>

በወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ አገምሳ ከተማ የሸኔ ታጣቂዎች 55 ሰዎች ገደሉ...  ( DW)

በወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ አገምሳ ከተማ የሸኔ ታጣቂዎች 55 ሰዎች ገደሉ… 

DW

151th EHRCO Special report september 2022 *…. “ ፋኖ ነን” ያሉ የታጠቁ አካላት ወደ ከተማዋ ገብተው ከኦነግ ጋር አብራችኋል በሚል በመደዳው ከተማዋ ላይ ተኩስ በመክፈታቸው ከ15 ሺህ የማያንሱ የከተማዋ ነዋሪዎች ከተማዋን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል

በኦሮሚያ ክልል ሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ አገምሳ ከተማ ትናንት ከማለዳ ጀምሮ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ ቢያንስ 55 ሰዎች ተገደሉ፡፡የአከባቢው ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ለአንድ ዓመት ያህል የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች በመደበኛነት ተመድበው የአከባቢውን ፀጥታ ሲያስከብሩ ነበር፡፡ ይሁንና ባለፈው ዕሁድ ነሃሴ 22 ቀን 2014 የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ከከተማዋ መነሳታቸውን ተከትሎ የተለያዩ ስያሜ ያላቸው ታጣቂዎች በከተማዋ መፈራረቃቸውን ነው የአይን እማኞች የገለጹት፡፡

አቶ ንጉሴ ባንጃ የተባሉ የአይን እማኝ ለዶይቼ ቬለ «መንግስት ‘ሸነ’ ያላቸው “የኦሮሞ ነጻነት ጦር” ሰኞ ጠዋቱን ገብተው ከተማዋን ተቆጣጠሩዋት፡፡” ብለዋል፡፡ የአይን እማኙ አክለውም እንዳብራሩት ታጣቂዎቹ ከተማዋ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መንቀሳቀስ ከጀመሩ በኋላ ወደ 59 መሳሪያ ከማህበረሰቡ አስፈትተው በዚያው ሰኞ ቀን ከተማዋን ለቀው ወጥተዋል፡፡

አቶ ንጉሴ አክለው በሰጡን አስተያየታቸው፤ “ትናንት ማክሰኞ ጠዋት ደግሞ ፋኖ ነን ያሉ የታጠቁ አካላት ወደ ከተማዋ ገብተው ከኦነግ ጋር አብራችኋል በሚል በመደዳው ከተማዋ ላይ ተኩስ በመክፈታቸው ከ15 ሺህ የማያንሱ የከተማዋ ነዋሪዎች ከተማዋን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል” ነው ያሉት፡፡ ከትናንት ማታ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የ55 ሲቪል ዜጎች አስከሬን መቅበራቸውን የሚናገሩት እኚው አስተያየት ሰጪ “ከማህበረሰቡ 87 ሰዎች የጠፉ በመሆኑ የ32 ሰዎች አስከሬን በየጫካውና በየገደሉ እየፈለግን ነው” ሲሉም የችግሩን ስፋት አስረድተዋል፡፡

በመምህርነት ሙያ የተሰማሩት ቢቂላ ዓለሙ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸዉ በጸጥታ ችግር ምክንያት ከየገጠር ቀበሌያት የተፈናቀሉ የተለያዩ የማህበረሰብ አካላት በዚሁ “የፋኖ ታጣቂዎች” ባሏቸው በተፈጸመው ጥቃት ከተማዋን ለቀው ተሰደዋል፡፡

ኒሞና ዴሬሳ የተባሉ አስተያየታቸውን የቀጠሉ ሌላው በመምህርነት ሙያ የሚተዳደሩ ነዋሪ እንዳሉት 20 አስከሬኖችን በአይናቸው አይተው ስማቸውንም መመዝገባቸውን አስረድተዋል፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ከ40 በላይ ቁስለኞች መታከሚያ ቦታ እንኳ አጥተው ‘አስከፊ’ ያሉት ችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የነዋሪዎች ንብረት የሆኑ ከብቶችን ጨምሮ በርካታ ሃብት መዘረፋቸውንም አንስተዋል፡፡

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የአሙሩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፋንታሁን ታዬ ስለሁኔታው ማብራሪያቸውን እንዲሰጡ ከዶይቼ ቬለ ለቀረበላቸው ጥያቄ ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ ሳይሰጡ፤ ከህበረተሰቡ ጋር በውይይት ላይ መሆናቸውንና ነገ መልስ እንደሚሰጡ አስረዱ፡፡

የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ስዩም ጌቱ ለኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለኦሮሚያ ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ እንዲሁም ለኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣናት የእጅ ስልካቸው ላይ ቢደውልም ምላሽ ባለመስጠታቸው ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

Filed in: Amharic