>

የዳዊት ከበደ ወየሳ የህይወት ታሪክ ...! (በቀድሞ የስራ ባልደረቦቹ የተዘጋጀ)

የዳዊት ከበደ ወየሳ የህይወት ታሪክ …!

በቀድሞ የስራ ባልደረቦቹ የተዘጋጀ

 


ዛሬ የምንሸኘው ቁመተ ሎጋው፣ መልከ መልካሙ፣ ለእውነት፣ ለሀቅ ሲል ግንባሩን የማያጥፈው፣ ለተጨቆኑ እና መከራ ውስጥ ለነበሩ ሁሉ አለሁላችሁ እያለ የሚጋፈጠው፣ አይፈሬው ጋዜጠኛ፣ ትንታጉ ጋዜጠኛ ፣ እጅግ የምንወደው ወንድማችን ዳዊት ከበደ ወዬሳ ነው።

ዳዊት ከበደ ወየሳ የኤምባሲዎች መናገሻ የሚል ስያሜ ከወጣላት አዲስ አበባ ቄራ አካባቢ፤  ኬላ በር በሚባል ሰፈር፤ ታህሣሥ 19 ቀን፣ 1961 ዓ.ም ተወለደ፡፡ እድሜው ለትምህርት ሲደርስ በእውቀት ምንጭ ት/ቤት ፊደል ቆጠረ። ከዚያም 1ኛ ክፍልን በ1969 ዓ.ም በካቴድራል የወንዶች የግል ትምህርት ተከታተለ፡፡ ከ2ኛ ክፍል ጀምሮ፤ 4ኛ 5ኛ ክፍልን በአንድ አመት አጥፎ በመማር እስከ 8ኛ ክፍል ትምህርቱን  በፈለገ ዮርዳኖስ ት/ቤት ተከታተለ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በዳግማዊ  ምኒልክ  ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ ከዚያም የተግባረ- ዕድ የቴክኒክና ሙያ ለመከታተል በምስራቅ አጠቃላይ ትምህርት ቤት በ1979 ዓ.ም በኤሌክትሪክ ሙያ ተመረቀ። ዳዊት በተጨማሪም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነጽሁፍ ክፍል ውስጥ የስነጽሁፍ ትምህርትን መከታተል ችሏል፡፡ ካናዳ መኖሪያውን ካደረገ በኋላም በMemorial ዩኒቨርስቲ of Newfoundland ገብቶ Information Technology  ዲግሪውን ማግኘት ችሏል፡፡

ዳዊት ከበደ ወዬሳ፣ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ፤ በመብራት ኃይል መስሪያ ቤት ተቀጥሮ ስራ ከመጀመሩ በፊት   የወጣት ከያኒያን ክበቦችን ያደራጀበት እና የተሳተፈበት ጊዜ በመሆኑ፤ በህይወቱ ውስጥ  እነዚያ ጊዜያት ልዩ ስፍራ እንዳላቸው ይገልጻል። በወቅቱ ከነበሩ የልጅነት ባልደረቦቹ አብሮ አደጎቹ መካከል አብዱራህማን አህመዲን፣ አየለ ሸጉ፣ ሙሼ ሰሙ፣ ታገል ሰይፉ፤ ሁለቱም ደረጀ ኃይሌዎች፤ ሀብቴ ምትኩ፤ እስጢፋኖስ ጸጋዬ፤ ሰራዊት ፍቅሬን፤ ሰለሞን አለሙ፣ ድርብወርቅ ሰይፉ፣ እስጢፋኖስ ባልቻ፣ ሳሙኤል አዳል፤ ውድነህ ክፍሌ እና ተመስገን መላኩ ይጠቀሳሉ፡፡

ዳዊት ከበደ በተመረቀበት የኤሌክትሪክ ዘርፍ፤ በኢትዮጵያ የመብራት ኃይል መስሪያ ቤት የመብራት ኃይል ልሳን ለሆነው “ፈለገ ብርሃን” ጋዜጣ በመጻፍም ይታወቃል።

በለገዳዲ ሬዲዮ ጣቢያ፤ የቅዳሜ እና የ’እሁድ ዝግጅት በማህበራዊ ህይወት ላይ ያተኮረ በመሆኑ፤ አጫጭር ድራማዎች እና ግጥሞችን እየጻፉ ለማቅረብ፤ በጊዜው ለነበሩ ወጣቶች ሌላኛው ምርጫቸው ስለነበር፤ ዳዊት ከበደ ከ16 አመቱ ጀምሮ በዚህ ስፍራ ያሳለፈውን ጊዜ፤ እንደትምህርት ቤት አድርጎ ይወስደዋል።

ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ሞገድ ጋዜጣ ውስጥ ኩራፒታ አምድ ላይ አዘጋጅ በመሆን  በተሳሳተ ትርክት ሲጎሳቆሉ የነበሩ ታሪኮችን ሲጠግን ቆይቷል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም ‹‹ፈለግ›› መጽሔት ላይ መጀመሪያ ላይ “ቦምባርድ አነሳሱና አወዳደቁ” የሚል ጽሁፍ ጽፎ ተወዳጅነት አገኘ። ቀጥሎም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ የተማሪዎችን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሲደረግ፤ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችንና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነሩን በማነጋገር፤ “ከመጀመሪያው ፉጨት እስከ መጨረሻው ጥይትና የዩኒቨርስቲው መዘጋት”  የሚል ፤ በዘመኑ ድፍረት የሚጠይቅ አስደናቂ ሪፖታዥ ሰርቶ ነበር። በዚህ ዘገባው ምክንያት ከአቶ ሙሉጌታ ሉሌ፣ መጽሐፈ ሲራክ እና አሁን ስማቸውን የማያስታውሳቸው ጋዜጠኞች ጋር በጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው መታየት ጀምሮ ነበር። የክስ ጥሪውም የተደረገው በፖሊስ ሳይሆን፤ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ነው።

ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ… በሩህ፣ በፈለግ፣ በሞገድ፣ መጽሄትና ጋዜጦች ላይ በአምድ አዘጋጅነት ብቃቱን አሳይቷል፡፡ በመብረቅ፣ በማዕበል እና ሌሎች የነጻ ፕሬስ ጋዜጦች ላይ  የራሱን አበርክቶ አድርጓል። ከምንም በላይ ግን ራሱ አዘጋጅ ሆኖ የሰራባቸው ታደለች፣ ወይ ፍቅር እና ብሌን መጽሄቶች የራሳቸው ቀለም የነበራቸው ብርቅዬ መጽሄቶች ናቸው። “ታደለች”  በሴቶች ህይወት ላይ የምታተኩር በወንድ የምትዘጋጅ የመጀመሪያዋ የሴቶች መጽሄት ነበረች፡፡ ዋና አዘጋጇም ዳዊት ከበደ ወየሳ ነበር፡፡ ‘ብሌን የተሰኘው መጽሄት ደግሞ ታዋቂ ብዕረኞች  እውቅ ጸሃፊያንን ያሰባሰበች በዳዊት ፊት አውራሪነት ትመራ የነበረች የህትመት ውጤት ነበረች፡፡

ዳዊት ከበደ ፊያሜታ  ጋዜጣን ከመሰረተ በኋላ በህወሃት የደህንነት አባላት ታድኖና ታፍኖ ካዛንቺስ በሚገኘው የደህንነት መስሪያ ቤት ህንፃ ስር በተሰራ ምድር ቤትታስሮ መንፈሳዊ ስብራት ደርሶበታል።

ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ የጋዜጠኝነት ሙያው ላይ ባሳለፋቸው ውጣው ረዶች  የበዙ ሁነቶችን ታዝቧል፡፡ የሚጠቅሙትን ደግሞ ቃርሟል፡፡ በተለይ  ሀሳብን በነጻነት መግለፅ ከመንግስት ትይዩ በህትመት ባለቤቶች  ሊታፈን እንደሚችል በተግባር የዘለቀ ትዝብት ነበረው፡፡

ዳዊት ከበደ የመጀመሪያውን ጋዜጣ፤ “ፊያሜታ” ብሎ ሲሰይም፤ ‘ትንሽ እና የምታምር የ’እሳት ነበልባል’ ማለት መሆኑን ታሳቢ አደረገ፡፡ ጋዜጣውን ሲያሳትም፤ እራሱ አሳታሚ እና ዋና አዘጋጅ ሆኖ ስራውን ጀመረ።

ትንታጉ ጋዜጠኛ ዳዊት አንድ የሚድያ ሰው አለባበሱ ስርአቱን የጠበቀ መሆን አለበት ብሎ ያምናል፡፡ እርሱ ራሱ ካፖርትና ሱፍ ከስካርፍ ጋር በማድረግ ይታወቃል፡፡ ጋዜጠኛ በልብሱ መከበር እንዳለበት ዳዊት ያምናል፡፡  ዳዊት በጋዜጠኝነቱ ለእስር ይዳረግ በነበረበት ጊዜ ካፖርቱን ለብሶ ሲሄድ ከሳሾቹ ራሱ አንተ ጋዜጠኛ ነህ ? ብለው ጥያቄ ያቀረቡበትን ጊዜ ያስታውሳል፡፡

ጋዜጠኛ ዳዊት በሙያው ፈታኝ ፍም ግፎችን ውጧል፡፡ የጀነራል ኃየሎም አርአያን ግድያ እስከ ገዳዩ ጀሚል ያሲን ድረስ ያለውን የፍርድ ሂደት ተከታትሎ ዘግቧል፡፡  ከጀሚል ከራሱ አንደበት ጄነራል ሃየሎምን እንዴት እንደገደለውና የመጨረሻ ኑዛዜው ድረስ የምርመራ ዘገባ ሂደትን በመጠ ቀም የሰራውን ዘገባ ፈጽሞ አይረሳም፡፡

የፓትሪያርኩ ተከታታይ ታሪክ፤ የአርበኞች ጉዳይ፤ በጋምቤላ ስለ ነበሩ ግድያዎች፤ አሰፋ አብርሃ የኮካ ኮላ ቅሌት፤ የሱር ኮንስትራክሽን እቃዎች ምዝበራ፤ የሚሸሹ ገንዘቦች የተለያዩ የክስ አይነቶችን እያስነሱ ጋዜጠኛ ዳዊትን አባትለውታል… ገሚሶቹ ክሶች በሚያቀርባቸው ተጨባጭ ማስረጃዎች ከሳሾችን አንገት አስደፍተዋል፡፡

ዳዊት ከበደ  በጥር 1992 በስደት መጀመርያ ኬንያ ከዚያም ካናዳ አቀና፡፡

የኢትዮጵያ ነፃ-ፕሬስ ጋዜጠኞች ማህበር እንደገና ሲደራጅ፤ ጋዜጠኞችን ያሰባሰበ፤ እነ አቶ ክፍሌ ሙላት በፕሬዘዳንትነት እንዲመሩ ሲመረጡ ዳዊት ከበደ በህዝብ ግኑኝነት ኃላፊነት ሰርቷል።

ዳዊት ከበደ የእድሜ ልክ እስራት በሌለበት ፍርድ ቤት ውሳኔ  የወሰነበት ትንታግ ጋዜጠኛ ነበር፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን በስደት ላይ ካሉ  ጋዜጠኛ ክንፉ አሰፋ፤ ግርማ እንድርያስ፣ አትክልት አሰፋ፣ ሉሉ፣ ሰይፉ፣ ክብረትና አክሊሉ ታደሰ ጋር በመሆን በስደት የሚገኙ የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞችን ፎረም መሰረተ፡፡ ከእለታዊ ችግሮችን ከመፍታት ጀምሮ ጋዜጠኞች ከሙያቸው እንዳይርቁ በርካታ ሙያዊ እና ሰብአዊ ሥራዎችን ሰርቷል፡፡ በዚህ የስደት ዘመን እንደአሜሪካ አቆጣጠር ከ2002 እስከ 2005 ድረስ የህብረት ድምፅ መጽሔት፤ ድምፅ ጋዜጣን በዋና አዘጋጅነት ለህትመት አብቅቷል። የስራ እና የሙያ ባልደረባው ለነበረው ጓደኛው ቴዲ  ቃል በገባው መሰረት፤ ቴዲ ካለፈ በኋላ፤ በሰሜን አሜሪካ በየወሩ የምትታተመውን ባለ 80 ገጽና ባለ ሙሉ ቀለም መጽሄት ሳያቋርጥ አስቀጥሏል።

ዳዊት ከኦሃዮ ወደ አትላንታ ሲዛወር፤ ከሙያ አጋሮቹ ቴዲ፣ መልካምዘር እና ዳኔል አሰግድ ጋር በመሆን፤ በ2006 አድማስ ሬዲዮን ሲሰራ ቆይቷል፡፡

ከ2005 ጀምሮ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በየቀኑ ወደ አገር ቤት ይገባ የነበረው የትንሳኤ ሬዲዮ ነው። ትንሳኤ ሬዲዮ የመጀመሪያው የተቃዋሚዎች ድምጽ የሚስተጋባበት የሬዲዮ ጣቢያ ሆኖ ለ3 አመታት ያህል ቆይቷል።

ዳዊት ከበደ ወየሳ በትንሳኤ ሬዲዮ ሃላፊ ሆኖ አገልግሏል፡፡

ዳዊት ከበደ ወየሳ  በ2006 ዓ.ም ከቴዲ እና ከጓደኞቹ ጋር በመሰረተው አድማስ ሬዲዮ በሃላፊነት ያገለግላል። እንዲሁም የፈረንጆቹ 2023 ሲመጣ ሃያኛ አመት የሚሞላት፤ በህይወት የሌለው የጓደኛው እና የአትላንታ ህዝብ ኩራት የሆነው ድንቅ መጽሔት ዋና አዘጋጅ እና አሳታሚ ነው።

ከምንም በላይ ለኢትዮጵያ ታላቅ ፍቅር አለኝ እያለ ሲደመጥ የነበረው ዳዊት ከበደ ወየሳ  ከ20 አመት በላይ ከሚኖርበት አሜሪካ ለእረፍት ወደ እናቱ ሀገሩ መጥቶ በድንገተኛ ህመም ማክሰኞ ጥቅምት 29 2015 በ53 አመቱ ህይወቱ አልፏል፡፡ ዳዊት ከበደ ወየሳ ባለትዳርና የአንድ ወንድ እና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነበር፡፡

ፈጣሪ የውድ ጓደኛችንን ነፍስ ይማርልን። ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጅ ጓደኞቹ መፅናናትን ይስጥልን።

Filed in: Amharic