>

ባለ ወርቅ ብዕሩ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ  አረፈ...!

ባለ ወርቅ ብዕሩ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ  አረፈ…!

          ጴጥሮስ አሸናፊ

በ1980ዎቹ በነጻው ፕሬስ ይታተሙ ከነበሩት ጋዜጦች የፊያሜታ ጋዜጣ መሥራችና ዋና አዘጋጅ፣ ከኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞች ማኅበር መሥራቾች አንዱና የረዥም ጊዜ የማኅበሩ አመራር ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ሐዋሳ በተዘረጉ የመንግሥት የአፈና ወኅኒ ቤቶች ግፍ ቀማሽ፣  ከመጀመሪያዎቹ የነጻው ፕሬስ የግፍ እስረኞች አንዱ፣ ከሀገሩ ተሰዶ ከወጣ በኋላም ቀዳሚ ከሆኑት ድረ ገጾች የኢትዮ ሚዲያ ፎረም ( Ethio Media From EMF) ዋና አዘጋጅ፣ ከ20 ዓመታት በላይ ከኖረባት አትላንታ የሚተላለፈው አድማስ ራዲዮ ተባባሪ አዘጋጅ የነበረው፣ ታሪክ አዋቂው ታሪክ ተራኪው፣ በተለይ በልዩ የአጻጻፍ ዘየው የሚታወቀው ባለ ወርቅ ብዕሩ ተወዳጁ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ በትናንትናው ዕለት በተወለደባት አዲስ አበባ ሕይወቱ አልፏል።

ዳዊት ከአሜሪካ ወደ አዲስ አበባ የገባው  ከአምስት ቀናት በፊት ባሳለፍነው አርብ ሲሆን፤ ከኹለት ቀናት በፊት በማኅበራዊ ሚዲያው አዲስ አበባን እንዴት እንዳገኛት እያጋራን ነበር ። ከሦስት ቀናት በኋላ ወደ ማተሚያ ቤት የምትገባውን አዲሱ መጽሐፉን አርትዖት ለማጠናቀቅ ደፋ ቀና በሚልበት ወቅት ይህን ለማመመን የሚከብድ አስደንጋጭ መርዶን መስማት በጣም ከባድ ነው።

ዳዊት በነጻ ሚዲያው አፈና ምክንያት ከሀገራቸው ተሰደው በመላው ዓለም ተበትነው ይኖሩ የነበሩትን ቁጥራቸው ከ 70 በላይ የሚሆኑ ጋዜጠኞችን በማስተባበርና የተቸገሩትን በመደገፍ ስሙን በወርቅ ያጻፈ ሙያተኛና የሙያው ጠበቃም እንደነበር በተለይ በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገራትም ያሉ የሙያው አጋሮቹ የሆኑት ጋዜጠኞች የሚመሰክሩለት ታላቅ ኢትዮጵያዊ ነበር።

ዳዊት ለረዥም ዓመታት በኖረባት ልጆች ወልዶ ለቁም ነገር ባደረሰባት የሰሜን አሜሪካዋ አትላንታ በትንሽ በትልቁ የተወደደ፣ በማኅበራዊ ሕይወቱ ከኹሉ ጋር ተግባቢ፣ ጨዋታ አዋቂ፣ እንግዳ ተቀባይ፣ በኅዘንና በችግር ጊዜ ቀድሞ ደራሽ፣ በኪነ ጥበባዊ፣ ሀገራዊና ስፖርታዊ ክንውኖች ፊት አውራሪ ነበር።

ለእናቱ፣ ለባለቤቱ፣ ለልጆቹ፣ ለመላው ቤተሰቦቹ፣ ለሙያ አጋሮቹ፣ ለጓደኞቹና ለወዳጆቹ በሙሉ መጽናናትን ያድልልን።

ዴቭ  ወንድሜ ነፍስ ይማር  ‼

Filed in: Amharic