>

የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ...! (ባላገሩ ቲቪ)

የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ…!

ባላገሩ ቲቪ

አቶ ፍቅሩ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ትናንት ሌሊት በ88 ዓመታቸው ሕይወታቸው ማለፉን ኢዜአ ከቤተሰቦቻቸው ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኝነት ታሪክ በዋናነት የሚነሱት ጋዜጠኛና ደራሲ ፍቅሩ ኪዳኔ የተወለዱት በ1927 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ነው።

አባታቸው የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ የነበሩ ሲሆን፣ የክለቡን ተጫዋቾች ከትምህርት ቤት ወደ ስታዲየም ይዞ በመሄድ ይታወሳሉ፡፡

በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ከአባታቸው ጋር የመሆን ዕድል የነበራቸው አቶ ፍቅሩ በኋላ የስፖርት አስተማሪ ሆነዋል።

በኢትዮጵያ ሬዲዮና የተለያዩ የአገር ውስጥ የሕትመት ውጤቶች ስለ አገር ውስጥ ስፖርት መዘገብ የጀመሩት አቶ ፍቅሩ በ1943 ዓ.ም በሱዳን እና ኢትዮጵያ መካከል የተደረገውን ጨዋታ በቀጥታ በሬዲዮ ማስተላለፍ የቻሉ የመጀመሪያው የስፖርት ጋዜጠኛ ናቸው።

አቶ ፍቅሩ የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር በ1961 ዓ.ም ሲመሰረት የመጀመሪያው ፕሬዝደንት የነበሩ ሲሆን በብስክሌት ፌዴሬሽን፣ቴኒስ ፌዴሬሽን እና በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ኮሚቴ በዋና ፀሐፊነት፣ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት በመሆን አገራቸውን አገልግለዋል፡፡

በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውስጥም በአመራርነት ፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የቀድሞ ፕሬዝደንት የነበሩት የኢሳ ሃያቱ አማካሪ ጭምር የነበሩ ፡፡

ከ1969 ዓ.ም ጀምሮ ኑሯቸውን በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ያደረጉት አቶ ፍቅሩ በሀገሪቷ ለሚገኘው ዕለታዊ የስፖርት ጋዜጣ ለኪፕ እና ሳምንታዊ የእግር ኳስ መጽሔት ፉትቦል ፍራንስ፣ ዶቼቬሌ (የጀርመን ድምፅ) እና ሌሎች የአለም አቀፍ ታዋቂ መገናኛ ብዙሃን መስራት ከመቻላቸው በተጨማሪ “የፒያሳ ልጅ” እና “የስፖርት ጨዋነት ምንጮች” የተሰኙ መጻሕፍት መጻፍ ችለዋል፡፡

ጋዜጠኛና ደራሲ ፍቅሩ ኪዳኔ አንድ ልጅ ያላቸው ሲሆን ሁለት የልጅ ልጆችንም አይተዋል።

Filed in: Amharic