>
8:22 pm - Thursday March 23, 2023

አማራው ለድርድሩ ምን ይዞ ይቅረብ? (ጌጥዬ ያለው)

አማራው ለድርድሩ ምን ይዞ ይቅረብ?

ጌጥዬ ያለው

ፕሬዚደንት ጆ ባይደን የሰብዓዊ ድጋፍን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ የትግራይ  መስተዳድርን ከእነ ሶሪያ እና አፍጋኒስታን እኩል በሉዓላዊ ሀገርነት ጠርተዋታል። የኢትዮጵያን ስም አላነሱም። በርግጥም ነገሮች ሁሉ አሜሪካ ትግራይን ከኢትዮጵያ የገነጠለቻት ይመስላሉ። ባለሥልጣናቷ ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ ከአዲስ አበባ እኩል መቀሌን መርገጣቸውም ለዚህ ነው። ትግራይ ለዘላለሙ በዓለም የምግብ ርዳታ ድርጅት በኩል ቁርስና ምሳዋ እንዲላክላት ተዋውላ መሆን አለበት¡
የሰሞኑ ድርጊቷ አሜሪካ ኢትዮጵያን የማፍረስ ውጥን እንዳላት የሚጠቁም ነው። የትግራይ ወራሪ ሃይል ባንዳነት ሲጨመርበት ውጥኑ የደምደም ዕድሉ ሰፊ ነው።    የአሜሪካ “ኤር ናሽናል ጋርድ” ከኮኔቲካት ተነስቶ ወደ ጅቡቲ ማቅናቱ ይፋ ሆኗል። የዚህ ቡድን ዋነኛ ሚና በተለያዩ የአሜሪካ ጦር ቀጣናዎች ከመሳሪያ ማቀበል እስከ ስለላ ይደርሳል። ሚናው ሌሎች አውሮፕላኖች በማያርፉበት ሜዳ ላይ በማረፍ ቁሳቁስ፤ የኮማንዶ/አየር ወለድ ሃይል ማመላለስ፣ መረጃ መሰብሰብ፣ በሳተላይት የጠላትን እንቅስቃሴ መከታተል፣ የታጠቁ ድሮን በራሪዎችን ማሰማራት እና በጠላት ላይ ጥቃት መፈጽምን ሁሉ ያጠቃልላል። እነዚህንም ተግባራት በኢራቅ፣ በሶሪያ፣ በሊቢያ እና በአፍጋኒስታን ጦርነቶች ላይ ሲከውኑ የጦር ፈጥኖ ደራሽ (Rapid deployment force) እንደሆነ የማይዘነጋ ታሪክ ነው። ይህንንም ከራሳቸው የተሰጡ መግለጫዎች ያስረዳሉ። የትግራይ ወራራ ሃይል ዳግም ጦርነቱን ለኩሶታል። ከዚህ ቀደም ብሎ ከባድ መሳሪያ እና ድሮን ከዩክሬን ማስግገባታቸውን የሚያጋልጡ መረጃዎች በወጡበት ወቅት ይህ የአሜሪካ  ፈጥኖ ደራሽ ሃይል ወደ ጂቡቲ በአስቸኳይ መላኩም ‘የወያኔን ጦር ለመርዳት ነው’ ቢባል ስህተት አይሆንም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በዚያው የአማራ ሲቪክ ድርጅቶችን በድርድሩ ጉዳይ እያወያየ ነው።   ከማይክ ሐመር ጋር ውይይት እንዲያደርጉ ባለፈው ሳምንት ምስጢራዊ ጥሪ ተደርጓል። ከፊሎቹ ተወያይተዋል፤ ከፊል ድርጅቶች በቀጠሮ ላይ መሆናቸውን የውስጥ አዋቂ መረጃዎች ያመላክታሉ። ታዲያ ጥሪው በገለልተኝነት ለማወያየት ነው፣ ለማዘናጋት፣ ለማስጠንቀቅ ወይስ የአማራውን የልብ ትርታ ለመለካት? ይህንን ጥያቄ እያንሰላሰሉ ለውይይት የሚቀርቡ አማሮች ወይም ሌሎች ኢትዮጵያውያን ሊያነሷቸው የሚገቡ ጥያቄዎች ምን ምንድን ናቸው?

የአማራው ጥያቄዎች

ሀ. ገዥው ኦሕዴድ-ብልፅግና በሽብርተኝነት እንዲፈረጅ  መጠየቅ
የአብይ አሕመድ አገዛዝ በአማራ ብሔር እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ እየተፈፀመ ላለው ተከታታይ የዘር ማጽዳት ቀጥተኛ ተጠያቂ መሆኑ እሙን ነው። በመሆኑም ዓለም በሕግና ሥርዓት የምትመራ ከሆነ በጅምላ ጭፍጨፋ ወንጀል ሊከሰስ እና በሽብርተኝነት ሊፈረጅ ብሎም ሥልጣኑን ለሕዝባዊ የሽግግር አስተዳድር አስረክቦ መልቀቅ አለበት።
አማሮች ይህንን ጥያቄ ስላቀረብን በቀጥታ ተቀባይነት ያገኛል ማለት አይደለም። ቅቡልነት ቢያገኝ እሰየው ነው፤ ባያገኝም አደራዳሪ ሆኖ ለቀረበው የአሜሪካ መንግሥት የህመማችንን ልክ ለማስረዳት ተገቢ ርቀት ነው። ስላለፈው ጥፋት ብቻ ሳይሆን ኦሕዴድ-ብልፅግና ወደ ፊት ስለሚፈፅመው የሀገር ብተና አደጋ ሲባል ጥያቄው በዚህ ልክ መነሳት አለበት። ወደ ፊት አማራ ለሚመሰርተው የዘር ማጥፋት ክስም መሰረት ነው።
ምንም እንኳን ይሄም ሞራላዊ ቢሆንም፤ የአብይ አገዛዝ በሽብርተኝነት ካልተፈረጀ ታንቀን እንሞታለን ወይም የባይደን አስተዳድር ላይ እናምፃለን አላልንም። አራት አመት ሙሉ የተደበደብንበትን ቁስል ግን ሙሉ በሙሉ ገልበን ማሳየት ልንከለከል አይገባም። ቁስላችንን በትክክል የሚያሳየው ይህ ጥያቄ ነው። ይህንን ጥያቄ ማቅረብ ያልተገባ ወይም አፈንጋጭነት መስሎ የሚታያችሁ ካላችሁ የተገደለብንን አስክሬን ከማንሳትና አልቅሶ ከመቅበር የተለየ እንዳልሆነ አጢኑት።
አሜሪካኖቹ ለውይይት የሚጋብዙን በድርድሩ ምን መወሰን እንዳለበት የራሳቸውን አቋም ይዘው ሊሆን ይችላል። የእኛ አስተያየት የተፈለገው በውሳኔው የመደሰትና የመከፋት መጠናችንን፤ የልብ ትርታችንን ለማወቅ ሊሆንም ይችላል።
ለዚህ ተገቢው መልስ ማዕከላዊው አገዛዝ እና ወያኔ ራሱ በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ መጠየቅ ነው። ይህን ስንል ቴክኒካዊ ጉዳዮች የሕግ መስመሮች ስለሚሆኑ ከእነ ማይክ ሐመር ጋር በሚደረገው ውይይት በዝርዝር አንገባበትም። ፖለቲከኞቹ  የዘር ማጥፋት ወንጀሎቹ በእነዚህ ሁለት ጸረ አማራ ቡድኖች መፈጸማቸውን ካመኑ በቂ ነው። ይህን ካመኑ ከእነርሱ የምንፈልገው ፖለቲካዊ ፍርድ ነው። የሕግ ፍርዱን ለሕግ ተቋም እናቀርባለን።
አሜሪካኖች በሥልጣን ላይ ያሉ መንግሥታት በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። በጎረቤታችን ሱዳን፤ የልበሽር መንግሥት ኦሶማ ቢላድንን በመደበቅ ተወንጅሎ በቢል ክሊንተን ፕሬዚደንትነት ዘመን በሽብርተኝነት መፈረጁ ይታወሳል።
ለ. በድርድሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መወከል እንዳለባት መጠየቅ
ፖለቲካ እና ሃይማኖቶች የተፋቱ መሆናቸው በግልፅ በሕግ ቢደነገግም ፖለቲካው ቅድስት ቤተክርስቲያን ላይ እየፈፀመ ያለውን የዘር ማጥፋት ግን አላቆመም። የደርግ መንግሥት ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እየተጠቃች ነው። በመሆኑም ባለጉዳይ ነች፤ የድርድሩ አካል መሆን አለባት። መስቀል ተሸክማ ክራባት ካሰሩ ፖለቲከኞች ጋር የምትቀመጠው የፖለቲካ ሥልጣን ወይም ውክልና ፈልጋ አይደለም። ሁለት ነገሮችን ግን ትፈልጋለች፦
1.ጥቃቱ ወደፊትም በመንግሥታት ቅብብሎሽ እንዳይቀጥል ያላትን የህልውና ስጋት ማሳወቅ
2. ባለፉት 4+27+17 ዓመታት ለደረሱባት የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ፍትሕ መቀየቅ
ይህንን ጥያቄ መንፈሳዊ ማህበራት ቢያቀርቡት ተመራጭ ነው። እነርሱ ከሌሉ ወይም ማቅረብ ካልፈለጉ ግን አማራው ሌላ ድርጅት የማቅረብ ታሪካዊ ግዴታ አለበት።
ሐ. የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እና በሌሉበት የተከሰሱት ክሳቸው እንዲቋረጥ መጠየቅ
አዛዎንቱ ጋዜጠኛ እና የታሪክ ጸሐፊ ጋሽ ታዴዎስ ታንቱ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ በአፋር፣ በኦጋዴን፣ በአዲስ አበባ፣ በአማራ መስተዳድር እና በሌሎችም  ታጉረው የሚገኙ ፋኖዎች . . .  በአስቸኳይ ምርመራቸው (ክሳቸው) እየተቋረጠ እንዲፈቱ መጠየቅ አስቸኳዩ ጉዳይ ነው።
መ. በድርድሩ ፋኖ እንዲወከል መጠየቅ
እዚህ ላይ መድረኩ የሲቪሎች እንጂ የታጣቂዎች አይደለም በሚል በሩ ሊዘጋ ይችላል። ሆኖም ፋኖ ሀገርን ከፍርሰት የታደገ፣ አሁንም በየ ምሽጉ በጦር ግንባር የሚገኝ መሆኑን ጠቅሶ የፖለቲካ ሥልጣን የመያዝ ፍላጎት ስለሌለው ሲቪል ወኪል እንደሌለው፤ አስፈላጊ ከሆነ ግን አሁን ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ማቋቋም እንደሚችል ማስረዳት አስፈላጊ ነው። ወያኔም ሆነ ማዕከላዊ አገዛዙ ወታደሮቻቸውን ከጀርባ አሰልፈው የሚደራደሩ መሆኑም መጠቀስ አለበት።
ሠ. ፌዴሬሽኑ እንዲፈርስ መጠየቅ
ፌዴሬሽኑ ከፈረሰ የክልል አጥሮች፣ የየመስተዳድሩ ልዩ ሃይሎች፣ የሕገ መንግሥቱ ችግሮች፣ የሰንደቅ አላማ ጣጣ፣ የብሔራዊ መዝሙር ጣጣ ሁሉ አብረው ይፈርሳሉ። ገነጣጣይ ወጋግራዎች ሁሉ አብረው ይነቀላሉ።
ረ. በመጨረሻም ፖለቲከኞችን በተለይም ሽብርተኞችን እና ገንጣዮችን ማለትም ኦሕዴድ-ብልፅግና-ን፣ ወያኔ-ን፣ ኦነግ-ን እና ኦብነግ-ን ያገለለ የባለሙያዎች ባለአደራ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ሁኔታዎችን ማመቻቸት አስፈላጊ ነው
ዛሬ ረቡዕ በራያ ግንባር የተጀመረው ጦርነት በአጭር የማይቆም ከሆነ አማራ በደስታ ሊገባበት ይገባል። አማራ በታሪኩ በጦርነት አትርፎ እንጂ ከስሮ አያውቅም። አድዋ ላይ ባንዋጋ ኖሮ  የዓለምን የነጭና ጥቁር የፖለቲካ ሚዛን ልንቀይር ቀርቶ ለራሳችንም ቅኝ ተገዥዎች ነበርን። ማይጨው ላይ ባንዋጋ ኖሮ ተንበርካኪዎች ነበርን። ባለፈው አመት ከትግራይ ወራሪ ሃይል ጋር ባንፋለም ኖሮ ራያ እና ወልቃይትን መልሰን በእጃችን አናስገባም ነበር።
ጦርነት ጎጂ ብቻ ሳይሆን መፍትሔም ነው!
ዓለም ከጦርነት ወጥታ አታውቅም። ሁልጊዜ የሰላም ሽምግልናዎች ቢደረጉም ሁልጊዜ አፈሙዞች እንደተፋጩ ናቸው። ይህ የሚሆነው ሀገራት ጠባጫሪዎች ስለሆኑ ሳይሆን ጥቅማቸውን ለማስከበር ስለሚሞቱ ነው። የጦር እና የምጣኔ ኃብት የበላይነትን ለመያዝ ዓለም ዛሬም ትናንትም እየተዋጋ ነው። የዛሬዋ አሜሪካ መልክ መሰረቷ የተጣለው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ነው። በምስራቁ ዓለም ላይ የበላይነትን ከመውሰዷም በላይ የምዕራባውያን መሪ አድርጓታል። የምስራቁ ዓለምም ለዘላለም እጅ ሰጥቶ የሚኖር አይደለም። የቀደመ የበላይነታቸውን ተነጥቀው በሩሲያ መሪነት የቆዩ የምስራቁ ዓለም ሀገራት ዛሬ ቻይናን የመሰለች የምዕባውያን ተገዳዳሪ ጉብል አድርሰዋል።
ምዕራብና ምስራቅ ዩክሬን ላይ ጎድበው ሲዋጉ ከርመዋል። ሰሞኑን ደግሞ ታይዋን ሌላኛዋ የጦር አውድማቸው እየሆነች ነው። በእስራኤል እና ፍልስጤም የሚደረገው ጦርነትም አገርሽቷል። ይህ ሁሉ ሲሆን ቱርክ የሩሲያ እና የዩክሬን አደራዳሪ፣ ግብፅ ደግሞ የእስራኤልና የፍልስጤም ሸምጋይ በመሆን ጠረንጴዛውን ከበውታል።
ድሉ ግን የአፈ ሙዝ እንጂ የጠረንጴዛ አይደለም። ጦርነቱ አሸናፊና ተሸናፊውን ከበየነ በኋላ የይስሙላ መፈረሚያ ነው፤ ሽምግልና።
የትግራይ ወራሪ ሃይል ዳግም በአማራ ላይ ያወጀው ጦርነትም ከላይ ከጠቀስኩት አውድ ውጭ አይደለም። የሰርጌ ላቭሮቭ እና ማርያ ዛካሮቫ አዲስ አበባን መርገጥ፤ ይባስ ብሎም አሜሪካ በሸምጋይነት አንዳዴም በአዋጊነት በምትሳፍበት የትግራይ ጦርነት የሩሲያ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሰሞኑን መግለጫ መስጠቱ ‘ትግራይ እንደ ዩክሬን እና ታይዋን’ ማስባሉ አይቀርም። ያበጠው ይፈንዳ!
ይህ ጦርነት ለአማራ አፅመ ርስቶቹ ወልቃይት፣ ራያ፣ ጠለምትና ጠገዴ  ባለቤትነቱን ማረጋገጫ ብቻ አይደለም። ወደ ቀደመ የፖለቲካ የበላይነቱ መመለሻ መንገዱም ነው።
Filed in: Amharic