>

አቶ ስንታየሁ ቸኮልን “የእጅ ስልኩን እየመረመርኩ ስለሆነ ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ” የኦሮሞ ፖሊስ

መረጃ

“የእጅ ስልኩን እየመረመርኩ ስለሆነ ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ” የኦሮሞ ፖሊስ
ከአዲስ አበባው እስር ቤት ስታመጡኝ ስልክ አልነበረኝም፤ ኤግዚቢት አልያዛችሁም ፤ ከየት አምጥታችሁ ነው የምትመረምሩት?” አቶ ስንታየሁ ቸኮል
የስርዓቱ አስጨናቂ አቶ ስንታየሁ ቸኮል ዛሬ ረቡዕ መስከረም 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ቡረዩ ፍርድ ቤት ቀርቧል። መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረው መርማሪ የኦሮሞ ፖሊስ ‘አሉኝ’ ያላቸውን ማስረጃዎች ለችሎቱ እንዲያቀርብ ነበር። ሆኖም አንዳች ማስረጃ ሳያቀርብ የስንታየሁን የእጅ ስልክ እንደሚመረምር ገልፆ ለዚሁ ሥራ 14 የምርመራ ቀናት እንዲሰጠው ጠይቋል። አቶ ስንታየሁ ቸኮል በበኩሉ የኦሮሞ ፖሊስ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ሲረከበው እስር ቤት በመቆየቱ ምክንያት ስልክ እንዳልነበረው፤ ብሎም በኦሮሞ በፖሊስ በኤግዚቢትነት የተያዘ ስልክ እንደሌለው ተናግሯል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ለነገ መስከረም 27 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ምልከታ
የሁሉም የአገዛዙ ፖሊሶች በተለይም የኦሮሞ ፖሊስ ዋነኛ አላማ የኦሮሞን የወረራ አገዛዝ ማስቀጠል ነው። የሕብረተሰብ ጠባቂ ሳይሆን የአንድ ሰባራ ወንበር ዘብ ነው። የፖለቲካ እስረኞችን አሰሮ መጠበቅ እንጂ አንዳንድ ጊዜ ዶሴያቸው ምን እንደሆነ ሁሉ አያውቀውም። ለዚህ ነው ‘ስልኩን እየመረመርኩ ነው’ ያለው ፖሊስ ስንትሽ ከእስር ቤት ወደ እስር ቤት መወሰዱን የረሳው።
ነገ ደግሞ ‘ከአዲስ አበባው እስር ቤት ሲወጣ በኩርቱ ፌስታሉ የያዛቸውን መፅሐፍት፣ የቤት ውስጥ ጫማዎች እና አልባሳት እየሜረሜርኩ ኔው፤ ከደረት ኪሱ ያገኘሁትን ውዳሴ ማርያም እያጤናሁት ነው፤ ቤቀይ ቤቀይ የቴፃፈውን ለከፊቴኛ ሚርሜራ ወደ ፌዲሬል ኢንሳ ሜላክ አለቢኝ፤ አሁኒም 14 ቄን ይሴጤኝ።’ ሊል ይችላል። ማን ያውቃል። እዚህ ላይ አንድ ገጠመኝ ልጨምርበት፦
በርከት ያልን ሰዎች በአንድ መዝገብ ምርመራ ተከፍቶብን ቆይቶ ዋስትና ስለተፈቀደልን ከሁለት ወራት ገደማ እስር በኋላ ተፈታን። የብዙዎች የእጅ ስልክ ለምርመራ በሚል በአዲስ አበባ ፖሊስ እንደተወሰደባቸው ነው። የእኔ ለብቶፕ ኮምፒዩተር ደግሞ ቤቴ ሲበረበር እንደተሞነጨቀ ነው። በተፈታን አፍታ ንብረታችንን እንዲመልስልን አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ጠየቅን። “አሁን አይቻልም ሌላ ጊዜ ተመለሱ” ተባልን። በቀጠሮው መሰረት ተመለስን። አሁንም እንድንመለሰ ተነገረን። በሌላኛው ቀን ስንመለስ “ለምርመራ ኢንሳ እንደተላከ ነው። ተመለሱ” ተባልን። በሌላ ቀን ስንመለስ የምርመራ ክፍል ሓላፊው ለይስሙላ ስማችንን ወረቀት ላይ እያየ ከኢንሳ መመለስ ወይም አለመመለሱን ያረጋግጥልን ጀመር። ነገር ግን ዓይኑን ለይስሙላ ወደ ወረቀቱ ያዞራል እንጂ አያነበውም ነበር። ምክንያቱም  ንብረታችን እንደማይሰጠን ያውቀዋል። በዚህ መሀል “የአንተ ስልክ አልተመለሰም፣ የአንቺም ስልክ አልተመለሰም” እያለ ስማችንን ሲያደርስ “የጌጥዬስ?” አልኩት።  አሁንም ዓይኑን ወደ ወረቀቱ ዞር አድርጎ “የአንተም ስልክ አልተመለሰም” አለኝ። “የእኔ እኮ ስልክ ሳይሆን ላብቶፕ ነው” ስለው ደንገጥ ብሎ ወረቀቱን የምር ማንበብ ጀመረ። የኮምፒዩተሬን አይነት ከእነመለያ ቁጥሩ ነግሮ እርሱም እንዳልተመለሰ ሲገልፅልኝ፤ “እሺ የሱሪ ቀበቶየስ? እርሱም አይመለስም?” እንዳልኩት በጋዜጠኝነት የሚታወቅ አንድ ትግሬ የኦህዴድ-ብልፅግና ካድሬ ሰላምታ ነፍጎን ዘው ብሎ ገባ። ፖሊሱም ጆሮ ነፈገኝ። እኔም በክንፈ ዳኛው ላይ ዶኪዩመንተሪ ሊሠሩ ይሆናል እያልኩ ወጣሁ። ኮምፒዩተሬም እንደተወረሰ ነው።
ከሳምንታት በኋላ አባሪዎቼ ስልክ እየተደወለ “ኑ ንብረታችሁን ውሰዱ” እንደተባሉ፤ በዚህ ጥሪ እንዳልሄዱና በተከታታይ ጊዜያት ከያሉት እየታደኑ እንደገና እንደታሰሩ ሰማሁ። (ጌጥዬ ያለው)
Filed in: Amharic