ከብልጽግና እጅ ሰላም የሞላው ሕይወት ቀርቶ ድል ያለው ጦርነት ማግኘት አይቻልም!!
አሳዬ ደርቤ
▬▬▬▬
እንደ ብልጽግና ያለ መንግሥት ግን በሰላም ተደላድሎ ለመኖር ይቅርና እራስን ለመከላከል የማያስችል መሰናክል ደርድሮ ተፈናቃይ ያደርግኻል፡፡ ሰላምን ብቻ ሳይሆን ጦርነትንም የማይቻል ያደርግብኻል፡፡
በዚህም መሠረት የአማራ አርሶ አደር ፊቱን ወደ ሰላም እና ልማት አዙሮ ማሳውን መንከባከብ ሲጀምር እንስሳትን የሚረሽን፣ ሴቶችን የሚደፍር፣ ጥሪትን የሚያወድም…. ጠላት የከሰብ ወቅት ጠብቆ ይመጣበታል፡፡
ያን ጊዜም ከማሳው እና ከቀየው የሚያፈናቅል ጠላት አሻግሮ እያዬ ግብር የሚከፍለውን መንግሥት ሲጣራ ‹‹የሰብል ጉብኝት ላይ ስለሆንኩ አትረብሸኝ›› በማለት ያለምጥበታል፡፡ ልክ እንደዚሁ ሁሉ ከብልጽግና እጅ የወደቀው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትም በወታደራዊ ሳይንስና በእራሱ የትግል ሰሌዳ የሚያዋጋው ባለቤት አጥቶ ድሮን የማይበርበትን፣ መንግሥት ያንቀላፋበትን… ጊዜ ጠብቆ ጥቃት በሚፈጽም ሽፍታ መክፈል የሌለበትን መስዋዕትነት ሲከፍል ታይቷል፡፡
ከብዙ ጉዳት በኋላም ይሄው ሕዝብ እራሱን እና ልጆቹን አደራጅቶና ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ተቀናጅቶ እንዲሁም የተወረረ ቀየውን በከፊል አጽድቶ ከመከላከል ወደ ማጥቃት ሲሸጋገር በጠላት አፈሙዝ የተጀመረው ውጊያ በመንግሥት ትዕዛዝ እንዲቆም ይደረጋል፡፡
ከዚያም….
ተመትቶ የሸሸው ጠላት በማይወረርና በማይደፈር ክልሉ ውስጥ ሆኖ ከአየር ጥቃት የሚታደገው የክረምት ወቅት እስኪመጣ ድረስ ለሌላ ዙር ጦርነት እራሱን ሲያዘጋጅ ይከርማል፡፡
ለጦሩ ስንቅ የሚሆን ስንዴ እና ነዳጅ ከፌደራል መንግሥት እስኪላክለት ድረስ ስለ ድርድር እያወራ በርካታ ጦር ያሰለጥናል፡፡
ውጫዊ ኃይሎች በአውሮፕላን የሚጭኑለትን ጥይትና ዱቄት ያከማቻል፡፡ ከዚያም ያረቀቀውን የትግል ካሌንደር መሠረት አድርጎ የድል ባለቤት ያደርግልኛል በሚለው ግንባር ጦርነትና ወረራ ይለኩሳል፡፡
የሰላም ሕይወትን መግፋት ቀርቶ በቅጡ መዋጋት የተነፈገው የአማራ ሕዝብ ግን ከጠላት ወረራ ነጻ በወጣ ማግስት ፋኖ ልጆቹን የሚያሳድድ መንግሥት ይመጣበታል፡፡
በእራሱ የትግል ሰሌዳ የሚመራው የሽብር ቡድን ደስ ባለው ግንባር ወረራ ፈጽሞ ወደ እርሱ ሜዳ እስኪመጣ ድረስ ፋኖዎችን የሚያፍስ እና ለወራሪዎች ስንቅ የሚያደርስ የጭነት መኪና ሲቆጥር ይውላል፡፡
ጅምላ ጨራሽ መሳሪያ በአውሮፕላን የሚጫንለት ጠላት ባለበት ሁኔታ ‹‹ጥቁር ክላሽ ታጥቀኻል›› ተብሎ ሲንገላታ ይከርማል፡፡ ሰላማዊ ሕይወትን ብቻ ሳይሆን ለጦርነት መዘጋጀትን ተነፍጎ በክልሉና በፌደራሉ መንግሥት ሲዋከብ ይሰነብታል፡፡ ከዚያም ከወንዝ ማዶ ከባድ መሳሪያ የሚተኩስና ወደ እርሱ ቀዬ የሚገሰግስ ጠላት ተመልክቶ መንግሥትን ፍለጋ ዐይኑን ሲያዞር ብቻውን ቁሞ እራሱን ያገኘዋል፡፡
ባንድ በኩል ያለ ጦርነት መኖር የማይችል ጠላት እጁን ስቦ ወደ ትግል ያስገባዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የማሸነፍ ፍላጎት የሌለው መንግሥት በትግሉ እኩሌታ ላይ እግሩን ወልክፎ ያለ ድል ያስቀረዋል፡፡
እናም የዚህን ቁማርተኛና ዳተኛ መንግሥት ባሕሪይ ስትታዘብ በእነ በላይ ዘለቀ ሲመራ የነበረው መንግሥት አልባ ትግል ይናፍቅኻል፡፡