገው ይመስላል። አንድ ሰው አየር ባየር የገዛውን ቤት አንድም ቀን ሳይኖርበት በብዙ ሚሊዮን አትርፎ የምሸጥበት ብችኛ ከተማ ብትኖር አዲስ አበባ ትመስለኛለች። ሰኞ በአምስት ሚሊዮን የገዛውን ቤት በሳምንቱ ሰኞ በአሥር ሚሊዮን ሸጦ የሚያተርፍ አይን ያወጣ የኢኮኖሚ ማጅራት መቺ የሞላባት ከተማ ሆናለች። በዚህ የኢኮኖሚ አሻጥር ውስጥ ከባንኮች አንስቶ በርካታ መንግስታዊ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሹም ባሻዎች እጃቸው እንዳለበት ስትሰሙ ይዘገንናል። በአዲስ አበባ እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት እና የዋጋ መናር ብዙዎችን የከፋ የኑሮ ዋስትና ማጣት ውስጥ ከቷቸዋል። የአንድ ኪሎ ሙዝ ዋጋ 60 ብር መግባቱን ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ‘ዳቦ በሙዝ ብሉ‘ ምክር ለመተግበር እንኳ ሚሊዮኖች እንዳቃታቸው ለመረዳት የሸገርን ጎዳናዎች ዞር ዞር ብሎ ማየት በሚ ነው።

4ኛ/ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ዋነኛ ሥጋት ከሙስናው ባልተናነሰ በጠራራ ጸሀይ የሚፈጸሙ ዝርፊያ እና የወንጀል አድራጎቶች ናቸው። በጅዎት ላይ ካለው ተንቀሳቃሽ ሞባይል አንስቶ የሚያሽከረክሩትን መኪና በሰላም ከቤት ይዘው ወጥተው በሰላም ይዘው ለመመለስዎ ምንም ዋስትና የሌለዎ እና ደህንነት የማይሰማዎት ከተማም ሆናለች። ይህ ችግር ከኑሮ ውድነቱ፣ ከፍልሰተኛው ቁጥር መጨመር እና ሌሎች ችግሮች ጋር ሊያያዝ ይችላል። አዲስ አበባ ግን ከአመታት በፊት እንደነበረችው የነዋሪዎቿ ደህንነት የተረጋገጠባት ከተማ አይደለችም። በርካታ ሰዎችን በማነጋገር የተረዳሁትም ሕዝቡ በጸጥታ አስከባሪ አካላት ላይ እምነት እንዲያጣ የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች ስለሚያጋጥሙት ፍርሃቱ ሌቦቹን ብቻ ሳይሆን ጸጥታ አስከባሪዎቹ ላይ ጭምር እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል።

5ኛ/ አገሪቱ ሌሎች አማራጭ ከተማዎችን  የመፍጠር ወይም የማሳደግ ፖሊሲ ነድፋ የማትንቀሳቀስ መሆኑ ደግሞ የአዲስ አበባን ጣር ያከፋው ይመስላል። ከላይ እንደጠቀስኩት ግለሰብ ባለሃብቶች ብቻ ሳይሆኑ ክልሎችም ያላቸውን መዋለ ንዋይ አዲስ አበባ ላይ የሚያፈሱበት አግባብ ከተማዋን ውጥረት ውስጥ ይከታታል። ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ወደ ናዝሬት ወይም ወደ ደብረ ብርሃት ግራ ቀኙን እያዩ ቢሄዱ በቅርብ እርቀት ያሉ ከተሞች እንኳ ምን ያህል እንደተጎሳቆሉ፣ በቂ የሆነ መዋለ ንዋይ እና ተቋማት እንዳልተገነቡባቸው ይታዘባሉ። ከአዲስ አበባ በ61 ኪሜ ርቀት ላይ የምትገኘውን ቢሸፍቱን ብንወስድ ከተማዋ እጅግ በተፈጥሮ ሃብት እና አቀማመት የታደለች ብትሆንም ምንም እድገት የማይታይባት የቆረቆዘችና አቧራዋን ያላራገፈች ከተማ እንደሆነች ይታያል። በተቃራኒው የኦሮሚያ ክልል መንግስት በርካታ የቢሊዮን ብሮች ፕሮጀክቶችን በተጨናነቀችው አዲስ አበባ ላይ ኢንቨስት በማድረግ ሕንጻዎችን እና ተቋማትን ሲገነባ፣ ከባለሃት ጋር መሬት ሲሻማ እና የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ለልማት በሚል ሲያፈናቅል ታያላችሁ። ክልሉ አዲስ አበባ ላይ ገንዘብና ጉልበቱን ከሚፈጅ ቢሸፍቱን እና አዳማን አገናኝቶ አንድ ትልቅ ከተማ ቢገነባበት አዲስ አበባም ትተነፍሳለች፣ አገሪቷም ትጠቀማለች፣ ሁለተኛ አማራጭ ከተማም ይኖረን ነበር። ነገሩ ግን ወዲህ ነው፤ አገር ከመገንባት ያለፈ የፖለቲካ አጀንዳ ክልሉን እና ፖለቲከኞቹን ሰቅፎ የያዛቸው ይመስላል።

6ኛ/ ሌላው ችግር ምንም እንኳ የአዲስ አበባ ሕዝብ ብልጽግናን ባለፈው ምርጫ የመረጠ ቢሆንም በተደጋጋሚ በከተማው መስተዳድር ውስጥ በሚያያቸው ሙስናዎች፣ የመድሎ አሰራሮች እና ብልሹ የአስተዳደር ተግባራት የተነሳ በመስተዳድሩ፣ በካቢኔው እና በከንቲባዋ ላይ እምነት የማጣት እና የመጠራጠር መንፈጽ ሰርጿል። አዲስ አበቤ በወ/ሮ አዳነች በሚመራው ካቢኔ በአግባቡ እወከላለው፣ ጥቅሞቼም ይጠበቃሉ፣ ችግሮቼም በአግባቡ ይፈታሉ፣ ፍትሕም አገኛለሁ የሚል እምነት እና ተስፋ ያለውም አይመስልም። ይህንን ችግር በብዙ መልኩ አፍጦ ታዩታላችሁ። ከዚያም ባለፈ ወ/ሮ አዳነች አበቤ የኦሮሚያ ብልጽግና አባለ በመሆናቸው እና ፓርቲያቸውም በአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ ላይ የተዛባ፣ ሕገ መንግስታዊ መሰረት የሌለው እና የሌሎችን ሕዝቦች ጥቅም ወደ ጎን የገፋ አቋም ያንጸባርቅ ስለነበር በከተማዋ እና በኦሮሚያ ክልል መካከል በተካሄደው የድንበር ማካለል ሥራ ላይ የጥቅም ግጭት ውስጥ ሊገቡ የሚችልበት ዕድል ሰፊ መሆኑን ከግምት በማስገባት አዲስ አበቤዎች ከንቲባዋ ላይ እምነት ማጣታቸውን በማህበራዊ ድህረ ገጾች ቅሬታ ሲያሰሙ ይስተዋላል። በእርግጥም ይህ የድንበር ማካለል ጉዳይ ከሁለቱ ወገኖች በተጨማሪ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ በተለይም በሚካለሉት አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሊሳተፉበት ይገባ ነበር። ይህ አለመሆኑ የድንበር አከላለሉ ጉዳይ በኦሮሚያ ብልጽግና አመራሮች መካከል የተደረገ ስምምነት እንጂ የሁለት ወገኖች ስምምነት አድርገው እንዳይቆጥሩት ምክንያት ሆኗል። በዚህ የድንበር አከላለል ላይ ጥቅማቸው የሚነካ አካላት ለማን እና እንዴት አቤቱታቸውን ማቅረብ እንዳለባቸው የተዘረጋ መስመር መኖሩ አልተቀመጠም።

7ኛ/ ከተማዋ በኦሮሚያ ክልል ከመከበቧ ጋር ተያይዞ በዜጎች የመንቀሳቀስ መብት ላይ የሚጣሉት ገደቦች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል። ዜጎች ከየትኛውም የአገሩቱ ክፍል ለፈለጉት ጉዳይ ወደ መዲናዋ የመምታት፣ የመቆትና ባሻቸው ጊዜ የመመለስ መብታቸው መጠበቅ አለበት። ወደ ከተማዋ ማን መግባት እንዳለበትና እንደሌለበት የኦሮሚያ ክልል ሊወስን የሚችልበት አግባብ ሕገ መንግስቱን የጣሰና በክልሎችና በሕዝቦች መካከል መቃቃርን የሚፈጥር ነው። ለዚህም ለሳምንታት እቀባ የተጣለበት ከደሴ አዲስ አበባ ያለው መንገድ አንድ ጥሩ ማሳያ ነው።

ነገሬን ለመጠቅለል፤ አዲስ አበባ የአገሪቱ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና የፖለቲካ መዘውር እምብርት በመሆኗ የከተማዋ ሰላም ማጣት የአገሪቱን ጤና ማጣት ማሳያ ነው። ዳር ዳሩ በተናጋበት አገር መሃሉንም ማደፍረስ አገሪቱን ወዳልተፈለገ ቀውስ ይከታታል። መሃሉ ሰላም እና ደህና ከሆነ ዳር ዳሩን ከማናቸውም ጥቃት ለመከላከል አቅም ይፈጥራል። የፌደራል መንግስቱ አዲስ አበባ ውስጥ የሚካሄዱቱ ነገሮች ለከተማዋ አስተዳደር ብቻ ትቶ ዳር ሆኖ መመልከቱ በኋላ ዋጋ ሊያስከፍለው ስለሚችል ከወዲሁ ነገሮችን ማረቅ ይኖርበታል። አዲስ አበባ ውስጥ መረን የለቀቀ ሙስና፣ መረን የለቀቀ የመሬት እና ቤት ችብቸባ፣ መረን የለቀቀ ሌብነት እና ዝርፊያ፣ መረን የለቀቀ የአስተዳደር በደል፣ መረን የለቀቀ የከተማ ግንባታ በግልጽ ይታያል። ይህን ማስቆም የፌደራል መንግስቱ ተቀዳሚ ሥራ ሊሆን ይገባል። ማህሉ ከደፈረሰ ዳሩ ይናዳል።

በቸር እንሰንብት

Filed in: Amharic