>

ህገ ወጥ ኬላ በማቋቋም..." በዘመነ ካሴ ላይ የቀረበ ውሀ የማይቋጥር ክስ...?!?  (ደሳለኝ ጫኔ)

ህገ ወጥ ኬላ በማቋቋም…” በዘመነ ካሴ ላይ የቀረበ ውሀ የማይቋጥር ክስ…?!?

ደሳለኝ ጫኔ

የአማራ ክልል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ዛሬ ጠዋት ለአማራ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በሰጡት መግለጫ የዘመነ ካሴ «ወንጀል» ተብሎ የተነገረው «ህገ ወጥ ኬላ በማቋቋም፣ የህዝብ እና የመንግስት እንቅስቃሴ ላይ ችግር ሲፈጥር ነበር» የሚል ነው። የተጠረጠረበት የወንጀል ምርመራም በአማራ ክልል እንደሚከናወን አሳውቀዋል።

ዘመነ ፋኖ ያሰለጥን የነበረው በአብዛኛው በጎጃም አካባቢ እንደሆነ ይታወቃል። እኔ ባለኝ መረጃ የትህነግ ወራሪ ሀይል ወደ አማራ ክልል በተስፋፋበት ጊዜ በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ፋኖዎች ሰርጎ ገቦችን ለመቆጣጠር ኬላዎችን አቋቁመው የነበር ቢሆንም በጎጃም አካባቢ ከጸጥታ መዋቅሩ ውጪ አንድም ቦታ በፋኖዎች የተቋቋመ የፍተሻ ኬላ አልነበረም። አለ ከተባለ ለመታረም ዝግጁ ነኝ።

ስለዚህ ዘመነ የተጠረጠረበት ኬላ የት እና መቼ ተቋቋመ? በሂደቱ ውስጥ የዘመነ ተሳትፎ ምንድን ነበር? በየትኛው አካባቢ የህዝብ እና የመንግስት እንቅስቃሴ ላይ ችግር ፈጠረ የሚሉትን ጭብጦች በመገምገም ብቻ ዘመነ የተጠረጠረበት ወንጀል ብዙ ውሃ የሚቋጥር ነገር አይመስልም።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በምክትል ኮሚሽነሩ በኩል ከገለፀው ከዚህ ጭብጥ የተለየ ነገር በሂደት ያመጣል ብየ አልጠብቅም። ዘመነም በዚህ ጉዳይ ክስ የሚመሰረትበት ከሆነ በቀላሉ ራሱን በፍርድ ቤት መከላከል እና ነፃ መውጣት ይችላልም ብየ ተስፋ አደርጋለሁ።

ፍራቻየ ዘመነ በጎጃም አካባቢ ፋኖ በስፋት በማሰልጠኑ፣ በወጣቶች ዘንድ ያለው ተወዳጅነት እና ተሰሚነት መጨመር፣ በገዢው መንግስት ላይ የሰላ ትችት በመሰዘንዘሩ እና አንዳንድ ካድሬዎች እና በፀጥታ መዋቅሩ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ለዘመነ ካላቸው የግል ጥላቻ እና «ለምን በአጃቢ ይንቀሳቀሳል» በሚል ምክንያት ታርጌት ተደርጓል የሚል ነው። ሁሉንም ወደፊት እናየዋለን። ጥሩው ነገር ወንድማችን እንደነ አስቻለው ደሴ፣ ዋዋ ጎቤ መልኬ፣ እና ሌሎች ወንድሞቻችን እንኳን አልተገደለ፣ እንኳንም አልሞተ ነው። መቼስ በቀን በሺዎቹ እየተጨፈጨፈ ላለ ህዝብ እስር ከጫጉላ ሽርሽር እና ከከተማ ግርግር ወጣ ወዳለ ስፍራ ለመዝናናት ወይም ለንባብ እንደሚደረግ ሽርሽር ለመቁጠር በቅተናል።

አሁን ከመሼ ዘመነን ለመጠየቅ ጓደኞቹ በታሰረበት 2ኛ ፓሊስ ጣቢያ ሂደው አግኝተው ምን እንደሚፈልግ ሲጠይቁት «የምፈልገው መጽሐፍ ብቻ ነው» ብሏቸዋል። ልብስ እና መጽሐፍ ገብቶለታል፣ ሰላም እንደሆነና በጥሩ መንፈስ እንደሆነ ተረድቻለሁ። የባህር ዳር እና አካባቢው ወጣቶች እንዲረጋጉም መልዕክት አድርሱልኝ ማለቱን ነግረውኛል።

ነገሩ ባሕር ዳር 9ኛ ፖሊስ ጣቢያ አብሮን ታስሮ የነበር አርሶአደር በቀረርቶው እንዳለው ነው፦

መታሰሩን ታሰር፣ ነገ ትፈታለህ፤

ወዳጅ እና ጠላት፣ ትለይበታለህ!

Filed in: Amharic