>

የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የፍርድ ቤት ክርክር ለመጪው ዓመት ተሸጋገረ...!!! (ኢትዮ ኢንሳይደር)

የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የፍርድ ቤት ክርክር ለመጪው ዓመት ተሸጋገረ…!!!

ኢትዮ ኢንሳይደር

*…. የዛሬውን የችሎት ውሎ ዝርዝር ዘገባ

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ በቀረቡ የሰነድ ማስረጃዎች ላይ የተከሳሽ ጠበቆች ያቀረቡትን አስተያየት እና ዐቃቤ ለአስተያየቱ የሰጠውን ምላሽ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 10፤ 2015 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ። ፍርድ ቤቱ ከዚህም በተጨማሪ ጋዜጠኛው ካለበት የጤና ችግር በተያያዘ እንዲፈቀዱለት የጠየቃቸው ጉዳዮች በማረሚያ ቤት ተፈጻሚ እንዲሆኑ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

በጋዜጠኛ ተመስገን ላይ የቀረበውን ክስ በመመልከት ላይ የሚገኘው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ችሎት ለዛሬ አርብ ነሐሴ 27፤ 2014 ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው፤ ዐቃቤ ህግ በክስ መዝገቡ ባያያዛቸው የሰነድ ማስረጃዎች ላይ የተከላካይ ጠበቆች በጽሁፍ ያቀረቡትን አስተያየት መርምሮ ብይን ለመስጠት ነበር። ሆኖም የፌደራል ዐቃቤ ህግ ከቀጠሮው ሶስት ቀናት አስቀድሞ ለፍርድ ቤቱ በጻፈው ደብዳቤ፤ በጠበቆች  አስተያየት ላይ መልስ መስጠት እንዲችል ይፈቀድለት ዘንድ በመጠየቁ፤ ችሎቱ በዛሬው ውሎ ይህንኑ ጉዳይ ወደ መመልከት ዞሯል።

ጋዜጠኛ ተመስገን በዛሬው የችሎት ውሎ የመናገር ዕድል እንዲሰጠው ጠይቆ በፍርድ ቤቱ ተፈቅዶለታል። በዐቃቤ ህግ የአቤቱታ ደብዳቤ ላይ እርሱን በተመለከተ የቀረበው “የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በመተላለፍ” እንደሆነ የጠቀሰው ጋዜጠኛው፤ ከዚህ ቀደምም ዐቃቤ ህግ “መከላከያ ሰራዊት በተደጋጋሚ ጊዜ አስጠንቅቆታል” በማለት በችሎት መናገሩን አስታውሷል።

“ሁላችንም እንደምናውቀው የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ካጠፉ በህግ ይጠየቃሉ። የሰሩት ወንጀልም ካለ በሚዲያ ይጋለጣሉ። ሆኖም ዐቃቤ ህግ የሚያቀርበው በህግ የማይጠየቁ፣ የማይከሰሱ አድርጎ ነው” ሲል ለፍርድ ቤቱ የገለጸው ጋዜጠኛ ተመስገን፤ ዐቃቤ ህግ “የመከላከያ ሰራዊትን ተገን አድርጎ” እንዲህ አይነት ገለጻዎችን በተደጋጋሚ የሚጠቀመው “እኔን በእስር ቤት ለማቆየት ነው” ሲል አጽንኦት ሰጥቷል።

የተከሰሰበትን ጉዳይ የሚመለከተው ችሎት “በነጻነት ይሰራል” ብሎ እንደሚያምን ለዳኞች የተናገረው ተመስገን፤ ሆኖም እርሱ በእስር እንዲቆይ የመከላከያ አመራሮች ከኋላ “ተጽዕኖ ያደርጋሉ” የሚል እምነት እንዳለው ገልጿል። በዛሬው ችሎት ከተሰየሙ ሶስት ዳኞች መካከል የመሃል ዳኛው የተከሳሹን ንግግር አቋርጠው “ይህን ያስባልዎት ነገር ምንድንነው?” ሲሉ ጠይቀዋል።

* * የዛሬውን የችሎት ውሎ ዝርዝር ዘገባ ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፦ https://ethiopiainsider.com/2022/7946/

Filed in: Amharic