>

ለኢሰመጉ: የግፍ እስረኛ ስለሆነው ወጣት ቢኒያም ታደሰ አቤቱታ ስለማቅረብ

ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን

አዲስ አበባ

ጉዳዩ፡- የግፍ እስረኛ ስለሆነው ወጣት ቢኒያም ታደሰ አቤቱታ ስለማቅረብ

ወጣት ቢኒያም ታደሰ በአዲስ አበባ ከተማ ፓሊስ ክትትል ተይዞ 5 ቀን በአዲስ አበባ ወንጀል ምርመራ ታስሮ ቢቆይም ፍ/ቤት አልቀረበም፡፡ በቀጣይም ባልታወቀ ምክንያት ያለማንም ፍ/ቤት ትዕዛዝ አዋሽ አርባ ወስደው 40 ቀን ፍ/ቤት ሳይቀርብ ከታሰረ በኋላ በ41ኛው ቀን አዋሽ ሰባት ፍ/ቤት ቀርቦ በ14 ቀን ቀጠሮ ተጠይቆበታል፡፡

ይሁን እንጂ የቀጠሮ ቀኑ ሳይደርስ ባልታወቀ አካል ትእዛዝ  ከአዋሽ ሰባት ወደ አባ ሳሙኤል እንዲመጣ ተደርጓል፡፡ እስከ ዛሬም መርማሪ ፖሊስ ሊያናግረው አልቻለም፡፡ አባሳሙኤል እስር ቤት ከመጣ አስር ቀን የሞላው ቢሆንም፣ ፍ/ቤት አልቀረበም በአጠቃላይ ሃምሳ ስድስት ቀን በግፍ ታስሮ ይገኛል፡፡

በርሃማ በሆነው በአዋሽ ሰባት እስር ቤት ታስሮ በቆየበት ጊዜ  የደረሰበትን ኢ- ሰብዓዊ ድርጊቶችን ስንመለከት፡-

1ኛ. ሻወር በ40 ቀን ውስጥ 2 ጊዜ ብቻ እንዲወስድ መደረጉ፣

2ኛ. ያለቅያሬ ልብስ 40 ቀን እንዲቆይ መደረጉ፣

3ኛ. 40 ቀን ሙሉ ከእስር ቤት እንዳይወጣና ፀሐይ ብርሃን እንዳያገኝ ተደርጓል፡፡

4ኛ. ከጠበቃ ጋር፣ ከቤተሰብ ጋር፣ ከኃይማኖት አባት ጋር እንዳይገናኝ ተደርጓል፡፡

5ኛ. ለ15 ቀን ቁርስ፣ ምሳ፣ እራት አንድ አንድ ዳቦ ከውሃ ጋር ብቻ በማቅረብ የርሃብ ቅጣት ደርሶበታል፡፡

6ኛ. ከ15 ቀን በኋላ ደግሞ ለቁርስ አንድ ዳቦ ከሻይ ጋር፣ ምሳ እና እራት ሁለት ዳቦ ከወጥ ጋር እያቀረቡ ለ40 ቀን በረሃብ ቀጥተውታል፡፡

7ኛ. የስነልቦና እና የሞራል ውድቀት ደርሶበታል፡፡

በአጠቃላይ ህገ መንግስታዊ መብትና በሰብዓዊ መብቱ ተገፏል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የዜጎችን ሰብዓዊ መብት እና ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ ስላለበት፣ አሁን ታሰሮ በሚገኝበት አባ ሳሙኤል እስር ቤት በመገኘት እንዲጎበኝና አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠው ፓርቲያችን ይጠይቃል፡፡

ከዚህ በፊት ሐምሌ 25/11/2014 ዓ.ም ለዚህ ተቋም ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አቤቱታ ያስገባ ቢሆንም ምንም መልስ ያላገኘ መሆኑን እየገልፅን፣ ለሁለተኛ ጊዜ አቤቱታ ማቅረባችን ተረድታችሁ መልስ እንድትሰጡን በድጋሜ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

Filed in: Amharic