>

ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ በ100ሺ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቅ ፍርድ ቤቱ ወሰነ...! (በጌትነት አሻግሬ)

ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ በ100ሺ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቅ ፍርድ ቤቱ ወሰነ…!

በጌትነት አሻግሬ


የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ የ100 ሺ ብር ዋስትና በማዝያስ ከእስር እንዲለቀቅ ውሳኔ አስተላልፏል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ፣ በጋዜጠኛ መዓዛ መሀመድ እና በደራሲ አሳዬ ደርቤ ላይ በአቃቢ ህግ የቀረበባቸውን ክስ በተመለከተ ክርክር ከተደረገበት በኋላ ዋስትና አያስከለክልም በሚል በዋስ እንዲወጡ መፍቀዱ ይታወሳል።

ይህን ውሳኔ ተከትሎም አቃቢ ህግ ይግባኝ በማለት ወደ ፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ጉዳዩን በመውሰዱ ችሎቱም በጋዜጠኛ መዓዛ መሀመድ እና በደራሲ አሳዬ ደርቤ ላይ የቀረበው ክስ ይግባኝ አያስቀርብም በሚል የወሰነ ሲሆን፤ የጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ክስ ግን ይግባኝ ያስቀርባል፤ ስለዚህ ክርክር ይደረግበት በማለት ሂደቱን ማስቀጠሉ አይዘነጋም።

ከዚህ በፊት ጥቅምት 22/2015 ዓ/ም በፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ በዋለው ችሎት ሦስተኛው ዳኛ በህመም ምክኒያት ባለመገኘቱ  በዋስትናው ጉዳይ ብይን ለመስጠት  ለጥቅምት 30/2015 ዓ/ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን የአማራ ድምፅ ዘግቦ ነበረ።

በዚህም መሰረት ትላንት ጥቅምት 30/2015 ዓ/ም በዋለው ችሎት ዳኞች ጉዳዩን በደንብ መርምረን አልጨረስንም በማለታቸው በይደር ለዛሬ ተቀጥሮ ነበር።

ዛሬ ህዳር 01/2015 ዓ/ም በዋለው ችሎት ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ የ100 ሺ ብር ዋስትና በማዝያስ ከእስር እንዲለቀቅ ነው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ  ውሳኔ ያስተላለፈው።

Filed in: Amharic