>

የሮሙ ወታደር አበበ ቢቂላ...! (ሽመልስ ወንድሙ)

የሮሙ ወታደር አበበ ቢቂላ…!

ሽመልስ ወንድሙ


ሮማ ላይ ለሚደረግ የማራቶን ውድድር ሐገሩን ወክሎ በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ አበበ ቢቂላ ተመረጠ። ውድድሩ አንድ ወር ሲቀረው እዚያው ሮማ ከተማ ውስጥ ስልጠናውን እያደረገ የሩጫውን መንገድ በጥንቃቄ አጠና። ልምምዱ በባዶ እግርም በጫማም ነበር። አበበም በጥናቱ በጫማ ሲሮጥ በአምስትና በስድስት እርምጃዎች እንደሚዘገይ ደረሰበት። እናም የማራቶኑ ጌታ ውድድሩን በባዶ እግሩ ለመሮጥ ወሰነ። ሁለቱም ከውሳኔውም በኋላ ከሌላኛው ኢትዮጵያን ወካይ ተወዳዳሪ ጋር በመሆን ውስጥ እግራቸው እንዲጠነክር ኦሊምፒክ መንደሩ ውስጥ ሁሉ በባዶ እግራቸው መሔድ ጀመሩ።

የውድድሩም ቀን ደረሰና ሩጫው ተጀመረ። ፍጥነቱ ከፍተኛ በመሆኑ በተወዳዳሪዎች ይታጀብ የነበረው አበበ ይመራቸው ጀመር። ቀስ በቀስም የምሬቱ ርቀቱ እየሰፋ ሔደና የሚመራቸው ተወዳዳሪዎች ኮቴ ከጆሮው ራቁ። በመጨረሻም ቀድሞ በሰርጌይ ፖፖቭ ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረ ወሰን 2:15:17.0 በማሻሻል 2:15:16.2 በመግባት የዓለም ክብረወሰኑን በማሸነፍ ውድድሩን አጠናቀቀ። አበበ ያመጣው በረከት ከሐገሩም አልፎ ለአህጉሩ አፍሪካ የተትረፈረፈ ሆነና በኦሎምፒክ ውድድር አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ የወሰደ ጥቁር አፍሪካዊ ነውና ለብዙ ጥቁር አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ ውድድር እንዲሳተፉ በር ከፍቷል። ይህንን ያየ የዓለም ሕዝብ ስለአበበ አውርቶ አልጠግብ አለ። ጋዜጦች ስለአበበ ለመጻፍ ብራናቸውን ወጠሩ ፤ ብዕራቸውን ዘቀዘቁ። በነጋታው የጣሊያን ጋዜጦችም <<ኢትዮጵያን ለመውረር የጣሊያን ሐገር ወታደር ሁሉ አስፈልጎ ነበር። ኢትዮጵያ ግን አንድ ወታደር ብቻ ልካ ድፍን ሮምን ወረረችው>> የሚል ጽሑፍ ይዘው ወጡ። የአበበ ቢቂላ ዝናም ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ ተዳረሰ።

በዚህ ብቻ አላበቃም። አበበ ከሮሙ ድል አራት ዓመት በኋላ ድሉን በቶኪዮ ደገመው። ድሉን የደገመው የኦሎምፒክን ብቻ ሳይሆን የዓለምንም ክብረ ወሰን በመስበር ነው። በዚህም ምክንያት ከእርሱ በፊት ማንም ያልፈጸመውን ፣ ከእርሱም በኋላ ለ16 ዓመታት ማንም ያላደረገውን የኦሊምፒክ ማራቶን ሁለት ጊዜ አከታትሎ የመውሰድ ገድልንም ፈጸመ። ይህንን የአበበን ድል ቀረጣጥፎ መብላት የተመለከቱት በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊና የልዑካኑ መሪ የነበሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ

‹‹እንደ በረዶ ነጫጭ ጥርስ አብቅሎ

ይቆረጣጥማል ሰዓት እንደቆሎ››           ብለው ተቀኙለት።

የሐገሬ ሕዝብ ጀግናን መቀበል ያውቅበታልና አበበ ቢቂላ ኹለተኛውን ወርቅ ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሰ የአዲስ አበባ ሕዝብ ተገልብጦ ወጥቶ የጀግና አቀባበል አደረገለት። ንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለ ሥላሴምየ ሻምበልነት ማዕረግን ሸለሙት። አዲስ ቮልስ ዋገን ቢትል መኪናም ደረቡለት።

ሻምበል አበበ ቢቂላ በ ፲፱፻፷፩ ዓ.ም በሽልማት የተሰጠውን ቮልስ ዋገን መኪና በአዲስ አበባ ውስጥ ሲነዳ አደጋ ደርሶበት ከወገቡ በታች መንቀሳቀስ አልቻለም ። የሮማውን ወታደር ለማዳን  ንጉሠ ነገሥቱ ለሕክምና ወደ እንግሊዝ አገር ልከውት በታወቀው የስቶክ ማንደቪል ሆስፒታል (Stoke Mandeville) ሲረዳ ቢቆይም ጥረቱ ሳይሳካ ቀርቶ ወደሚወዳት ሐገሩ ኢትዮጵያ በተንቀሳቃሽ ወንበር(Wheel chair) ተመለስ። አዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የሮሙን ወታደር ፣ የማራቶኑን ጌታ ቤተሰቡ፣ ወዳጆቹ ፣ ደጋፊዎቹ እንዲሁም በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በየመንገዱ ዳር ተሰልፈው እያጀቡ በጀግና አቀባበል ተቀበሉት።

ከተወዳደረባቸው አሥራ አምስት የማራቶን ውድድሮች አሥራ ኹለቱን በአንደኛነት የጨረሰው <<ሮማን የወረረው ብቸኛው ወታደር>> ኢትዮጵያዊው ጀግና አበበ ቢቂላ የእድሜ ዘመን መቋጫው ደርሶ በተወለደ በ፵፩ ዓመቱ ጥቅምት ፲፭ ቀን ፲፱፻፷፮ ዓ/ም የሕይወት ትግሉን ጨርሶ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለ ሥላሴ ፣ ዘመዶቹ ፣ ወዳጆቹ እና ከ፸፭ ሺህ በላይ የሚሆን ሕዝብ ተሰብስቦ እየተላቀሰ የመጨረሻ ስንብት አድርገውለት በቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን የቀብር ሥነ ስርዓቱ ተፈጽሟል። ዕለቱም በመላ ኢትዮጵያ የሐዘን ቀን ሆኖ እንዲውል ተደርጓል።

ነፍስ ኄር!

ጥቅምት ፲፮/፲፭ ዓ.ም

Filed in: Amharic