>

በጎውን እንምሰል!! (በአባ ያዕቆብ ሊቀ ጳጳስ ምሥራቃዊ ወመስአዊ)

በጎውን እንምሰል!!

ያ ጠቢብ ያሉት ሰው …. እጅግ ‘‘የተማረ’’፣

እጁን ባፉ ጫነ … ጆሮው ደነቆረ፣

‘‘ማር ነው’’  ሲባል ከርሞ … ከኮሶ መረረ፣

ሕሊናውን ሽጦ …. ለሆዱ አደረ፣

በማይጠቅም ስሌት መልካሙን ቀየረ፡፡

በክፋት ቋጠሮ – ጠፍቶ መላቅጡ፣

በቂም በጥላቻ – ወጥቶ ውጥንቅጡ፣

ያስተማሩት ድሆች …

የኳሉ የዳሩት – መደገፊያ  ሲያጡ፣

በቀንና ሌሊት – በችግር ሲቀጡ፣

በብሔር በጎሳ እንዲህ ሲናወጡ፣

እርሱ ግድ የለሽ ነው እያወቀ በውስጡ፡፡

ግና…!!

ለእግዜር የተገዙ … ሕሊናን ያልሸጡ፣

ከእርግማን የሸሹ … ከአዚም ያመለጡ፣

የጥበብን ውኃ … ለትውልድ ያጠጡ፣

በጥልቅ አሳቢነት  መልካምን ያመጡ፣

ጠቢባን፣ ምሁራንም አሉ ለእኛ የተሰጡ፡፡

በጸሎት በምልጃ  ለሕዝባቸው ተግተው ፣

ፍቅርን ተጎናጽፈው ሰላምን አንግበው፣

አሉ በየዋሻው የበግ ሌጦ ለብሰው፣

በገዳም በደብሩ … በከተማ፣ ጎጡ ፣

ብዙ ጀግኖች አሉ ለሀገር የተሰጡ፣

ብዙ ቅኖች አሉ ለሕዝብ የተሰጡ፡፡

‘‘ወዳጅ ሆይ፥ ነፍስህ እንደሚከናወን፥ በነገር ሁሉ እንዲከናወንልህና ጤና እንዲኖርህ እጸልያለሁ። ወንድሞች መጥተው አንተን  በእውነት እንደምትሄድ ስለ እውነትህ ሲመሰክሩ እጅግ ደስ ብሎኛልና፤ ልጆቼ በእውነት እንዲሄዱ ከመስማት ይልቅ የሚበልጥ ደስታ የለኝም፡፡’’

(፫ኛ የዮሐንስ መልእክት ቁጥር ፪-፬)

(በአባ ያዕቆብ ሊቀ ጳጳስ- ምሥራቃዊ ወመስአዊ)

(በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል)

Filed in: Amharic