>

"የቀድሞ የነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞችን ነበር  ልንከትብ መክረን ነበር የሆነው ወዳጄ...! (ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን)

“የቀድሞ የነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞችን ነበር  ልንከትብ መክረን ነበር የሆነው ወዳጄ…!

ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን


ከሁለት ሳምንት በፊት

ደወለልኝ።

እና አወራን።

ከ25 ዓመት በኋላ መሆኑ ነው ድምፁን ስሰማ።

የዛሬ 25 ዓመት ገደማ ከበርካታ የጋዜጣ ፅሁፎች ክስ በኋላ፣ ድንገት ታፈነና ዘብጥያ ተወረወረ። ካዛንችስ አካባቢ የሚገኘው የደህንነት መ/ቤት ነው የታሰረው።

እናም የሃገሪቱ ደህንነቶች ዋና ኃላፊ አቶ ክንፈ ገብረመድህን እንዲህ አሉት፦

“ከአሁን በኋላ ኢህአዴግ ላይ ብዕርህን ታነሳና ውርድ ከራሴ። በሕይወትህ  መፍረድህን እወቅ”

በማስጠንቀቂያ ለቀቁት።

ከዚያ በኋላ ሐገሩን ለቅቆ ለመውጣት ወሰነ። ተሰደደ።

እነሆ ከ25 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ስልክ ደወለልኝ። እንዲደውልልኝ መልዕክት የሰደድኩበት እኔው ነኝ።

“የነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞች ትግል እና ታሪክ በወጉ አልተፃፈም፤ ለምን የጋዜጠኞቹን ታሪክ አሰባስበን ዳጎስ ያለ መፅሐፍ  አናሳትምም?” አልኩት።

“ልክ ነህ” አለኝ።

“እኛም አሜሪካ በመሠረትነው የነፃ ፕሬስ ጋዜጠኛ ማሕበር አማካኝነት ነገሩን አስበን ነበር። የጥቂት የተሰደዱ ጋዜጠኞችን ታሪክ አሰባስቤአለሁ፤  ነገሮች ስላልተመቻቹ በጅምር ቀረ እንጂ። ፅሁፉ እኔጋ ነው ያለው። ከሁለት ሳምንት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ስለምመጣ እዛው እሰጥሃለሁ። አንተ የሌሎቹን ታሪክ ጨምረህ ታሳትመዋለህ” አለኝ።

(በነገራችን ላይ ዳዊት በ1997 ምርጫ ሰበብ በሌለበት ተከስሶ ዕድሜ ልክ የተፈረደበትና ወደ ሀገሩ እንዳይመለስ የታገደ ጋዜጠኛ ነው)

እናም

“አዲስአበባ በመጣሁ የመጀመሪያው ሳምንት በማገኛቸው ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ተካተሃል፤ አገኝሃለሁ” አለኝና ከአንድ ሰዓት የስልክ ወሬ በኋላ ተሰናበተኝ።

ከ15 ቀን በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጣ።

ዕሁድ ጥቅምት 27  ቀን 2015  ዓም በFacebook  ገፁ አዲስ አበባ ከገባ ሁለተኛ ቀኑ መሆኑን ፃፈ። ያየውን፣ የታዘበውንም ጨምሮ። ፅሁፉን እያነበብኩ በዚህ ሳምንት እንደምንገናኝ አሰብኩ።

ትናንትና፤

ጥቅምት 29 ቀን 2015 ከቀኑ 8 ሰዓት አካባቢ ከውጪ ሃገር አንድ ስልክ ተደወለ።

“ዳዊት ከበደ ወዬሳ ሞተ እየተባለ ነው፤ እስቲ አጣራ” አለኝ። ሠማይ ምድሩ ዞረብኝ። ደዋዩ የባለቤቱን ስልክ ሰጥቶኛል። ከተረጋጋሁ በኋላ ደወልኩላት።

“…… እቤት ውስጥ ቁጭ ብሎ ኮምፒወተር ከፍቶ እየፃፈ ነበር፤ ድንገት ሸተት ብሎ ወደቀ፤ አመለጠኝ” አለችኝ ባለቤቱ እያለቀሰች።

ማመን አልቻልኩም። “ቶማስ”ን የሆንኩ መሰለኝ።

ዳዊት ከበደ ወዬሳ (የአውራምባው አይደለም) የነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞች ፊታውራሪ የነበረ ነው። ከቀደምቶቹም ቀደምት። በተለይ ለተሰደዱ ጋዜጠኞች “መከታ” የነበረ ነው። ሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች ሲታሰሩ ቤተሰቦቻቸውን “አለሁ” የሚል  ብርቱ ታጋይ ነበር።

ይኸው ሀገሩ ለስራ ጉዳይ መጥቶ በአራተኛ ቀኑ ሞተ። ሞቱን እንዴት  ማመን ይቻላል?! ሆኖም ግን እርግጥ ሆኗል። ዳዊት ተለይቶናል።

ሞቱ፣ “የሀገሬ አፈር ይብላኝ” እንዲሉ ይመስላል።

ያሳዝናል።

😭

Filed in: Amharic