>

ጋሼ ኃይሉ (ገሞራው) ሲታወስ ...! (ሱራፌል አየለ)

ጋሼ ኃይሉ (ገሞራው) ሲታወስ …!

ሱራፌል አየለ


አዎ ጋሼ ኃይሉ ለመጨረሻ የአገኘሁት ጊዜ እቤቱ ምሳ ጋበዘኝ::  ከዚያ አንድ ቀን ቀድሞ ይህን ፎቶ ያነሳሁት ዕለት ደግሞ ወደ አንድ እስቶኮልም ከተማ ውስጥ ወደሚገኝ የሀገራችን ምግብ ቤት ወስዶ አስተናግዶኝ ነበር:: ስቶኮልም ዋና ቤተመጻሕፍት አጠገብ ተገናኝተን::   በማግስቱ በአደረገልኝ የምሳ ግብዣ ላይ የአልቀረበ የምግብ ዓይነት አልነበረም::  አምሮህ ይሆናል እያለ ቆሎው አረቂው ጠጁም አልቀረም::  ዕድሜውን በሙሉ ለሰው ልጅ ፍቅር የኖረ ሰው ነው::  በምር ህይወቱም በብዕሩም::  ቸር አዛኝ በዕለት ተዕለት ህይወቱም በብዕሩም ፅኑ ሰውን አፍቃሪ ነው::  “ደራሲ ለሰው ልጅ ለህይወት ስሱ ስሜት አለው” ለሚለው የተለመደ ሙያዊ አባባል የምር ማሳያ ነው ጋሼ ኃይሉ ገሞራው::  የሀገራችንን ታሪክና ወግ ከሩቅ ምሥራቅ ወጎችና ፍልስፍና ጋር እያሰናኘም በደረሳቸው ዘመንና ትውልድ ተሻጋሪ ህዝባዊ የሥነፅሁፍ ስራዎቹ ብቻ ሳይሆን በሰብዕናውም የገዘፈ አባት የጥበብና የፍልስፍና ኮከብ ነው::  በመቶ ዓመታት ውስጥ ተፈጥረው በየዘመኑ ፈንጥቀው ከሚያልፉ ጥቂት እጅግ በጣም ጥቂት ከዋክብት ውስጥ አንዱ ነው ጋሼ ኃይሉ::

አንድ የጋራ ወዳጃችን ስለእሱ ያጫወተኝን ገጠመኝ ላውጋችሁና ትውስታዬን ልቋጨው::  አንድ ስቶኮልም የሚኖር ሰው ወደሀገር ቤት ሲሄድ ጋሼ ኃይሉ ለተቸገረ ሰው ስጥልኝ  ብሎ ገንዘብ ይሰጠዋል::  ግለሰቡ ሲመለስ የተላከውን አላደረሰም ነበርና ህሊናውን እየቆረቆረ ስለፀፀተው አንድ ቀን “የላከኝን እረስቼ አልሰጠሁም” በማለት ሲነግረው ፈገግ ብሎ የመለሰለት እንዲህ በማለት ነበር::  “እኔ እኮ ለይቼ ለእገሌ ስጥልኝ አላልኩህም::  ለተቸገረ ነው ስጥልኝ ያልኩህ::”

*   *   *

በ1959 ዓም በቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ አንድ የግጥም ውድድር ይካሄዳል ከተወዳዳሪዎች መካከል አንዱ “በረከተ መርገም” የተሰኘ ስራ በስሜት  ያቀርባል። ሲጨርስ ውጤቱን ለመስማት ግድ ሳይሰጠው አዳራሹን ጥሎ ይወጣል ። የውድድሩ አሸናፊ የዚህ ሰው ስራ ሆነ!

ሀይሉ ገ/ዩሀንስ (ገሞራው) !

ይህ በረከተ መርገም የተሰኘ የግጥም ስራ ለሰው ልጆች መጠቀሚያና ህይወትን ማቅለያነት ተፈልስፈው ለላይኛው መደብ   መጠቀሚያነት ብቻ የዋሉ ፣እኩልነት ማስፈን ሲገባቸው የሰውልጆችን በደረጃ ለመከፋፈያነት የዋሉ ሀሳቦች ፣ ፈጠራዎች እስከነ ፈጣሪያቸው በማውገዝ ይረግማቸዋል ።

ከብዙው መሀል አንድ እርገማን

” ከቶ መመስረትህ  በደል ለማፅደቂያ የውሸት ምክርቤት

በተስማምቻለሁ ለማድለብ ከሆነ የሰዎችን ሙክት

መንጋ ማጎሪያውን ፓርላማ ነው ብለህ ለኛ ስላሳለፍክ

የአንግሎ ሳክሶኑ ለፍዳዳው ዊሊያም ዘርህ አይባረክ    ”

የግጥሙ ጭብጥ ዘመን የማይሽረው  (classic) እንዲሆን የሚያስችለው አሁንም ድረስ እኩልነትና ፍትህ የትም ቦታ በሰዎች አብርሆት (Enlightment) ልክ ባለመመንደጋቸው ነው። ሰው የትኛውንም አይነት መራቀቅ(Advancement) በየዘርፉ ቢያሳይ በሌላው ላይ  ማነቆ ማጥለቁ አይቀሬ ነው። ገሞራው ማነቆውን ጌጡ አድርጎ የሚዞረውን፣አወልቆ ለመጣል ከሁኔታዎችም ይሁን ከራሱ ጋር የማይታገለውን ከከንቱነት ይፈርጀዋል ። እንዲህ ይረግመዋልም።

” እንደዚህ ከሆነ የተፈጥሮህ ፀባይ

ለስሜት ከሆነ የመኖርህ  ጉዳይ

ችግርን ተደሰት ደስታህን ተሰቃይ ”

አላማ ቢስ ዋል ፈሰሶችን ደግሞ እንዲ ይገልፃቸዋል

“ላለመኖር መኖር ለመኖርም መኖር

ላለመማር መማር ለመማርም መማር

ለማግኘት መታገል ለማጣትም መጋር” …….

በግጥሙ ውስጥ ገሞራው ወጫዊ ግጭት (external conflict) ውስጥ ይገባና ተፈጥሮን ይረግማል።

ፀሀዩን አየሩን ምክኒያት አድርገህ

ጥንት ያልነበረውን መንደሮችን ፈጥረህ

ትግሬና ጉራጌ አማራ ኦሮሞ

ሽናሻና ዶርዜ በማለት ሸንሽነህ

በቋንቋ በልማድ ባልባሌ ፀባይ

በዥጉርጉር መንፈስ ያላግባብ ከፋፍለህ

ቃዲውን ከቄስ ጋር በምህታት ማስረጃ

በእምነት ለያይተህ

ይህን የመሰለው ሽርፍራፊ ህግህ

ደደብ ስላሰኘህ

ተፈጥሮ አማትክን!  ባለጌ ዳኛ ነህ ።

…….

ከዚህ ሁሉ መውጫ ህብረት አንድነት መሆኑን በመጠቆም በሚያሳይበት ስንኞች ላብቃ።

ያሰብከው አላማ አልሆን ብሎ ሲከሽፍ

ሁኔታው ሲጠጥር

ጠጣሩ እንዲላላ የላላውን ወጥር!

—–

ገጣሚው ኃይሉ ገ/ዮሃንስ ዘመኑን ሙሉ ከሃገሩ ተሰድዶ ኑሮውን በእንግልት እንደገፋና ለእውነት በመወገኑ ብቻ ከምቾት ተነጥቆ ነፍሱ ከፍ እንዳለ፤ ስጋው ደግሞ የዝቅታ ሕይወትን እየገፋ የምድር ምልልሱን ጨርሷል። በስደት በነበረበት ዘመን ከጎኑ ካልጠፉት ጥቂት ወዳጆቹ መሃል አንጋፋው ጋዜጠኛ፣ ደራሲ ገጣሚ ጋሼ Abera Lemma አንዱ ነበሩ።

—-

NB. ለአንባቢ እንዲመች በተጠቀሱ ስንኞች ላይ ማሳጠርና በቃል ደረጃም የተደረገ ለውጥ አለ ።

ገሞራው አንረሳህም

Filed in: Amharic