>

ስለ ጅሎች ጅላጅሎችና ስለ ጅላንፎው የክልል ጠያቂው የጉራጌ ህዝብ (ብርሃኑ ዘርጋው)

ስለ ጅሎች ጅላጅሎችና ስለ ጅላንፎው የክልል ጠያቂው የጉራጌ ህዝብ

ብርሃኑ ዘርጋው

berhanuz@gmail.com


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ብዙ መናገር ያውቁበታል። ጥልቀት ያለው ንግግር  ያለመሆኑንና ስላቅ እንደሆነ የሚያውቀውም አዳማጩ ብቻ ይመስለኛል። በንግግራቸው ተስበው ድጋፍ ካልነፈጉዋቸው ጅላጅሎች መሃል አንዱ ነኝ። ያኔ ገና መንበሩን እንደተቆጣጠሩ ሆ ብሎ የተቀበላቸው የትግሬና የአማራ ህዝብ የመሄጃቸውን ጊዜ እየተጠባበቀ ይመስላል። በኔ የእድሜ ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ለአገራችን ለኢትዮጵያ ብዙ ከማለማችን የተነሳ ህልማችን ዕውን እንዲሆን በሚል ያላሰለሰ ድጋፍ ሰጥተናቸው እንደ ነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። እሳቸው ግን ጥቅሻ የማይገባቸው ጅል መሆናቸውን ደጋግመው በሚያደርጉት ከስራ የተፋታ ዲስኩር ልንገነዘብ ችለናል። ለህዝብ ስሜት ግድ የሚሰጣችው አልሆኑም፡፡ ለህዝብ ሰላም: ደህንነት፡ ጤንነትና ደስታ አረንጉዋዴ አብዮትን እንደ መፍትሄ ከማናፈስ በቀር የተሻለ አማራጭ አለቀረቡም። አገራችን ሰላም የናፈቀችውን ያህል የሽብር የሞትና የጦርነት ቀጠና ሆናለች። 

ሰሞኑን ለብልጽግና የወጣት ሊግ ስብስብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ላደረጉት የጥያቄዎች መልስ የታዘብኩትን ሶስት ነገሮች ጠቅሼ የታዘብኩትን የተሰማኝንና የመፍትሄ ሃሳቤን ለማካፈል እሞክራለሁ።

  • ዲሞክራሲ ዲሞክራሲ አሁንም ባዶ ዲሞክራሲ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዲሞክራሲን ለራሳቸው እንጂ ለሌላው መስራት ያለበት አይመስላቸውም። ሁለት ምሳሌዎችን ላንሳ፦ መንግስታቸው በግፍ ያሰራቸውን ጋዜጠኞች እና የጉራጌ ህዝብን የክልል ጥያቄ ለማኮላሸት የሚደረገው የማስፈራራትና የማሰር ርምጃ አሁንም አለመቆሙ ነው። ይህ የዲሞክራሲ እጦት ግለ ሰቦችንና የመንግስት ሰራተኞችን ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ከመጨፍለቅ በላይ አምባ ገነንነትን መጠቀሚያ እያደረጉት ነው። እነ ተመስገን ደሳለኝ እነ ታድዮስ ታንቱ አይነተኛ ምሳሌዎች ናቸው። ስለ ዲሞክራሲ የሚሉት ከተግባራቸው ጋር ሲነጻጸር ውሃ ያልቁዋጠረ ዳመና ነው። ባብይ አህመድ ኢትዮጵያ አፈና፡ እገታና ስደት የእለት ተእለት ሰቆቃ መሆን አሁንም አላቆመም። ታፍነው የተወሰዱት ልጃ ገረዶች ከ900 ቀናት በላይ የት እንዳሉ አይታወቅም። በኦሮሞ ክልል ውስጥ የሚፈጸመው የዘር ማጥፋት ዘመቻ ግድ የሚሰጣቸው አይመስልም።በምዕራብና በምስራቅ በደቡብና በሰሜን ለሚፈጸም ቀውስ መልስ የላቸውም። በዲስኩር ሊያልፉት ይሞክራሉ። ጸጸት የሚባል ነገር የሚያልፍባቸውም አይመስልም። ነገር ግን የዲሞክራሲ ጥግ የደረሱ ይመስል ሲያጃጅሉን ኖረዋል። እኛም የጅል ተከታይ በመሆን ተጃጅለናል። ዲሞክራሲን የሚያውቅ መሪ ጀሌዎቹን ልኮ ህዝባችንን አያጠቃም፡፡ የጉራጌ ህዝብ ይህን ውንብድና ለመቀበል ዝግጁ አይደለም፡፡ እጅህን አንሳ፡፡

  1. ጅሎች ጅላጅሎችና ጅላንፎዎች

ከማያቁዋርጥ ዲስኩር በላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዙሪያቸው በከበቡዋቸውና በተከታዮቻቸው ደስተኛ የሆኑ አይመስሉም። ለዚህም ይመስለኛል ጅላጅሎችና ጅላንፎዎች እያሉ ህዝቡንና ደጋፊዎቻቸውን የሚያጣጥሉት። በዚሁ አፋቸው ኢትዮጵያን ከገባችበት የድህነት ኑሮ ለማውጣት ህልም ሰንቆ በዐላማው ጸንቶ ፋሺስቶችን ተዋግቶ ህይወቱን እስከ መሰዋት ያደረሰውን ለአብይም ፅኑዕ ድጋፍ የሆነውን የማህበረ ሰብ ክፍል ሲዘልፍ ይደመጣል። በአብይ ዕይታ ህልም የሚፈቀደው በልጅነት ነው። የህንፃና የመኪና ጋጋታ የዛፍ ተከላ ነው ለጅላጅሎችና ለጅላንፎዎች የሚያስፈልገው ብለው ያመኑ ይመስላል። የክልል ጥያቄ ማንሳትማ ጅላጅሎችና ጅላንፎዎች ስርአተ አልበኝነትንና ቀውስን መፈለግ እንጂ መብትን መጠየቅ አድርገው አያዩትም። ይህም የጠቅላዩን አምባ ገነንነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ጅል አለቅነት ነው። እኛም ጅላጅሎች የሆንነው ጅሉን ስላመንን ነው።

  1. የጉራጌ “ጅላጅሎችና ጅላንፎዎች” ያነሱት የክልል መብት ጥያቄ 

ወደ ገደለው ስናፈጥን የጉራጌ ህዝብ የማንንም ወጭት አልሰበረም። ጦርነት አንስቶ ኢኮኖሚ አላንኮታኮተም። የብልግናና የበደል ተግባር አልፈጸመም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚወዱት ህገ መንግስትን በመጥቀስ ባለም ዙሪያ የሚኖሩ የጉራጌ ተወላጆች በሙሉ ክልል የመሆን መብታቸውን አስረግጠው በስነስርአት እየጠየቁ ነው። ይህንን ነው እንግዲህ ጋጠ ወጥ (አብዩሲቭ abusive) ነው በሚል ለጅላንፎ አድማጮቻቸው ያስተላለፉት መልእክት። ሆኖም የጉራጌ ህዝብ ህገ መንግስቱ የሰጠውን መብቱ እንዲከበር እንጂ እንዲናቅና እንዲሰደብ አይገባውም። 

የጉራጌ ህዝብ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 39 ቁ. 1 መሰረት በማንኛውም መንገድ ያልተገደበ የራሱን ክልል የመሆን መብት አስከብሮ የኢኮኖሚውን የደህንነቱንና የእድገቱን አካሄድ በራሱ እጅ መቆጣጠር ይፈልጋል። ከቁጥር 2 እስከ ቁጥር 5 ያሉት ዝርዝሮችም መብቱን በበለጠ ያጠናክሩለታል። አንቀጽ 43 እና 44 ስለ ልማትና ደህንነት በበለጠ ይገልጻሉ። አንቀጽ 47 ቁ. 2 ህዝብ የራሱን ክልል የማቁዋቁዋም መብቱን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ሰሞኑን እንደምናየው የአብይ መንግስት የህዝብን ዲሞክራሲያዊ መብትን ከማክበር ይልቅ አላስፈላጊ እስራት ከስራ የማባረር ጫና የከተማዎች ወረራና ፍተሻ በማድረግ ጋጠ ወጥ ቁስቆሳ እያካሄደ ይገኛል። ታድያ ማነው ጋጠ ወጡ?

ይህንን መብት በመጻረር ባዘጋጀንላችሁ የክለስተር ስብስብ ካልተደራጃችሁ መብታችሁን እንገፍፋለን የሚል አካሄድ ኢዲሞክራሲያዊና በመንፈስም በግብርም ከዲሞክራሲያዊነት ጋር ግንኙነት የሌለው ነው። በዚህ ጉዳይ የጉራጌ ህዝብ ጅላጅል ወይም ጅላንፎ አይደለም። ጅል አይከተልም። 

ምን ይደረግ?

  1. ህዝብን መስደብና ማዋረድ፤ ሰድቦ ለሰዳቢ መስጠት፤ ንቀትና ማን አለብኝነት ይቁም። ህዝቡን የሚንቅ መሪ ቦታው የማይገባው ነበር ማለት ነው። ይህ ህዝብ ከኛ ትሻላለህ ብሎ ነው ለዛ ቦታ ያበቃህ። አሁን ግን ከኛ አልተሻልክም እያለህ ነው።
  2. የጉራጌ ህዝብ ክልሉን በእጁ ለማስገባት ዝግጁ ነው። ክለስተር ውስጥ መግባት አይፈልግም። የጉራጌን እድል ጉራጌ ይወስናል እያለህ ነው። እኔ አውቅልሃለሁ አትበለው። ህዝቡን አታፍን መሪዎቹን አትሰር ወታደሮችን ከዞኑ አስወጣ። ህዝቡን በካድሬዎችህ ማደናገሩን ተዉን፡፡
  3. ጉራጌ ሆይ፦አብይ እንዳለው ጅላጅልና ጅላንፎ እንዳትሆን። ክዚህ በፊት የተናቅህበትን መጃጃል እንዳትደግመው። ብልጽግና መሪዎችህን ከመጥለፍና ከማጠላለፍ ወደሁዋላ አይልም። አይንህን ዋና ጉዳይህ ላይ ትከል። ከመሃልህ ከግራህና ከቀኝህ ከአላማህ ሊያደናቅፉህ በውሸት ወሬ ሊያጠምዱህ የሚነሱ ሃሳውያን ይነሱብሃል። ካንተ ነጻነትና መብት ይልቅ ለዝናና ለገንዘብ የተገዙ ብዙ እንዳሉ አትርሳ። ሊከፋፍሉህ የሚፈልጉ ብዙ ናቸው። ጉራጌ ነህ። ኢትዮጵያዊ ነህ። የማንም ጥገኛ አይደለህም። አዎ አለም አይበቃህም። የአሁኑ ጥያቄህ ግን ክልል መሆን ነው። ድሉ የአንተ ነው!
Filed in: Amharic