>
5:18 pm - Saturday June 14, 1451

የዮናታን እጅግ አደገኛ መንገድ (ሳይቃጠል በቅጠል)...!!! አብርሃም ይሄይስ

የዮናታን እጅግ አደገኛ መንገድ

(ሳይቃጠል በቅጠል)…!!!

አብርሃም ይሄይስ

ይህ ጽሑፍ በፍጹም ሃይማኖታዊ አይደለም…!

ሰሞኑን አንዳንድ ኦርቶዶክሳውያን ወዳጆቼ በዮናታን የቴሌቪዥን ጣቢያ ተላልፈው በዩቲዩብ የሚለቀቁ መረጃዎችን በመመልከት ‹‹አካሄዱ ትክክል አይደለም . . . በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንቶች መካከል ጸብ ለመፍጠር ይመስላል›› እያሉ ስጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡

አንዱ ጓደኛዬ ‹‹እስኪ ወንድ ከሆነ ከሙስሊም ተከታዮች ቆባቸውንና ሂጃባቸውን አድርገው የተመለሱ/የተለወጡ ሰዎችን ያሳየን? . . . አንገታቸው ላይ መስቀል ያሰሩ ወጣቶችን ብቻ ለምን ያሳየናል?›› የሚል ጥያቄ አነሳ፡፡ ምንም የለም፣ ምክንያቱም ዮናታን የሚያሸፍተውና የሚዘርፈው ኦርቶዶክሳውያንን ነው፡፡ ጸብ መፍጠር ሆነ ማሸነፍ የሚፈልገው፣ ማብሸቅና ማናደድ የሚፈልገው ኦርቶዶክሳውያንን ነው፡፡

ለማንኛውም እስኪ ልይ ብዬ የተለቀቁትን ማየት ጀመርኩ፤

ክፍል አንድ

የጨርቆስ ልጆች ነን ከሚሉ ልጀምር

የጨርቆስ (ቂርቆስ) አካባቢ ማኅበረሰብ እጅግ በማሕበራዊ ኑሮ የጠነከረ፣ ለእምነቱ ሟች፣ ለሰማዕቱ ቅዱስ ቂርቆስ ደግሞ የተለየ ፍቅር ያለው ሰው (ወጣት) የሚኖርበት አካባቢ ነው፡፡ የአካባቢው ወጣት በማሕበር ተደራጅቶ ነዳያንን የሚረዳ፣ የታረዘ የሚያለብስና የተራበ የሚመግብ ወጣት በብዛት ያለበት ሰፈር ነው፡፡ ብዙ እጅግ ብዙ የሀገር ባለውለታዎች የወጡበትም ሰፈር ነው፡፡ በአካባቢው የተለያየ ሃይማኖት ተከታዮች ያሉበት፣ የተለያዩ ብሔረሰቦች በፍቅር የሚኖሩበት፣ የኢኮኖሚ ልዩነት ሳይሆን ሰው መሆን የሚያሸንፍበት አካባቢ ነው፡፡ በተቃራኒው ወጣቶቹ በሱስ ለመያዝ፣ በማሕበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የሌለውን ድርጊቶች ለመፈጸም ተጋላጭ የሆኑበትም አካባቢ ነው፣ ጥቂት ወጣቶችም በዚህ ተግባር ላይ እንደሚሳተፉ እሙን ነው፡፡

ዮናታን የተጠቀመው የመጨረሻውን መገለጫ ነው፡፡ ‹‹ምስክሮቹ›› እንጠጣ ነበር፣ እናጨስ ነበር፣ እንቅም ነበር፣ ወላጆቻችንን እናሳዝን ነበር›› አሉና አንደኛው ‹‹በአካባቢያችን ቸርች ክፈትልን›› አለ፡፡ ይህ ምስክርነት ሲተላለፍ ብዙ የአካባቢው ሰዎች ተናደዱ ይበልጥም ‹‹ከጨርቆስ ሰማይ ሥር›› የሚባል የፌስቡክ አካውንትም ስማችንን እያጠፋ ዛቻ ደረሰብን፣ ገንዘብ ተሰጥቶን ነው የመሰከርነው ካላችሁ እንተዋችኋለን ተብለናል እኛ ግን አሁን ከገባን እውነት አንነቃነቅም›› አሉ፡፡ ከ‹‹ጨርቆስ ሰማይ ሥር›› የሚለውን አካውንት ከፍታችሁ ስታዩ ስለእነዚህ ሰዎች ምንም ተጻፈ ነገር የለም፣ ብዙ በጎ በጎ ነገሮች ብቻ ነው ፖስት የተደረጉት፡፡ በዚህ አጋጣሚ ገጹን ላይክና ፎሎው አድርጉ፤

ትዝብቴ

ወጣቶች ከተለያየ አካባቢ፣ ከተለያዩ የማሕበረሰብም ሆነ የእምነት ቦታዎች በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ዮናታን ፕሮጄክት ይሄዳሉ፡፡ (ወደብዙ መፍትሔ አለን ወደሚሉ ቦታዎች እንደሚሄዱት) ይሄ መብታቸው ነው፡፡ ማንም የሰጣቸው፣ ማንም የሚነፍጋቸው አይደለም፣ ሊኖርም አይገባም፤

የምስክርነቶቹ ዓላማ ወጣቶቹን መልካም ወጣት ማድረግ ነው? ወይስ ሰፈር እየጠቀሱ በጓደኛሞች፣ በማሕበረሰቦችና በሃይማኖት መካከል ጸብ መፍጠር? . . . የእነዚህ ወጣቶች ዓላማ ምንድን ነው?

‹‹እናቴ ታማ ማንም አልጠየቃትም፣ ጎረቤቶቻችንም አልጠየቁንም . . . ወንድሜ ሲሰክር ማንም ቀርቦ አልጠየቀውም›› የሚሉ ምስክርነቶች ቂም ካረገዘና ወደፊት ሊበቀል ካሰበ ወጣት የሚጠበቅ እንጂ ወደ መልካም ወጣትነት የሚሄድ ወጣት የሚመሰክረው ነው?

‹‹በአካባቢያችን ቸርች ክፈትልን›› የሚሉት ዮናታን ማን ነው? . . . ቸርች የሚያስከፍት አቅም (ጀርባ) ከየት አመጣ . . . ከዚህ በፊት ጨርቆስ አካባቢ ቸርች የለም? . . . እነዛ ቸርቾች ከዮናታን ጋር ያላቸው አንድነትና ልዩነት ምንድን ነው? . . . ወጣቶቹ ወደነባሮቹ ቸርቾች እንዳይሄዱ ለምን ተፈለገ? . . . ነባር የጨርቆስ ልጅ የሆኑ ፕሮቴስታንቶችስ የሉም? . . . እንዴት ነው ፕሮቴስታንቶቹ ከጨርቆስ የኦርቶዶክስ ማሕበረሰብ ጋር በፍቅርና በአንድነት የኖሩት? . . . የ‹‹ለሚከፈተው ቸርች ፓስተሩ አንተ ነህ›› ተብሎ ተስፋ የተሰጠው ወጣት ከአሁን በኋላ ዝም ብሎ ይቀመጣል ተብሎ ይታሰባል? (ፓስተሮች ምን ያህል ሀብታም እንደሆኑ ይታወቅ የለ)

እንደዚህ ዓይነት ምስክርነትስ ለምስክሮቹ ጥሩ ነው? . . . ተወልደው ካደጉበት ጎረቤት ጓደኛ ካፈሩበት ሰፈር ልጆች ጋር በሰላም ያኗኑሯል? ፕሮቴስታንት ሲሆኑ በአካባቢው እነርሱ የመጀመሪያ ናቸው?

እየተስተዋለ . . . ከነ መምሕር ምሕረተአብና ከዬኔታ ቲዩብ ጋር ለተገባ እሰጥአገባ በትውልድ መካከል ጸብ መፍጠር፣ ቂምና ጥላቻ ማትረፍ እንዲሁ በቀላሉ የሚፈታ ነገር አይደለም::

‹‹ተቀምጠው የሰቀሉት ቆሞ ለማውረድ ይቸግራል›› እንዲሉ አበው

Filed in: Amharic