>

"ከመካከላችን በእረብጣ ገንዘብ ያማለሏቸውን በውል እስክንለይ ጎጃምን ለቅቄ ለመሄድ ወስኜ ነበር....!!!"  (አርበኛ ዘመነ ካሴ)

“ከመካከላችን በእረብጣ ገንዘብ ያማለሏቸውን በውል እስክንለይ ጎጃምን ለቅቄ ለመሄድ ወስኜ ነበር….!!!” 

– አርበኛ ዘመነ ካሴ

መስከረም 21 ቀን 2015 ዓ.ም (አሻራ ሚዲያ) መንግስት እኔን መከታተል በጀመረ በ11 አመቱ ይዞ አሰረኝ። እለተ ማክሰኞ ተሳካላቸው። ውጥናቸው የሰመረው ባህርዳርን በረገጥኩ በሳምንቱ ነው። ወደ ውባ ባህርዳር የመጣሁት ከ120 ቀናት በሗላ ነበር። ከነበርኩበት ተነስቸ ባህርዳር ለመድረስ ከ13 ሰዓት በላይ በእግሬ ተጉዣለሁ። የተወሰኑ መንገዶችን በባዶ እጄ ጭምር።

ወደ ባህርዳር ጉዞ የጀመርኩት አንድ አላማ ለማሳከት ነበር። አንዲት ስንጥር ጉዳይ ከተሳካ ውስጤ ይዣለሁ። አላማየ ባህርዳርን እንደ መሻገሪያ ተጠቅሜ ጎጃምን ለቅቆ መሄድ መራቅ ነበር። ይሄንን ለመወሰን በቂ የሆኑ ምክንያቶች ነበሩኝ። ወደ በረሃ በሬጀ ባሳለፍኳቸው 4 ወራት ዘመነን ለመያዝ በሚል ወታደር ሲያሰማሩ አውቃለሁ። እኔን ለመያዝ በተፈጠሩ ግብግቦች ገበሬው በቅጡ አርሶ አልዘራም። የጎጃም ምድር ቀልብ እርቆት ነበር የከረመው። በተለይ የእኔ የትውልድ ስፍራ አክራሞቱ የሲዖል ነበር።

አቅሟ የደከመ መነኩሴ እናቴን ሳይቀር ደሳሳ ቤት በጥይት እየበሳሱ ሲሳለቁባት ነበር። በአጠቃላይ ለወገኔ እረፍት ለመስጠት ስል ጎጃምን ለቅቄ ለመሄድ ወሰንኩ። በጥይት፣ በሽማግሌ ሌላ ጊዜ ከዳተኛ በመፈለግ እጀን ለመያዝ ሞክረው አልተሳካለቸውም ነበር። እኔም የነበርኩበትን ቦታ መቀየር ግድ ሆነብኝ።

እናም ወደ ባህርዳር በስውር ገባሁ።

በአንድ በኩል እልቂቱ ይብቃ መደራደሪያ ነጥባችሁን ይሳችሁ ቅረቡ ጉዳዩ በሰላም ይፈታ የሚል ውትወታ ወጥሮ ይዞናል። ይህንን ለማድረግ በተለያዬ ቦታ ተበታትነን ያለን አመራሮች ትኩረት ከተደረገበት ቀጠና ወጥተን መክረን ውሳኔ የምናሳልፍበትን እድል መፍጠር የግድ አስፈላጊ ነበር።

በሌላ በኩል ከመካከላችን በረብጣ ገንዘብ ያማለሉትን በውል እስክንለይ ግንኙነታችን መገደብ፣ የቦታ ለውጡንም በሚስጥር ማድረግ ያስፈልግ ነበር።

በዚህ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ መሆን ከሃላፊነት ስሜት እንዳያጎድለን መጠንቀቅ አለብን። የከተማ ጦርነት እንዳንገጥም ማሰብም የእኛ ድርሻ ሆነ። መቼም ጦርነት አውድማ ላይ ታጥቆ የመጣ ጠላት ክንዴን እንዳልጨበጠው እነሱም፣ ህዝባችንም የሚያውቁት ሀቅ ነው።

እንደ ግለሰብ ለ11 አመታት ተረጋግቸ ኑሬ አላውቅም። ይሄ ቦታ ያመኛል፣ ምርመራ አድርጉልኝ ብዬ ታክሜ አላውቅም። በተለይ ላለፉት 4 ወራት የገጠመኝ የጤና ችግር በእጅጉ ፈትኖኛል። ህመምና ስቃይ ግን ከቆምኩበት አላማ በላይ አይደለም።

ባህርዳርና አካባቢው የእኛ መዋቅር ሳያውቅ ከተማዋን ተሻግሬ የቦታ ለውጥ ለማድረግ መወሰኔ እጅጉን ከባድ ነበር። ውሳኔዬ ግን ግብታዊ አልነበረም። ምንም እንኳን እኔ በክፉዎች እጅ ብወድቅም፣ መዋቅራችን አውቆ ቢሆን ባህርዳር ሊፈጠር የሚችለው ደም መፋሰስን በማስቀረቴ ደስታ እንጂ፣ ፀፀት አይሰማኝም። እዚህ ቦታ ተከብቢያለሁ ብል እንደ አቦ ሸማኔ ተወርውረው የሚደርሱ ተርቦች ነበሩ። በዝምታ በመያዜ ግን መዋቅሬ እንደሚያዝን አውቃለሁ።

ደም ማፋሰስን ለማስቀረት እጄን ስለሰጠው ግን ግዳይ እንደጣሉ በመቁጠር እጄን የፊጥኝ አስረው ካሜራ እየደገኑ ተሳለቁብኝ። በበኩሌ ጠብታ ደም ባለመፍሰሱ ደስተኛ ነኝ። በእረብጣ ገንዘብ በተገዛ ሆድ አደር መንገድ መሪ እየተመራ አልቻለኝም።

እኔ እጃቸው ላይ ስወድቅ ሁለት የእጅ ስልኮች፣ አንድ የፆለት መፅሐፍ፣ አንድ የፓወር ባንክ ወስደዋል። በተጨማሪም 10,700 ብር ገደማ እጀ ላይ ነበር። እኔ ካረፍኩበት ቤት ግን ለቤተክርስቲያን ማሰሪያ ከፅዋ ማህበር አባላት የተሰበሰበ ከ540,000 በላይ ብር  መሰበሰቢያ ሰብረው ወስደዋል።

(አርበኛ ዘመነ ካሴ – ከባህርዳር ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ “እጃቸው ላይ የወደቅኩባት እለት” በሚል ርዕስ ለፍትህ መፅሔት ከላከው ፁሑፍ የተወሰደ)

Filed in: Amharic