>

"በምንጓዝበት ጊዜ  ኤርፖርት ላይ የተፈጸመው ስሕተት ወይም ኢ-ሕጋዊ የሆነ ድርጊት እጅግ የሚያሳዝን ነው!!!" (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ )

“በምንጓዝበት ጊዜ  ኤርፖርት ላይ የተፈጸመው ስሕተት ወይም ኢ-ሕጋዊ የሆነ ድርጊት እጅግ የሚያሳዝን ነው!!!” 

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ 

“በቦሌ አየር ማረፊያ በቅዱስነታቸውና በልኡካቸው ላይ የተፈጸመው ድርጊት  በድርጅታችን ሠራተኞች የተፈጸመ አይደለም…!!!” 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 

ጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት

ዛሬ ጳጉሜን ፩ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም. ለሕክምና ከቆዩበት ሀገረ አሜሪካ ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ በሰላም የተመለሱት  ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በተደረገላቸው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ ከኢትዮጵያ ሲወጡ በቦሌ አየር ማረፊያ በተፈጸመው ሕገ ወጥ ድርጊት ማዘናቸውን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ድርጊቱ የሚያሳዝንና የታላቋን ቤተ ክርስቲያን ክብር የነካ ሕገ ወጥ ተግባር መኾኑን አሳውቀዋል::

ቅዱስ ፓትርያርኩ ሐምሌ ፲፱ ቀን ፳፻፲፬ ወደ አሜሪካ ለመጓዝ በቦሌ አየር ማረፊያ በተገኙበት ጊዜ አስፈላጊውን ሕጋዊ አካሔድ አሟልተው ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የያዟቸውን ታቦታት እና ንዋያተ ቅድሳት ከሕገ ወጥ ቅርስ የማሸሽ ተግባር ጋር በማያያዝ ክስተቱን በምስል ወድምፅ በመቅረፅ የወነጀሏቸው አካላት ነበሩ።

ድርጊቱ ኾን ተብሎ ከግማሽ በላይ የሚኾነው የሀገራችን ሕዝብ ሃይማኖት የኾነችውን ጥንታዊት እና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊና አስተዳደራዊ አንድነት ለማወክ የተፈጸመ እንደኾነ የተረዳው ጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት የትራስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴርን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን እና የኢትዮጵያ ሲቭል አቬሽን ባለሥልጣንን ማብራሪያ እንዲሰጡ ሐምሌ ፳፯ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም. በቁጥር ጴ/ጥ 0021/21 በተጻፈ ደብዳቤ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለተጠየቀው ጥያቄ በቁጥር ኢአመ/ግኘመኩ/110/14፣ ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ለኅብረቱ በሰጠው ማብራሪያ በቅዱስ ፓትርያርኩና በልኡካኑ ላይ በቦሌ አየር ማረፊያ በተፈጸመው ክስተት ማዘኑንና ድርጊቱም መፈጸም ያልነበረበት አሳዛኝ ድርጊት መኾኑን አጽንኦት ሰጥቶ ገልጿል።  ሠራተኞቹም በዚህ ድርጊት ተሳታፊዎች አለመኾናቸውን አሳውቋል:: አያይዞም ከሀገር የሚወጡ ሃይማኖታዊ ንዋያተ ቅድሳትን፣ ባህላዊና ታሪካዊ ቁሳቁሶችን ሕጋዊነት ማረጋገጥና መሰል ተግባራትን የሚያከናውነው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት መኾኑን ጠቁመዋል።

  በመኾኑም ሌሎች ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁ መንግሥታዊ ተቋማት ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጡ እየጠየቅን፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የቅዱስ ፓትርያርኩን ስም ቅርስ ከማሽሽ ወንጀል ጋር አያይዞ በሐሰት ለማጠልሸት መንግሥታዊ መዋቅርን በመጠቀም በተቀናበረ ኹኔታ የተፈጸመው ሕገወጥ ድርጊት በግልጽ ማውገዝ ይጠበቅበታል። ከግማሽ በላይ የሀገሪቱን ሕዝብ እና በነጻ ኀሊና ለእውነት የቆሙ ዜጎችን ሁሉ ያሳዘነ ተግባር መኾኑን በመገንዘብ ለተፈጸመው ድርጊት ይቅርታ መጠየቅ እና በድርጊቱ የተሳተፉ ሠራተኞቹን በሕግ እንዲጠየቁ በማድረግ በሚሊዮኖች አባት ላይ የተፈጸመው ክብረ ነክ ድርጊት እንዳይደገም እንዲያደርግ እንጠይቃለን።

Filed in: Amharic