ፓስፖርት ማውጣት እና ከአገር ውጭ የሚሄዱ ተጓዦች
በተረኞች የሚያጋጥማቸው ፈተና
ከይኄይስ እውነቱ
ዘርፈ-ብዙና ፈርጀ-ብዙ የሆነው የአገራዊው ችግሮች ፍንካች በሚል በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ተሐዝቦቴን (observations) ሳካፍል ቆይቼአለሁ፡፡ ላለፉት 5 ዐሥርታት ባጠቃላይ፣ ለ32ቱ ዓመታት በተለይ፣ ኢትዮጵያን የያዛት ሕማም ሥርዓታዊና ሁለንተናዊ በመሆኑ መጠኑ ይለያይ እንጂ በሕማሙ ያልተነካ ወይም ጤነኛ የምንለው መንግሥታዊም ሆነ የግል ተቋም፣ የሃይማኖትም ሆነ የማኅበረሰብ ድርጅት፣ የማኅበረሰብ ክፍልም ሆነ ግለሰብ አለ ለማለት የማይቻልበት ደረጃ ደርሰናል፡፡
በርእሰ ጉዳዩ እንደተመለከተው በዛሬው አስተያየቴ ሁለት ጉዳዮችን ባጭሩ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡
1ኛ/ የጉዞ ሰነድ (ፓስፖርት) ስለማውጣት
ከእንግዚዝኛው ቋንቋ እንዳለ ወስደን ከምንጠቀምባቸው ቃላት መካከል ፓስፖርት የምንለው የጉዞ ሰነድ አንዱ ነው፡፡ ፓስፖርት ሥልጣን በተሰጠው የመንግሥት አካል የሚሰጥ፣ የያዡን ማንነትና ዜግነት የሚያረጋግጥ፣ በእርሱም ጥበቃ ሥር ከአገር ቤት ወደ ውጭ አገር፤ ከውጭ አገር ወደ አገር ቤት ለመጓጓዝ የሚያስችል ይፋዊ ሰነድ ነው፡፡ ከትርጕሙ ተነሥተን ሰነዱ ሁለት ገጽታዎች እንዳሉት እንረዳለን፡፡ አንደኛና በዋናነት፣ የጉዞ ሰነድ መሆኑ፤ ሁለተኛ፣ እንደ መታወቂያ ካርድ ማገልገሉ፡፡
ባገራችን ፓስፖርት ለመስጠት ሥልጣን የተሰጠው መንግሥታዊ ተቋም በየጊዜው የስም ተፋልሶ የገጠመው ቢሆንም አሁን ባለው አጠራር የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የሚባለው (Immigration and Citizenship Service/ICS) መ/ቤት ነው፡፡ ይህ መ/ቤት ባለፉት 32 ዓመታት የወንጀል ሥርዓቶች በሆኑት ዘረኞች እጅ ወድቆ የንቅዘት ማዕከል ከሆኑና ፓስፖርትን እንደ ልዩ መብት (privilege) እንዲታይ ያደረገ ተቋም ነው፡፡ ለነገሩ የመኖሪያ መታወቂያ ካርድስ የአገዛዙ ሰዎች በየወረዳው ባስቀመጧቸው ተረኞች አማካይነት ነዋሪው ተነፍጎት በዘረኝነት ለተረኞች የሚታደል ልዩ መብት አልተደረገም እንዴ? በመሠረቱ ፓስፖርት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በሕግ የተቀመጡ ግዴታዎችን እስካሟላ ድረስ በመብት ደረጃ አመልክቶ ሊሰጠው የሚገባና (ተጓዘም/አልተጓዘም) በተመጣጣኝ ዋጋ ሊያገኝ የሚገባው ሰነድ ነው፡፡
መ/ቤቱ አሠራሩን ለማዘመን በእጅ ከሚሠራ የሰነድ ማመልከቻ ወደ ኤሌክትሮኒክስ ኮምፒዩተር ማመልከቻ (online application) መሸጋገሩ ተገቢና መልካም ነው፡፡ ሆኖም ቅጹ እየተሞላ ባለበት ጊዜ ለምሳሌ የኤሌክትሪክ ኃይል ቢቋረጥ የተሞላውን ክፍል በመረጃ ቋቱ ውስጥ እንዲቆይ የሚያደርግ አማራጭ (saving option) የለውም፡፡ እንደገና እንደ አዲስ መጀመርን የግድ ይላል፡፡
በአገልግሎቱ መሠረታዊ ችግር ብዬ የማነሳው የቀጠሮው ርዝመት ነው፡፡ አዲስ ፓስፖርት ለሚያወጣ ሰው ቢያንስ 4 ወራት ይወስዳል፡፡ የማመልከቻው ሂደቱ አልቆ ፓስፖርቱን ለመውሰድ ደግሞ ቢያንስ 2 ወራት ይጠይቃል፡፡ በድምሩ አንድ ፓስፖርት ለማውጣት ከ6 ወራት በላይ መውሰዱ በየትኛውም መመዘኛ ሲታይ ትክክል አይደለም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የአመልካቹ ብዛት ወይስ የመ/ቤቱ አሠራር ቀልጣፋ አለመሆን ወይስ በቂ ኅትመት አለመኖር? ምክንያቱ የትኛውም ይሁን ተገቢውን ሥልጠና በመስጠትና (ለደኅንነት ክሊራንስ የሚደረግ ጥንቃቄ ካለ ይህንንም ጨምሮ) የአመልካቹን ብዛት ግምት ውስጥ ያስገባ ኅትመት እንዲኖር በማድረግ ሥራውን በክፍለ ከተማ ደረጃ ወይም ለአገልግሎቱ ተስማሚ ነው ተብሎ በሚታሰብ ተቋም አማካይነት በውክልና ማሠራት አይቻልም ወይ?
ሌላው የኦን ላይን አገልግሎቱ ጠቀሜታና አስፈላጊነት እንዳለ ሆኖ፣ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ወገኖቻችንን ጨምሮ በአገልግሎቱ ለመጠቀም የሚቸግራቸው ዜጎች ለዝርፊያ የተጋለጡ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ይኸውም ቅጹን የመሙላት አገልግሎት እንሰጣለን በሚሉ የጽሕፈት አገልግሎት በሚሰጡ የንግድ መደብሮች የተጋነነ ክፍያ እየተጠየቁና አማራጭ በማጣት እየከፈሉ መሆናቸው ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ባጠቃላይ ፓስፖርት ከጉዞ ሰነድነቱ ውጭ እንደ መታወቂያ የሚያገለግል ሰነድ በመሆኑ፣ አገልግሎቱን ዜጎች በተቀላጠፈና በተመጣጠነ ዋጋ ሊያገኙ እንደሚገባ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
2ኛ/ ወደ ውጭ አገር የሚጓዙ ዜጎች የሚገጠማቸው ፈተና
በአገዛዙ ተረኞች ወረራ ከተደረገባቸው፣ ከፍተኛ ዝርፊያ ከተፈጸመባቸው ፣ እጅግ የሠለጠነ የሰው ኃይል ከፈለሰባቸውና ብሔራዊ መለያችንና መኩሪያችን ከሆኑት ተቋማት አንዱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው፡፡ በኢትዮጵያችን የሠለጠኑት የወንጀል አገዛዞች ኢትዮጵያን የማጥፋት አንዱና ዋነኛ አካል አድርገው ከሠሩአቸው አገራዊ ጥፋቶች አንዱ አየር መንገዳችንን ማዳከምና የጥቂት ዘረኞች መፈንጫ ማድረጋቸው ነው፡፡ ታዲያ ቀስ በቀስ እያጠፉት ካለው ተቋም መልካም አገልግሎት መጠበቅ የዋህነት ይሆናል፡፡
በሕጋዊ መንገድ ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ አገር የሚጓዝ መንገደኛ ባዲሳባ ቦሌ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ማለፉ የማይቀር ነው፡፡ አንድ መንገደኛ ለበረራ የሚያስፈልጉትን ሕጋዊ ሰነዶች (የጸና የጉዞ ሰነድ፣ የጸና ቪዛ፣ የበረራ ቲኬት ወዘተ.) ሁሉ ካሟላ እና ዕቃዎችን ከያዘም በአየር መንገዱ ሕግ መሠረት ካስፈተሸ፣ በበረራው ዕለት በሰዓቱ በመገኘት ሰነዶቹን ለሚመለከተው የአየር መንገዱ ሠራተኛ ካሳየ ሌላ የሚጠበቅበት ግዴታ የለም፡፡ ባንፃሩም በወንጀል ሥርዓት ውስጥ የአገርና የሕዝብ ደኅንነትን ጉዳይ ሕግና ሥርዓትን ተከትለው የሚፈጽሙ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ስለመኖራቸው አጠያያቂነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በወንጀል ተጠርጥሮ እየሸሸ መሆኑ ወይም ለአገር ደኅንነት ሥጋት መሆኑ በማስረጃ ካልተረጋገጠ በቀር ከጉዞው ሊያስቀረው የሚችል አንዳች ምክንያት አይኖርም፡፡
አሁን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ በተለይም የጉምሩክ ባለሥልጣን መ/ቤትን ወክለው እየሠሩ ያሉ አብዛኞቹ ሠራተኞች በተግባር እየተፈጸመ ያለ አሳሳቢና አሳዛኝ ጉዳይ አለ፡፡ ይኸውም ወደ ዓረብ አገራት በሚሄዱ እኅቶቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለ በደል ነው፡፡ በእነዚህ እኅቶቻችን ላይ በባዕድ አገር ስለደረሰባቸውና ስለሚደርስባቸው ስቃይና እንግልት ያለስማ ወገን አለ ብዬ አላስብም፡፡ ብዙዎቹ ከገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል መጥተው ፓስፖርትና ቪዛ ከማግኘት ጀምሮ የሚደርስባቸው እንግልት ሳያንስ፣ ተበድረውና ወላጆቻቸው ያላቸውን ጥሪት ሙልጭ አድርገው እንደሚልኳቸው እየታወቀ፣ አየር መንገዱ ከሰባ ዓመታት በላይ የገነባውን መልካም ስምና ዝና በሚያጎድፉ፣ ከአገዛዙ ሥርዓት ጋር አብረው በሚያልፉ ተረኞች ምክንያት የማይጠገን ጉዳት እየደረሰ ይገኛል፡፡
ወደ ዓረብ አገራት ‹እንጀራ› ፍለጋ የሚሄዱ እኅቶቻችን ከፍ ብዬ እንደገለጽሁት ሕጋዊ ሰነዶችን ሁሉ አሟልተው እያለ በጠቀስኳቸውና ሰነዶችን የማረጋገጥ ሥልጣን ባልተሰጣቸው የጉምሩክ ‹ዘራፊዎች› አማካይነት ሰነዳችሁ ትክክል አይደለም ወይም አልተሟላም እየተባሉ ከፍተኛ ገንዘብ እየተጠየቁና እየተጉላሉ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ምስኪን እኅቶቻችን የውጩ መከራ ሳያንስ ለውስጥ ‹አውሬዎች› ተጋልጠው ይገኛሉ፡፡ እውን ጭራቅ (monster) ካልሆነ በቀር ከሰው የተፈጠረ ሰው የእነዚህ ምስኪን ወገኖቻችንን ደም እንዴት ይመጣል? ኧረ እባካችሁ ለነውራችሁ እንኳን ቅጥና መልክ አበጁለት፡፡ ይሄም የሚቀናበት ሆኖ ነው ወይስ እነዚህ ምስኪን እኅቶቻችን የመጡበት የኢትዮጵያ ክፍል አገዛዙና በጭራቅነት ያሠለጠናቸው ጉዶች ከሚጠሉት ማኅበረሰብ የተገኙ ይሆኑ? ተዉ!!! እነዚህ እኅቶቻችን የረጩት ደም እምባ ሰማየ ሰማያትን ሰንጥቆ እንደ ራሔል እምባ መንበረ ጸባዖት የሚደርስበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡