>
5:28 pm - Friday October 9, 7096

አብይ አህመድ ተማምነው ጦርነት ይቀጥል ለሚሉ  (ግርማ ካሳ)

አብይ አህመድ ተማምነው ጦርነት ይቀጥል ለሚሉ

ግርማ ካሳ

 

“ጦርነቱ መቀጠል አለበት ፣ ወያኔን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መደምሰስ ያስፈለጋል” የሚሉ : እኛ ድርድር በማለታችን “የወያኔ ተላላኪዎች” በሚል ድንጋይ እየወረወሩ ያሉ አሉ::

ጀነራል ተፈራ ማሞ፣ የአማራ ፋኖዎች፣ ሚሊሺያዎች፣ የአማራ ልዩ ኃይል በአንድ እዝ ስር (ከፌዴራል መንግስቱ ውጭ) መሆን ካልቻሉ ውጤት ማምጣት እንደማይቻል ነው የተናገሩት፡፡

በአሁኑ ጊዜ በሰሜኑ አገራችን ክፍል እየተዋጉ ያሉ ፋኖዎች፣ ሚሊሺያዎች እየተዋጉ ያሉት በብልጽግና መንግስት አመራር ስር ነው፡፡ መከላከያ በሚያሰማራቸው አቅጣጫዎች ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ ያ ማለት የጦርነት እንቅስቃሲያቸውን እየመራ ያለው ዶር አብይ አህመድ ነው፡፡

ፋኖዎችም ሆነ ሌሎች በነ አብይ አህመድ እየተመሩ፣ ቁሙ ሲባሉ  እየቆሙ፣ ተነሱ ሲባሉ እየተነሱ ፣ ብዙ ርቀው መሄድ ይችላሉ ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡፡ በነ አብይ አመራርም የሚደረግ ጦርነት፣  ፋኖን፣ የአማራን ወጣት ማስጨረስ ነው፡፡ ወያኔንም ማሸነፍ አይቻልም፡፡

ማሸነፍ የማንችለውን  ጦርነት ማስቀጠል  ደግሞ ብልህነት አይደለም፡፡ ለዚህ ነው ድርድር አስፈላጊ ነው የምለው፡፡

በአብይ አህመድ አመራር ላይ፣  ይቅርታ ይደረግልኝና ከዜሮ በታች ኔጌቲቭ እምነት ነው ያለኝ፡፡  እንደውም ሆን ብሎ እያሴረ: ነገሮችን እያጏተተ: ሰሜኑን የጦርነት ቀጠና አድርጎ በመሃል ስልጣኑን ማስቀጠል እየሰራም ይሆናል::

“ጦርነት ይቀጥል፣ ትግራይ ይገባ”  የምትሉ፣  የአብይ አህመድ ፕሮፓጋዲስቶች የሚሉትን ብቻ ከመስማት፣  በተለያዩ ዩቱበሮች የሚነገሩትን የተጋነነ ብዙዎቹ የዉሸት የድል ዜና ብለው በሚያቀርቡት በስሜት ከመስከር፣  በትክክል ምን እየሆነ ነው ብለው ከሁሉም አቅጣጫ መረጃዎች አያሰባስቡም ?

የአብይ መንግስት የውሸት ቋት የሆነ፣ ገንዘብ ከፍሎ ውሸት የሚያሰራጩለት ተደማሪ ተለጣፊ ፕሮፓጋዲስቶች እንዳሉት እንዴት ይረሳሉ ?

እውነት የሚናገሩትን ፣ እንደ ጎበዜ ሲሳይ ያሉትን ወደ ወህኒ እየወሰደ ያለ አረመኔ መንግስት አይደለምን ?

የአማራ ኃይሎች በርግጥ አንድ ሆነው፣ ብቃት ያለው አመራር ኖሯቸው ቢንቀሳቀሱ ኖሮ በጦር ሜዳ የተለየ ውጤት ሊገኝ ይችል ነበር፡፡ ጦርነቱም ገና ድሮ ተጠናቆ ነበር፡፡ ግን ያ  ሁኔታ አሁን የለም፡፡ የአማራ ክልል በኦህዴድ ብልፅግና ቀንበር ውስጥ የወደቀ ነው:: ታዛዦች እንጂ ለርሱ የቆሙ መሪዎች የሉትም::

የአብይ መንግስት ምን አልባት የኤርትራ መንግስትን ሙሉ ድጋፍ ካገኘ፣ ኤርትራ በጦርነቱ ሙሉ ለሙሉ ከተሳተፍች፣ ወታደራዊ ሚዛኑ በከባድ ሁኔታ ሊቀየር ስለሚችል   የበላይነቱን ሊይዝ ይችል ይሆናል:: ያንን ተከትሎ  ህወሃትን ከመቀሌ ማስወጣት ይቻል ይሆናል፡፡

ግን እርሱም ቢሆን ጊዚያዊ ድል እንጂ ዘለቄታዊ ሰላም አያመጣም፡፡ ከሁለት አመት በፊት የነበረውን መድገም ማለት ነው፡፡ ከሁለት አመት በፊት ወያኔ መቀሌን ብትለቅም፣ ከአንድ አመት በፊት መልስ መቀሌን ይዛለች፡፡

ማሸነፍ የማንችለውን ወይን አሸነፍን ብለን ዘላቂ ሰላም ማምጣት የማይቻለውን  ጦርነት፣  ደግሞ መዋጋት ትልቅ ስህተትና በዜጎች ለጋ ሕይወት ላይ መቆመር ነው !!!!!!!

ለአብይ አህመድና ለብልጽግና ስልጣን ማስቀጠያ፣  የህዝቡ ልጆች ፋኖዎች የሚያልቁበት ምንም ምክንያት የለም፡፡

ለህወሃቶች ደጋግሜ ተመሳሳይ ሃሳቦችን ነው ያቀረብኩት፡፡ ህወሃት የትግራይ ወጣትን ከማስጨረስ ውጭ ምንም አይነት ነገር በጦርነት ማሳካት አትችልም፡፡ የትግራይ ሕዝብ መከራ ለማስቆም፣ ከጀብደኝነትና ከጥጋብ ወጥተው በተለይም ከአማራውና ከአፋር ማህበረሰብ ጋር መነጋገር ያስፈልጋል ብለን ስንጎተጉታቸው ነበር፡፡ እንደጠየቅነው፣ በተወሰነ  መልኩ ሕወሃቶች በአዲስ አመት ትንሽም ቢሆን ልቦና ገዝተው ለድርድር መዘጋጀታቸው መግለጻቸው ጥሩ ነገር ነው፡፡

Filed in: Amharic