>

በድርድሩ የአሜሩካ ጣልቃ ገብነት፣ ዛቻና ማስጠንቀቂያ ትልቅ ሚና እንደነበረው ተገለጸ...! (ኢትዮ 360) 

በድርድሩ የአሜሩካ ጣልቃ ገብነት፣ ዛቻና ማስጠንቀቂያ ትልቅ ሚና እንደነበረው ተገለጸ…!

ኢትዮ 360 


በህውሃት እና ብልጽግና መካከል የተካሄደው ድርድር ያለ ስምምነት ለመቋረጥ ጫፍ ደርሶ እንደነበርና አሜሪካ ባቀረበቻቸው የማስጠንቀቂያ ነጥቦች ድርድሩ እንዲቀጥል መደረጉን የኢትዮ 360 የዲፕሎማቲክ ምንጮች አስታወቁ ።

 

በህውሃት እና ብልጽግና መካከል በደቡብ አፍሪካ የተካሄደው ድርድር በመጀመሪያው ዙር ሰኞ ያለ ስምምነት ተቋርጦ እንደነበርና አሜሪካ አቅርባው በነበረ የማስጠንቀቂያ ነጥቦች ድርድሩ እንዲቀጥል እና ስምምነት ላይ እንዲደረስ መደረጉን የኢትዮ 360 የዲፕሎማቲክ ምንጮች የሚናገሩት።

ሰኞ ላይ ያለስምምነት ሊበተኑ ሲሉ የአሜሪካው ወኪል ማይክ ሐመር አንድ መረጃ ይፋ አደረጉ ይላሉ ምንጮቹ ። ማይክ ሐመር ” ድርድሩ ያለስምምነት የሚበተን ከሆነ የአሜሪካ መንግስት አቋምን ይፋ እንዳደርግ በተሰጠኝ ሃላፊነት መሰረት በዝርዝር አቀርባለሁ” በሚል ነጥቦቹን ይፋ ማድረጋቸውን አስቀምጠዋል።

በዚህ መሰረትም አሜሪካ በመጀመሪያ ያቀረበችው የማስፈራሪያ ነጥብ በአለም አቀፍ አየር ትራንስፖርት ማህበር (IATA) እና የአለም አቀፍ ሲቪል አቬሽን ኦርጋናይዜሽን (ICAO) ያላትን ተጽእኖ ተጠቅማ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በየትኛው የአለም ክፍል እንዳይበር እገዳ እንዲጣልበት ታደርጋለች የሚል እንደሆነ የዲፕሎማቲክ ምንጮቹ ገልጸዋል ።

አሜሪካ በሁለተኛ ደረጃ ያቀረበችው ማስፈራሪያ በኢትዮጵያ ያሉ ባንኮች በኒውዮርክ ምንም አይነት ወኪል /Correspondent bank/ እንዳይኖራቸው እናግዳለን’ የሚል ጠበቅ ያለ ማስጠንቀቂያ ነው ይላሉ።

በሶስተኛ ደረጃ አሜሪካ ያቀረበችው ማስጠንቀቂያ በቀጥታ ለህውሃት ተወካዮች እንደነበር ይናገራሉ።

ማይክ ሐመር ለህወሐት ተወካዮች “በዚህ የማትስማሙ ከሆነ እናንተም ሆነ የትግራይ ህዝብ አሁን ባለው ከበባ ከማለቅ ውጪ ምርጫ የላችሁም” በማለት ያንዣበበባቸውን የመጥፋት አደጋ በግልጽ መናገራቸውን ያስቀምጣሉ።

አሜሪካ በአራተኛ ደረጃ ለኢትዮጵያ መንግስትና ለህውሃት ተወካዮች በጋራ ያቀረበችው ማስጠንቀቂያ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ስር ባለውና የአትሮሲቲ ዴተርሚኔሽን ሪፓርት በሚያወጣው ክፍል አማካኝነት በዚህ ጦርነት በሁሉም ወገኖች የሞቱ ወገኖች ምን ያህል እንደሆኑ መገናኛ ብዙሃን ይፋ እናደርጋለን የሚል እንደነበርም ገልጸዋል።

እሱን ተከትሎም በጦር ወንጀልና በሰብአዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች በባለስልጣናት ላይ ክስ እንዲመሰረት ግፊት እናደርጋለን የሚል ቁርጥ ያለ ማስጠንቀቂያ ማይክ ሐመር ማስቀመጣቸውን አመልክተዋል። ስምምነት ይፈጠራል ብለን በይደር ያቆየነው የጄኖሳይድ ብየና ሕግ አፋጥነን ዳር እናደርሰዋለን በማለት የመንግስታቸውን አቋም በግልጽ አስቀምጠውላቸዋል ብለዋል።

አሜሪካ ያቀረበችውን ማስጠንቀቂያ ተከትሎም ሰኞ ያለውጤት ሊጠናቀቅ የነበረው ድርድር እስከ ዕሮብ ድረስ እንዲራዘም ሆኗል ብለዋል የኢትዮ 360 የዲፕሎማቲክ ምንጮች።

ድርድሩ በተራዘመበት ወቅት የብልጽግና ወኪሎች ወደ ብልጽግናው መንግስት መሪ አብይ አህመድ ደውለው የሁኔታውን አሳሳቢነት ለማስረዳት ጥረት ሲያደርጉ እንደነበርም ምንጮቹ ሳይጠቁሙ አላለፉም።

ይሄንን ተከትሎም የብልጽግናው መንግስት በህገ መንግስታዊ አማራጭ ለመስማማት ተዘጋጅተናል የሚል አጀንዳ ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል። የብልጽግናውን ተደራዳሪ ቡድን የመራውና የተፈራረመው አቶ ሬድዋን ሁሴን ከስምምነቱ በኃላ አሜሪካ በዚህ ስምምነት ከፍተኛ ስፍራ እንደነበራት መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ ለውጭ ዲፕሎማቶች እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰቡ ገለጻ ማድረጉም ይታወሳል።

አቶ ሬድዋን በመግለጫቸው “አሜሪካ ህወሓትን ወደ ድርድሩ ለማምጣት፣ ለማሳመን እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት ጫና በመፍጠር ወደ ደቡብ አፍሪካም በማድረስ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክታለች” ሲሉ ምስጋናቸውን በአደባባይ ሲያቀርቡ መሰማታቸውም ይታወቃል። ይሁን እንጂ አሜሪካ በብልጽግናው ስርአት ላይ ስላሳለፈችው ከባድ ማስጠንቀቂያም ሆነ ተጽእኖ ከመናገር ተቆጥበዋል ይላሉ ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በስምምነቱ ላይ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላት የተገለጸው አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛው ማይክ ሐመር የፕሪቶሪያው ስምምነት እስኪተገበር ድረስ በቀጠናው እንደሚቆዩ እና ድጋፉም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማስታወቋንም ገልጸዋል።

በፕሪቶሪያ የተደረሰውን ግጭትን በዘላቂነት ማቆም ስምምነትን ተከትሎ በናይሮቢ የተጀመረው ንግግር አንዱ አጀንዳ በትግራይ የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መመለስ እንደሆነም አሜሪካ አስቀድማ በማስታወቅም በድርድሩ አጀንዳዎች ላይ የቅድሚያ እውቅና እንዳላት ማሳየቷንም ሳይጠቁሙ አላለፉም።

ከዚህ በተጨማሪም ለሁለት ዓመታት ያህል የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ከማስቀጠል በተጨማሪ የዚህ ውይይት አጀንዳዎች ስምምነቱን የመቆጣጠሪያ መንገዶችንና የትግራይ ኃይሎችን ትጥቅ ማስፈታት የሚሉ እንደሚገኙበትም አሜሪካ አስቀድማ መናገሯን አመልክተዋል።

Filed in: Amharic