>

የሐዘን መግለጫ መልዕክት (ክፍሌ ሙላት የ ኢ.ነ.ጋ.ማ - የቀድሞው ፕሬዚዳንት)

የሐዘን መግለጫ (መልዕክት)

ክፍሌ ሙላት

የ ኢ.ነ.ጋ.ማ – የቀድሞው ፕሬዚዳንት

የክቡር ሙያችን ባለቤትና የኢትዮያችን ባለውለታ፣ የፕሬስ ነፃነት ተሟጋችና የሕዝብ ባለአደራ የነበረው ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን የሰማነው በተሰበረ ልብና ጥልቅ የሐዘን ስሜት ተሞልተን ነው።

ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ በኢትዮጵያችን ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት እንዲከበርና የፕሬስ ነፃነት እንዲያብብ በቁርጠኝነት ሲታገል፣ ሲያስተባብርና ሲመራ የነበረው የኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞች ማበር ኢነጋ መስራች አባልና የአስተባባሪ ኮሚቴው የሕዝብ ግንኙነት ተጠሪም ነበረ።  ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ የበርካታ ጋዜጦች አሳታሚና ዋና አዘጋጅ ከመሆኑም በተሸማሪ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ተበትነው በስደት የሚኖሩ የነፃ ፕሬስ አባላትን በአንድነት በማስተባበር የሚካሄደውን የአንድነትና የሕብረት ዓለም አቀፋዊ መድረክ በመምራትም እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷክ።

ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ ግንምባራቸውን ሳይጥፉና ለአምባገነኖችና ፍርደ ገምድሎች የወቅቱ ዘረኛ ገዥዎች ሳይንበረከኩ ሕይወታቸውን ጭምር ለሙያው ክብር አሳልፈው ከሰጡ አይበገሬ ጋዜጠኞች ተራ በግምባር የተሰለፈ ሐቀኛ ባለሙያ ነበር።

በሙያቸውና ሕዝባዊነታቸው፣ እንዲሁም በመልክማ ምግባራቸው ትውልድና ታሪክ ከሚዘክራቸው ኢትዮጵያውያን የሙያ ባልደረቦቻችን አንዱ ዳዊት ከበደ ወየሳ መሆኑን በኩራት እንመሰክራለን።

ኃያሉ፣ ጠቢቡና ረቂቁ ፈጣሪያችን የሙያ ባልደረባችንን ነፍስ በአፀደ ገነት ያሳርፍልን። ለቤተሰቡ ለወዳጅ ዘመድ እንዲሁም የሙያ ባልደረቦቹ በኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞች ማህበር ኢነጋማ የቀድሞው አመራር አባላትና በራሴ ስም መፅናናትን እመኛለሁ።

ሒውስተን – ቴክሳስ

(ኖቬምበር ,2022)

Filed in: Amharic