ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤተ-መንግስት ግምባታ ማስፋፊያ ሲባል በርካታ የደሃ ቤቶች ሊፈርሱ ነው…!
ባልደራስ
በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 10 ጨለለቆ፣ ዳንሴ እና ንብ-እርባታ በመባል የሚጠሩ አካባቢዎች ላይ የሚኖሩ ነዋሪዎች “ቤታችን ሊፈርስ ነው” ሲሉ መረጃ አድርሰውናል፡፡ ከትናት በስቲያ በ15/02/2015 ዓ.ም በሦስት ቀናት ጊዜ ውስጥ የሚኖሩበትን ቤት እንዲያፈርሱ በወረዳው የግንባታ ኃላፊ በኩል ትዕዛዝ ደርሷቸዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ግን ከዚህ ቀደም ቅያሪ ቦታና ቤት መስሪያ እንደሚሰጠን ተነግሮናል፡፡ እንዴት እነዚህ ነገሮች ሳይሟሉ አፍርሱ እንባላለን በማለት ጠይቀዋል፡፡ የወረዳው የግንባታ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ባለስልጣን ግን “እኔ እሱን አላውቅም ዝም ብላችሁ አፍርሱ፡፡ ያለበለዚያ በግሬደር እናፈርሳለን” እንዳሏቸው ተነሱ የተባሉ ነዋሪዎች ገልፀዋል፡፡ ይህን ትዕዛዝ ካስተላለፉ በኋላ የወረዳው የግንባታ ኃላፊ አጅበዋቸው ከመጡ ፖሊሶች ጋር ተመልሰው ሄደዋል፡፡
ይህ ጉዳይ ያሳሰባቸው ነዋሪዎቹ ወደ ወረዳው ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሲሄዱ የቢሮው ኃላፊ “ይፈርሳል ከተባለ ይፈርሳል፤ ምን ታመጣላችሁ” ብለው እንደመለሱላቸው ነዋሪዎቹ በከፍተኛ ሀዘን ገልፀዋል፡፡
ነዋሪዎቹ ትላንት ጉዳዩን ይዘው ወደ ክፍለ ከተማ የሄዱ ሲሆን፤ የክፍለ ከተማው ሰዎች ለዛሬ ቦታው ላይ በመገኘት ቅሬታቸውን እንደሚሰሙ ነግረዋቸው ነበር፡፡ ሆኖም ዛሬ ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡ ነዋሪዎቹ በድጋሜ ወደ ክፍለ ከተማ ቢሄዱም የሚያነጋግራቸው ሰው አላገኙም፡፡
ዛሬ 17/02/2015 ዓ.ም ከ8፡00 ሰዓት ጀምሮ ፖሊሶች በሁለት የወረዳ መኪኖች ተጭነው በቦታው ላይ ተበትነዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ነዋሪዎቹ ዛሬ ለሊት ቤታችን ሊፈርስ ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሮባቸዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ቅያሪ ቦታና ቤት መስሪያ ገንዘብ ሳይሰጣቸው ቤታቸው እንዲፈርስ መደረጉ አግባብ ስላልሆነ ቤተ-መንግስቱን የሚያስገነቡት ጠ/ሚ/ር አብይ የሚገነቡት ቤተ-መንግስት በእምባ የራሰ መሬት ላይ መሆኑን እንዲያውቁት ያስፈልጋል። ለህዝብ እሮሮ ትኩረት በመስጠት በበላይነት የሚቆጣጠሩት የአዲስ አበባ መስተዳደር ከጀመረው ህገ ወጥ እርምጃ እንዲታቀብ ይገባል፡፡