ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት መኢአድ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሠጠ መግለጫ:_
“ለተከበረው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ለመብትህ እና ለነፃነትህ መከበር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከመኢአድ ጎን በመሰለፍ ለሰላማዊ ትግል እንድትዘጋጅ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡”
ድርጅታችን የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ለበርካታ አመታት ለሕግ የበላይነት እና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በርካታ እልህ አስጨራሽ ሰላማዊ ትግል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
አሁንም አጠናክሮ እየታገለ እና እያታገለ ይገኛል፡፡
መኢአድ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ውጥንቅጡ ከወጣ ፖለቲካዊ. ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ጉዞ ወጥታ፣ ችግሯ በዘላቂነት ተፈትቶ፣ ሠላሟ የተረጋገጠ፣ ሀገር እንድትሆን ፅኑ ፍላጎት አለው፡፡
የመኢአድ የአዲስ አበባ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለቀጣዩ ሦስት ዓመታት የሚያገለግሉ የድርጅቱን የትግል አቅጣጫ አሁን ካለበት ወደተሻለ ደረጃ ያራምዳሉ ተብለው የተመረጡ የአዲስ አበባ መኢአድ የም/ቤት አባል ምስረታና የአዲስ አበባ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫን በ27/02/2015 ዓ.ም በተሳካ ሁኔታ አከናውኖ አዳዲስ እና ወጣት የሥራ አስፈፃሚ አባላት ወደፊት እንዲመጡ አድርጓል፡፡
በመላ ሀገሪቱ የምትገኙ የመኢአድ አመራሮችና አባላት ይሄንን ፈለግ በመከተል ለተሻለ ሥራ እንዲነሳሱ የአዲስ አበባ መኢአድ ስራ አስፈፃሚ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
አዲሱ የአዲስ አበባ መኢአድ አመራር አዲስ አበባንና ህዝቦቿን በተመለከተ መንግስት የሚከተለውን ፖሊሲ በጥልቀት የሚከታተለው መሆኑን እና በተለያየ መንገድ የሚከሰቱ ተፈጥሯዊም ሆነ ሠው ሠራሽ ችግሮች ከህዝብ ጎን በመቆም የሚከላከል መሆኑን ይገልፃል፡፡
ከዚህ ቀደም ሲያደርግ እንደነበረው በሕዝባችን እና በሀገራችን ላይ የተለያዩ አደጋዎች ሲያጋጥሙ ከመንግስት ጋር የርዕዮተ-ዓለም ልዩነት ቢኖረንም እንኳ ለሕዝብና ለሀገር ጥቅም ሲባል ልዩነታችንን ወደጎን በመተው በትብብር የምንሰራ መሆኑን እየገለፅን፣ በመንግስት በኩል የሚፈፀሙ ስህተቶች ሲኖሩም መንግስት ችግሮችን በአስቸኳይ እንዲፈታ ተፅዕኖ መፍጠራችንን እንቀጥላለን፡፡
ለዚህም ተፈፃሚነት ከሕዝቡ ጋር የተለያዬ አደረጃጀትን በመፍጠር እንቅስቃሴዎችን እያደረግን እንገኛለን፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በከተማዋ የተለያዩ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ከኦሮሚያ ባንድራና መዝሙር ጋር በተያያዘ ለፀብ መነሻ የሚሆኑ ችግሮችን የከተማ አስተዳደሩ አፅንኦት በመስጠት ዘላቂ መፍትሔ የሚመጣበትን መንገድ እንዲያመቻች አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡
የዛሬ ወጣቶች የነገ ሀገር ተረካቢዎች ናቸውና ያለፍላጎታቸው ማንኛውንም ነገር በኃይል ለመጫን የሚደረግ ሙከራ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን እንዲህ አይነት ኢ-ሕገ-መንግስታዊ ጉዳዮች በጊዜ መፍትሔ ሊፈለግላቸው እንደሚገባ ድርጅታችን መኢአድ በፅኑ ያምናል፡፡
በመሆኑም የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የአዲስ አበባ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሚከተሉትን አስቸኳይ ጥሪዎች ያቀርባል፡-
1ኛ. ለተከበረው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ለመብትህ እና ለነፃነትህ መከበር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከመኢአድ ጎን በመሰለፍ ለሰላማዊ ትግል እንድትዘጋጅ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
2ኛ. የአዲስ አበባ ከተማ ህልውና ወደባሰና ውስብስብ ችግር ከማምራቱ በፊት መንግስት ያልተገባ አካሄዶችን እንዲያርም ህዝብም እየሆነ ያለውን ነገር በቅርበትና በትኩረት እንዲከታተል ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
3ኛ. መንግስት አሁን ያለውን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ሚሊዮኖችን ለከፋ ረሀብና ጉዳት ከመዳረጉ በፊት በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ ገብቶ ያለውን የገበያ ምስቅልቅል እንዲያርምና እንዲያረጋጋ እንጠይቃለን፡፡
4ኛ. በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ክፍት ቦታዎችን ባልተገባ ሁኔታ በገበሬ ልጆችና በአርሶ አደር ስም እየተመዘበረ ያለውን የህዝብና የሀገር ሀብት ከሕገ-ወጥ የመንግስት ባለሥልጣናትና ደላሎች እንዲጠብቅ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
5ኛ. በቅርቡ የሚደረገው ብሔራዊ መግባባት ላይ የአዲስ አበባን ህዝብ ጥቅም፣ ፍላጎትና መብት የሚከበርበት እንዲሆን በትኩረት እንሰራለን፡፡
6ኛ. ለአዲስ አበባ ከተማ መኢአድ አባላትና ደጋፊዎች፣ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ለእቅዳችን መሳካት የበኩላችሁን ሁለንተናዊ ድጋፍ እንድታደርጉልን ስንል ጥሪ እናቀርባለን፡፡
7ኛ. በመጨረሻም ለሚዲያ ተቋማትና ባለሙያዎች፡- ከእናንተ ጋር አገርን በሚጠቅሙ ማህበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ጉዳዮች በጋራ ለመሥራት በማንኛውም ቦታና ሰዓት አብረን ለመሥራት ቁርጠኛ መሆናችንን መግለፅ እንወዳለን፡፡