>

በስልጣን ላይ ያልጠቀመ ሰው ያለ ስልጣን ጥቅም አለውን? (በሙሀመድ ሀሰን)

በስልጣን ላይ ያልጠቀመ ሰው ያለ ስልጣን ጥቅም አለውን?

በሙሀመድ ሀሰን

ወያኔ አባ ዱላ ገመዳን አሰልጥና የኦሮሞን ህዝብ እንዲያስተኛላት የቤት ስራ ሰታ ብትሾመውም ሰውዬው ውስጥ ለውስጥ ወያኔን የሚገዘግዝ ሀይል በኦፒዲኦ ዙሪያ በመሰብሰብ ከዶር አብይ፣ ኦቦ ለማ መገርሳ እንዲሁም ጃዋር መሀመድን ማፍራት እስከ ሀገር መምራት የሚችሉ ፖለቲከኞችን ማፍራት ችለዋል።

ወያኔ ኦቦ አባ ዱላን በወያኔ ጉዳይ አስፈፃሚነት ኦሮሚያ ላይ ተክለናል ብለው ሲያስቡ አባዱላ ገመዳ በመልሱ ወያኔ አንገት ላይ ገመድ እያጠለቁ ነበር። አላማቸውም ኦሮሚያን ከወያኔ ተፅእኖ ስር ነፃ ከማውጣት ባለፈ ሀገርን መምራት ላይ ያተኮረ ራእይ ሰንቀው በመነሳታቸው ዛሬ የአባ ዱላ ልጆች ሀገር ተረክበው እያስተዳደሩ ነው። በጎጠኝነት ተከፋፍለው ቢሆን ኖሮ ዛሬ የሀገር መሪነት ሚና አይኖራቸውም ነበር። እናም አንድ ኦሮሚያ የፖለቲካ ህልውናቸው መሰረት አደረጉት።

የሰው ልጅ እንደ ፋብሪካ ምርት አንድ አይነት ሊሆን አይችልም። በሰዎች መካከል የሀሳብ ልዩነቶች ይኖራሉ። ነገር ግን የሀሳብ ልዩነቶችን ማጥበቢያውና ማሰሪያው የትግል የመጨረሻው አላማ ነው። በተለይ የትግል አለማው የህዝብን አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ በደል አንስቶ የተጀመረ ከሆነ በሰዎች ወይም በግለሰቦች መካከል የሚነሱ ልዩነቶች ከትግሉ አላማ አንፃር ይገራሉ። ከህዝብ ትህል በላይ የሚሆን ግለሰብ አይኖርምና የሀሳብ ልዩነቱን ለሚታገልለት ህዝብ ሲል ወደማስታረቅ ይሄዳል። at the end of the day የትግሉ አለማ የህዝብን ፍላጎት መጠበቅና ህዝብን ነፃ ማውጣት እንጂ የግለሰብን የፖለቲካ ፍላጎት entertain ማድረግ አይደለምና።

የነ ቹቹ አለባቸው ብአዴንና ~ አዴፓ

ድሮ ብአዴኖች  ዛሬ አዴፓዎች በዚያ መልኩ የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚተነትኑና ቀድመው ሂሳብ የሚሰሩ አልነበሩም፣ አይደሉምም። የኢትዮጵያን የመጨረሻውን ኢፊሴላዊ የህዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት እስከነ ሙሉ ችግሩ ብንወስድ አንኳ የአማራ ህዝብ የኢትዮጵያን ፖለቲካ check and balance ማስጠበቅ የሚችል ውክልና ያለው ህዝብ ነበር።

ችግሩ ተወካዬቹ ይሄን የፖለቲካ ሀይል ባለመገንዘብ ለራሳቸውም ፖለቲካውን መጠቀም ሳይችሉበት በስራቸውም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ወሳኝ ሚና ያለው የአማራ ህዝብ ተወካይ ማፍራት ሳይችሉ የህዝብ ሰልጣን ላይ ያለ ምንም ጥቅም ተቀምተውበት አርጅተውበታል።

ኦሮሚያ ዶር አብይ፣ ኦቦ ለማ መገርሳን፣ጃዋር መሀመድን ሲያፈራ አማራ ክልል አቶ ደመቀ መኮንን ከተሰየሙበትና ከያዙት ቦታ አልተንቀሳቀሱም። አቶ ደመቀ ተተኪ የአማራ ፖለቲከኛ ማፍራት ይቅርና በድርጅታቸው ውስጥ በተወሰነ መልኩ ለአማራ ህዝብ የመቆርቆር አዝማሚያ ያላቸውን የሳቸው ዘመን ጓዶቻቸውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተጠቅሞ ሲወረውራቸው እነሱን ለማዳን የሚሆን ሀይል እንኳ መፍጠር አልቻሉም።

ወደ ቹቹ አለባቸው ስንመጣ በብአዴንነት ዘመናቸው ለህዝብ የሚሆን ስራ መስራታቸውን ሳናውቅ ብአዴንን ጥለው የወጡ ሰው ናቸው። ብአዴኖች ድሮ አዴፓዎች ዛሬ በመካከላቸው የሰው መቀያየር የሚፈጠረው ለአማራ ህዝብ በመታገል ዙሪያ በሚያነሷቸው የትግል ሀሳቦች ሳይሆን ከመካከላቸው ማን የበለጠ ለተቀማጩ መንግስት አገልጋይ መሆን ይችላል በሚለው ሀሳብ ብቻ ነው። ከብአዴን እስከ አዴፓ በተዘረጋው የፖለቲካ ዘመን አንድ ሁነኛ ነፍስ ያለው ፖለቲከኛ አማራ ክልል ውስጥ መብቀል አልቻለም። ይህ የሆነው የአማራ ክልል ለብቻው ተለይቶ a mythological myths or  curse ስላለበት አይደለም።

ነገር ግን አዳዲስ የፖለቲካ አመራርን ማብቀል የግድ የነበረበት የብአዴን/አዴፓ ቤት የአማራ ልጆችን የሚበላ ሾተላይ ስለሆነ ነው። አቶ ቹቹ ከብአዴን ቤት ወተው የተለየ ሀሳብ ይኖራቸው ይሆናል ተብሎ ቢጠበቅም የፖለቲካ ትንታኒያቸው ጥግ በተለይ ከሰሞኑ ጎጃምና ጎንደር የሚል የጎጥ ልክፍት ውስጥ ተዘፍቀው ታይተዋል።

የአማራ ክልል ፖለቲከኞች ወደ ውጭ ትልቁን ስእል ተመልክተው በሀገር ደረጃ ተገዳዳሪ የፖለቲካ ሀይል እንዲሆኑ ለዘመናት ቢነገራቸውም፣ ቢለመኑም፣ ቢጠበቁም ከዚያ ይልቅ የቀለላቸው የራሳቸውን ህዝብ መዝለፍ፣ የራሰቸውን ወንድሞች ማሳደድ፣ ማስገደልና ማሳሰር እንዲሁም ለሀገር ሲመኛቸው መንድርና ጎጥ ውስጥ ሲልከሰከሱ የሚገኙ ሰዎች ሆነዋል።

ኦሮሚያ ወስጥ በዶር አብይና በኦቦ ለማ መገርሳ መካከል ወይም በጃዋር መሀመድና በፀጋዬ አራርሳ መካከል ያለው ልዩነት ስለ ኦሮሚያ ኦሮሚያ ክልል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በተገቢው ፍጥነትና በተገቢው መጠን አለመፈፀማቸው ነው። ወደ ማህበራዊ ሚዲያ አክቲቪስቶቻቸውም ስንሄድ ወለጋ፣ባሌ፣አርሲ፣ጅማ፣ ምእራብ ሸዋ እየተባባለ ሲራኮት አናይም።

አማራ ክልል ስንመጣ የአማራ ክልልና ህዝብ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ስላለው ሚና መከራከር ሲገባ የኛ ፖለቲከኞች ጭራሽ ህዝባችን አንድ እንዳይሆን በጎጠኝነት ማናከስን የ political intelligence መለኪያቸው አድርገው ህዝባችን አናት ላይ ቤታቸውን ሰርተው ቁጭ ብለዋል። የሰሞኑ የቹቹ አለባቸው ነገርም ይሄው ነው።

የአማራ ክልል የማህበራዊ ሚዲያ አክቲቪስቱም የሚበዛው የአዴፓ ~ ወ ~ ብልፅግና ተከፋይና ተደጋፊ ነውና መሰረታዊ የፖለቲካ ጥያቄዎች ዙሪያ ሀሳብን ከማንሸራሸር ይልቅ የወያኔን ወረራ ለመታገል የጦር ሜዳ ላይ ያሉ ፋኖዎችን በስም ከፍሎ ለማባለት መሞከር፣ የጎጥ ፖለቲካን በመነካካት የህዝባችንን አንድነት መሸርሸር ላይ expertise ሆነዋል።

ነገር ግን ያልገባቸው ነገር አሁን በተለይ በዚህ አራት አመት ውስጥ ይህ የበሰበሰ የፖለቲካ መንገድ ያንገሸገሸው አዲስ ትውልድ ወደፊት መቷል። የዚህን ትውልድ የፖለቲካና አስተዳደራዊ ጥያቄዎች ከመመለስና በአማራ ክልል ፖለቲካ ውስጥ ተሳታፊነቱን ከማሳደግ ውጭ ሌላ አማራጭ የለም። ነገር ግን ይሄን awakened የሆነ አዲሱን ሀይል በጎጥ ፖለቲካ፣በአማች ፖለቲካ፣ በአበልጅ ፖለቲካ አስተኝተን ለተቀማጩ መንግስት አስገብረን እንኖራለን ከሆነ አላማችሁ ያ አይሳካም።

አባ ዱላ ገመዳን መሆን ባትችሉ ይህ አዱሱ ትውልድ ሀሳቡን ይገልፅ ዘንድ ፣ ድምፁን ትሰሙ ዘንድ የግድ ይላችኋል።

Filed in: Amharic