>

አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም''፤ የአፍሪቃ ጭንጋፍ ፖለቲከኞች፣ ምዕራባዊያን እና ደሀው የአፍሪቃ ሕዝብ...! (ያሬድ ሀይለማርያም)

አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም”፤ የአፍሪቃ ጭንጋፍ ፖለቲከኞች፣ ምዕራባዊያን እና ደሀው የአፍሪቃ ሕዝብ…!

ያሬድ ሀይለማርያም


የአፍሪቃ ሕዝብ ከምዕራባዊያን ቅኝ ግዛት ቢላቀቅም ከራሱ ጉያ በወጡና በምዕራባዊያን በሚዘወሩ የካድሬዎች ቅኝ ከዋላ እነሆ ሦስት አሥርት አመታት ተቆጠሩ። ምዕራባዊያኑ ዝርፊያን፣ ዘረኝነትን እና ንቀትን መሠረት ያደረገውን አፍሪቃን የማራቆት የቅኝ ግዥ ፓሊሲያቸውን ከአፍሪቃ ጉያ ለወጡት ጭንጋፍ ልሂቃን አውርሰው እና ዘላቂ ጥቅማቸውን አደላድለው ነጻ የወጣች አስመስለው ለቀቋት። አፍሪቃም ነጻ ወጣች ተባለ። እውነታውን ግን በአህጉሪቷ ውስጥ ያሉ ብዙ ሀገሮችን ተዘዋውሮ ያየ ያውቀዋል። በብዙ ሀገሮች የቅኝ ገዢዎቹ አሻራ ጎልቶ ከመታየቱም በላይ ዙራያቸውን ከበው ጃስ እያሉ እና መሳሪያ እያስታጠቁ እንደ ውሻ የሚያፋልሟቸውን እና ሲሻቸው መሀል እየገቡ ገላጋይ መስለው የሚዳኟቸውን የቀነጨሩ የአፍሪቃ ልሂቃን እየተጠቀሙ ዛሬም አህጉሪቱ ከነሱ መዘውር እንዳትወጣ አርገዋታል። አንድ የደቡብ አፍሪቃ ተወላጅ የሆነ የሕግ ባለሙያ ቅኝ ግዥው በእጅ አዙር መቀጠሉን ጥሩ አድርጎ እንዲህ በማለት ገልጾታል፤  “ቅኝ ገዢዎቻችን የታሰርንበትን ሰንሰለት ከአንገታችን ላይ ቢያወልቁትም እግራችን ላይ አስረውታል። አንገታችን ነጻ ቢሆንም እግራችን እንደታሰረ ነው።” ይህን የተናገረው ደቡብ አፍሪቃ ከአፖርታይድ ከተላቀቀች ቡዙ አመታት በኋላ ነበር።

የሚያሳዝነው በቅኝ ግዛቱ ዘመን ለምዕራባዊያኑ ወረራ እጅ ያልሰጠችው እና በነጻነቷም ተከብራ የኖረችው ኢትዬጵያ በድህረ ቅኝ ግዛቱ ዘመን (ዛሬን ጨምሮ) ምዕራብ ነዳሽ በሆኑ ጭንጋፍ ልሂቃን እጅ ወድቃ ከሌሎች የአፍሪቃ አገሮች ተርታ መሰለፏ፤ ሊያውም በሚዘገንን ሁኔታ እንደ ሀገር የመቀጠል እጣ ፈንታዋን በሚገዳደር ደረጃ የዳግም ቅኝ ግዛቱ በትር አርፎባታል። ጸባችንንም እርቃችንንም የሚፈተፍቱልን ምዕራባዊያን መሆናቸው ያሳለፍነው ሁለት አመታት እንኳ ጥሩ ማሳያ ነው።

የቀዝቃዛው ጦርነት እንዳበቃ እነ ክሊንተን አራቱ ወጣት ትውልድና እና ተራማጅ የአፍሪቃ ቀንድ መሪዎች (the Young Generation and  Progressive Leaders)  ብለው ሁኔታዎችን አደላድለውና ደግፈው ወደ ስልጣን ያመጧቸው የድህረ ቅኝ ግዛቱ አመቻች መሪዎች፤ መለስ ዜናዊ፣ ኢሳያስ አፎርቄ፣ ዬሪ ሙሴቪኒ እና ፖል ካጋሜ ላለፉት ሦስት አሥርት አመታት ቀጠናውን ሲያተራምሱት ቆይተዋል። ከመለስ በሞት መለየት በቀር የቀሩት ሦስቱ ዛሬም የቀጠናው አለቆች ናቸው።  በመለስ የሙት መንፈስ የምትመራው ኢትዬጲያ ዛሬም እሱ ቀብሮ በሄደው አደገኛ እና ከፋፋይ የዘር ፖለቲካ እና ዘረኛ ሕገ መንግስት ፍዳዋን እየበላች ነው። መለስን የተኩት አቶ ጏይለማሪያም የምሪት ውሉን ስለማያውቁት ‘የመለስን ሌጋሲ አስጠብቃለሁ’ ብለው በመማል ነበር ሥልጣናቸውን የተረከቡት። የተነገራቸውንም ሲፈጽሙ ቆይተዋል። ምዕራባዊያኑ ለመለስ ያደርጉ የነበረውን ድጋፍ የሥልጣን ዱብዳ ለወደቀበት ጏይለማርያም ደሳለኝም እንዲሁ ሲያደርጉ ቆይተዋል። 100% ገዥው ፓርቲ ያሸነፈበትን ምርጫ ሳይቀር ፕሬዝደንት  ኦባማ ከእነረዳታቸው አዲስ አበባ ድረስ መጥተው እየተሳለቁ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ተካሂዷል ብለውና ቡራኬ ሰጥተው የሄዱት የዳግም ቅኝ ግዥው ውል ማጥበቂያ ነበር።

ኢትዬጲያ ዛሬም በመለስ ሌጋሲ እየተጋለበች ያለች አገር ነች። መለስ ተክሎ የሄዳቸው ሁለት መርዞች፤ አደገኛው ሕገ መንግስት እና የዘር ፖለቲካ ሕዝቧን እርስ በርስ እያጠፋፋ እና አገሪቱም መለስ በአምሳያው በቀረጻቸው ብሔረተኞች እየታመሰች ትገኛለች። ዛሬ ኢትዬጵያን የሚያስተዳድሩት፣ በግራና በቀኝ ተቧድነው የተሰለፉት፣ ሕዝብን በማያቀው ጉዳይ የሚያፋጁት ጭንጋፍ ካድሬ ፖለቲከኞች የመለስ የፖለቲካ የበኩር ልጆች ናቸው።

አብይ፣ ደብረጺዬን፣ ጌታቸው፣ ሬድዋን እና በዙሪያቸው ያሉ ፖለቲከኞች ሁሉ በመለስ የፖለቲካ ቅኝት የተቀረጹና መለስ የፖለቲካ ሀ ሁን ያስተማራቸው፣ በራሱ እሳቤ ያሰለጠናቸው እና በዘር ፖለቲካ የተቃኘው የአቢዬታዊ ዲሞክራሲ ፍሬዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ትላንትም ዛሬም ጓደኛሞች ናቸው። በሰላም ድርድሩ ላይ እርቅ መውረዱ እጅግ በጣም ያስደሰተኝን ያህል ትላንት አብረው የኢትዬጵያን ሕዝብ ሲያሽቆጠቁጡ፣ ግፍ ሲውሉበት፣ መብቱን ሲጥሱ የነበሩት ጓደኛሞች እሬድዋን እና ጌታቸው በመቶ ሺዎች አስከሬን ላይ ቆመው እጅ ለጅ ሲጨባበጡ ሳይ እውነት እውነት እላችኋለው በተቀመጥኩበት አጥወለወለኝ፣ አንዳች ነገር ተናነቀኝ። እንደውም ለራሴ ምናለ የሚጨባበጡትና ሰነዱ ላይ የሚፈርሙት ሌሎች የማናውቃቸው አዳዲስ ሰዎች ቢሆኑ አልኩኝ። ማፈር ድሮ ቀረ ነው ያሉት ኘ/ር መስፍን፤ አዎ ካድሬ እፍረት አያውቅም ብዬ እነሱን ማሰብ ትቼ የጓጓሁለት የሳም ድርድር ላይ አተኮርኩ።

ኢትዬጵያ ባለፉት አስርት አመታት ውስጥ ያስተናገደቻቸው ደም አፋሳሽ ጦርነቶች የምዕራባዊያን እና የነሱ ፈረስ የሆኑ የጭንጋፍ ፖለቲከኞቿ ዱለታ ውጤቶች ናቸው። ዱሮም ጥርስ የገባች አገር የተባለችው ያለምክንያት አልነበረም። ዛሬ ጥርሶቹ ሹለው እና አግጠው የመጡ ይመስላል። የምዕራባዊያኑም ከአገር ውስጥ አገር የማዋለድ ፖለቲካ መልኩን እየቀያየረ ዛሬም ኢትዬጲያን እየተፈታተናት ነው።

የወያኔ አመራሮች ከመነሻቸውም ከአገር ውስጥ አገር ሆኖ የመውጣት የነጻ አውጭ ቅኝት የያዘ ትልም ስለሆነ ያላቸው ይህን ቅዠታቸውን እውን ለማድረግ እስከ ሲኦል እንደሚወረዱ ምንም ሳያፍሩ ነው ባደባባይ የነገሩን። የኦነግ ሽኔ አይነት  እነሱን መሰል ሃይሎች አሰልፈው ኢትዬጲያን ሊቀራመቱ ከበዋታል። ሕዝቧንም በአለም ተሰምቶ የማያውቅ ግፍና መከራ እያዘነቡበት ነው። በተቃራኒ የቆመውና አገሪቱን የሚያስተዳድረው ጏይልም በመለስ ሌጋሲ የተቃኘ፣ አገር በማፍረስ ቅኝት የተዋቀረውን ሕገ መንግስት የሙጥኝ ያለ እና አገር አንድ አድርጎ የመምራት ፍላጎት ቢኖረውም እንኳ ግራ የተጋባና ውሉ የጠፋው ይመስላል። አባቶቻችን አሳፍረው የመለሷቸው ቅኝ ገዢ ምዕራባዊያን ኢትዬጲያን በከሸፉ ሊህቆቿ እየታገዙ ይሄው ለሰላሳ አመታት እየዘወሯት እዚህ ደርሰናል።

‘አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም’ አለ፤ የአፍሪቃ ችግሮች ተመሳሳይ ናቸው። ነጻ ቢወጡም ነጻ ባልወጡ ካድሬዎች ቅኝ ስር ናቸው።  የሁሉም የአፍሪቃ አገራት ችግሮች የሚመነጩት በዘር ከተቧደኑት፣ በሙስና ከተካኑት፣ ከእውቀት ከራቁት፣ በራሳቸው ፍቅር ከወደቁት ጭንጋፍ ፖለቲከኞች እና እነሱን በገንዘብ እየደለሉ አህጉሩን በሚዘርፉትና በእጅ አዙር ዳግም ቅኝ ግዥን ከሚያራምዱት የአለም ጏያላን የሚመነጩ ናቸው። ብዙዎች በአዲሷ የአለም ጏያል አገር ቻይና እና በተቀረው የምዕራቡ አለም መካከል ልዩነትና የጎራ መከፋፈል ያለ ይመስላቸዋል። እውነታው ግን ያ አይደለም። የቻይና መምጣት የዳግም ቅኝ ገዢ ሃዬሎችን ሌላ የመዝረፊያ መንገድ ነው የጠረገላቸው። ቻይና ከአፍሪቃ የምትመዘብረውን ጥሬ ሀብት ወደ ፋብሪካ ምርት ቀይራ ለገበያ የምታቀርበው ለምዕራባዊያኑ ነው። የቻይና ትልቁ የገበያ አቅርቦት ያለው የአሜሪካና የአውሮፓ ገበያ ላይ ነው። አሜሪካና አውሮፓ ያሉ ከትንሽ እስከ ትልቅ ደረጃ ያላቸው ገበያዎች የተሞሉት በቻይና ዕቃዎች ነው። ጥሬ ዕቃው ደግሞ ከአፍሪቃ። ለዱሮዎቹ ቅኝ ገዢዎች ስራ ነው የቀነሰላቸው።

ለማንኛውም የአፍሪቃ ሕዝብ ድህነት፣ እርሃብ፣ የአቅርቦት እጥረት፣ ግጭት፣ ጦርነት፣ ስደትና እንግልት ምንጩ ከላይ እንዳልኩት አንድ ጉድጓድ ነው። የምዕራባዊያን የማያባራ የጥቅም ፍላጎት እና የአፍሪቃ ጭንጋፍ ወይም የቀነጨሩ ልሂቃን የፖለቲካ መዘውሩን የሙጥኝ ብለው በጏይል መያዛቸው ነው። አህጉሪቱን ላልተወሰነ ጊዜ ሊነጋጋ በሚመስል ጭለማ ውስጥ እንድትቆይ አድርጓታል። የአፍሪቃ ምሁራን፤ እወነተኞቹን ማለቴ ነው የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ከፍለው የምዕራባዊያንን ቅኝ ግዢ እንዲያከትም የታገሉትን ያህል አሁንም አህጉሪቱን ከካድሬዎች ቅኝ ነጻ ለማውጣት በፓን አፍራቃዊነት ስሜት  ካልታገሉ ርሀቡም፣ ጦርነቱም፣ ዝርፊያውም፣ ሙስናውም ተጧጥፎ ይቀጥላል። የዳግም ቅኝ ግዛቱም ልጓም ይጠብቃል። የአፍሪቃ ሕዝብ ከባርነት ተላቆ የሥልጣን ባለቤት የሚሆንበት ዘመንም ይርቃል።

አፍሪቃ ከእጅ አዙር ወይም ድህረ ቅኝ ግዛት ነጻ ልትወጣ የምትችለው በእውነተኛ ምሁሮቿ ትግል ብቻ ነው። ትግሉም ከምዕራባዊያን ጋር ሳይሆን ከራሷ የቀነጨሩ ልሂቃን ጋር ነው።

ቸር እንሰንብት!

Filed in: Amharic