>

"አሳሪዎቹ ሆይ መጦሪያዋን ለነጠቃችኋት እርጅናዋን በመከራ ለለወጣቹሁባት እናታችን ምን ብዬ ልንገራት...!?" ( ታሪኩ ደሳለኝ)

“አሳሪዎቹ ሆይ መጦሪያዋን ለነጠቃችኋት እርጅናዋን በመከራ ለለወጣቹሁባት እናታችን ምን ብዬ ልንገራት…!?”

ታሪኩ ደሳለኝ


ዛሬ ከስምንት አመት በኋላም ጋዜጠኛው የእናቴ ልጅ ካለፈውም በከፋ ሁኔታ (ዋስትና በማያስከለክል ክስ፣ ዋስትና ከመከልከሉ አኳያ) ከስምንት አመት በፊት በዛሬዋ ቀን ባደረበት የቅሊንጦ እስር ቤት ያድር ዘንድ ተገድዷልና፤ ጠይቄው በመጣው ቁጥር “ልጄ እንዴት ነው?”   የምትለኝን እናቴ ለማጽናናት አቅምም ቃላትም አጥሮኛል።

እናቴ ሆይ አብዝተሽ የምትወጂው የየካው ሚካኤል ልጅሽ ነፃ እስኪሆን እርሱ ያበርታሽ።

አሁን እማወራው ስለ ብርቱው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ሳይሆን ስለ ሆደ ባሻዋና ሩሩዋ እናታችን ነው!!

ከእንቅልፌ ስነሳ ከንጋቱ 12 ሰዓት አልሞላም 70 ዓመት ያለፋት እናታችን የተመስገንን ነገር አሳለፋ ለሰጠችው ቅዱስ ሚካኤል የልጄን ነገር አደራ ልትል ሄዳለች፡፡

እናታችን ተመስገን ከታሰረበት ቀን ጅምሮ በብዙ እጥፍ አርጅታለች ነገሮቿ ሁሉ እህህ ነው መተኛት አቁማለች ሸለብ አደርጓት በነቃች ቁጥር አይ ልጄ እንዴት ሆኖ ይሆን ትላላች እንባ ባቀረዘዙ  አይኖቿ እራስጌዋ ላይ የተሰቀሉትን የመዳኒዓለም እና የቅዱስ ሚካኤልን ምስል እየተመለከትች ልጄስ ማለት ከጀመረች ዛሬ 14 ቀኖ ነው፡፡

አሁን ከንጋቱ 12፡45 ሆኗል:: እናቴ መጥታለች:: ነጠላዋን ሳታወልቅ  ማታ ሳትተኛ ለተመስገን የሚሄድን ስንቅ የሰራችውን ለማሞቅ እየቀነሰች  በመሀል  ተመሰገን፣ አብዮት .. አንተ ትንሽ ልጅ  አለች እናታችን አንዳችንን ለመጥራት የሁላችንም ስም መጥራት ልምዷ ነው:: “መብራት የለም መስልኝ እስቶቩ እንቢ አለኝ” አለችኝ፡፡ ቀና ስል መብራት አለ ተነስቼ ሄድኩኝ እስቶቩን አልሰካቸውም ሰሞኑን ከቀልቧ ስላልሆነች አንደዚህ  አይነት ነገር እየተደጋገመ ነው፡፡  ከምግቡ ጋር ለተመሰገን የሚሄድ ቡና ለማፍላት ጀበናዋን አንደኛው ምድጃ ላይ እየጣደች ነው:: ሁኔታዋ አሳዘነችኝ..

መሄድ ያለበትን ነገሮች ካስተካካለች በኋላ “ነገ ምን እንደሚፈልግ ጠይቁት” አአለችኝ እሺ በማለት ራሴን ነቀነኩ:: ነጠላዋን እያስተካከለች “ዛሬ እስጢፋኖስ ይነግሳሉ መኪና ስለማላገኝ አሁን ነው እምሄደው የሱን ነገር እንዳወክ ንግረኝ እዛው ሆኜ እጠብቃለሁ” አለችኝ

አሰብኩት ከጀሞ እስከ አብዮት አደባባይ ድረስ እንዴት እንደምትሄድ “አብሬሽ ልሄድ” አልኳት “አይሆንም አንተ እሱ ጋር ሂድና እሚሉትን ትነገረኛለህ” ብለኝ ለመውጣት ስትዘጋጅ እሺ እነደማትለኝ ባውቅም በማግባባት “ቀጠሮው እኮ ገና ከሰዓት ነው ታቦት አውጥተሽ ቤት ብተመለሺ ጥሩ ነው ምሳ በልተሽ አረፍ ትያለሽ” አልኩኝ  “የሱን ነገር ሳልሰማ ጎሮሮዬም እሺ አይለኝም” ብላ አየችኝ:: እምመልሳው ሳላልነበረኝ አንገቴን ደፋው፡፡

“ቅዱስ ሚካኤል ይከተልህ በልልኝ” አለችኝ እንዳቀረቀርኩ የድምጿን መለወጥ ስሰማ ቀና ብዬ አየኋት እናቴ እያለቀሰች ነው! ምን ላድርጋት ምንስ ብላት ትፅናናለች እንባዬ መጣ አንዳታየኝ ፊቴን አዙሬ “እነግረዋለሁ” አልከኝ:: እናቴ ስትሄድ ይሰማኛል ሁል ጊዜ ቤተክርስቲያን ስትሄድ እምታስረው ነጭ ሻሽ ወንበር ላይ ተቀምጧል ሻሽ አለማሰሯን ልብ አለማለቴ ገርሞኝ ሻሹን ይዤ ስወጣ ለሀዘን ጊዜ ብቻ ካልሆነ የማታስረውን ጥቁር ሻሽ  አስራ አንግቷን ደፍታ ስብር ብላ እየሄደች ሳያት አይኔ ዳር ደርሶ የነበረው አንባዬ ወረደ፡፡

አሁን ከቀኑ 9፡05 ነው ተመስገን ላይ አንባገነኖቹ የ3 አመት የግፍ ከፈረዱበት 5 ደቂቃ አልፏል:: ለናቴ ምን ብዬ ነው እምነግራት ከጠዋት ጀምሮ ቤተክርስቲያን  ተቀምጣ እየጠበቀችኝ ነው ምግብ ከበላች አንድ ቀን አልፏታል ፡፡

አውቃለሁ ተሜ ከቤተሰቡ በላይ ሀገሩን እንደሚያስቀድም! አውቃለሁ ተሜ ብርቱ እንደሆነ!

አውቃለሁ ተሜ ጉዞው ቀራኒዬ ድረስ አንደ ሆነ! አውቃለሁ ተሜ ድምፅ ለተነፈጉ ሰዎች ድምፅ እነደሆነ! አውቃለሁ ተሜ የዚህ ትውልድ ወካይ እንደሆነ!፡፡

ታዲያ በስተርጅና ላይ ለምትገኘው እናታችን  ይሄን አንዴት ነው የማስረዳት እናታቸን ልጄ ይመጣል እያለች በተስፋ እየጠበቀች ነው…..

አሳሪዎቹ ሆይ መጦሪያዋን ለነጠቃቹኃት እርጅናዋን በመከራ ለለወጣቹሁባት ተስፋዋን ላጨለመቹሁባት እናታችን ምን ብዬ አንደምንግራት ትነግሩኛላችሁ!?

አንቺም አባታችንም አለመዋሸትን ለእውነት መቆምን ላመነበት ነገር አለማፈግፈግን አስተምራቹ አሳደጋቹሁት:: እሱም ለአላማው ጎዞዬን ከሞቴ ውጭ የሚያቆመው የለም ብሎ ሁሉንም ሊቀበል ከፊት የተገኘው::

ምስኪኗ እናታችን ሆይ አሁን እስጢፎኖስ ነሽ:: እስጤፎኖስ ለእምነቱ ሲል በድንጋይ ተወግሮ መሰዋትነትን ተቀብሎ ሰመአት ሆኖል:: ልጅሽም ተመሰገን ለሚወዳት ሀገሩ ሲል ብቻ መክፈል ያለበትን እየከፈለ በመሰዋት መንገድ ላይ ነው::

አሁን አንባገነኖቹ ልጅሽ ላይ የግፍ የ3 አመት እስር ፈርደውበታል እናታችን ሆይ በርቺልን … አሁን ይሄን ልነግርሽ እየመጣሁ ነውና . . .

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከስምንት አመት በፊት  በግፍ ተፈረዶበት ወደ ማጎሪያቸው በወረወሩት ወቅት የፃፍኩት…

Filed in: Amharic