>

በአንድ ክስ ሦስት ጊዜ የዋስትና ገንዘብ በመጠየቅ 140 ሺህ ብር የከፈለው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በመጨረሻም ተፈቷል...!

በአንድ ክስ ሦስት ጊዜ የዋስትና ገንዘብ በመጠየቅ 140 ሺህ ብር የከፈለው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በመጨረሻም ተፈቷል…!

ዶችዌሌ


የፍትሕ መፅሔት ባለቤትና ማኔጂንግ ኤዲተር ተመስገን ደሳለኝ ከ6 ወራት እስራት በኋላ ዛሬ በ30 ሺሕ ብር ዋስትና ተፈታ።ጋዜጠኛዉ የታሰረዉ “የሐገር መከላከያ ምስጢሮችን ማውጣት ፣ ሐሰተኛ መረጃዎችን ለሕዝብ ማሰራጨትና ለወንጀል ማነሳሳት” በሚሉ ሶስት የወንጀል ጭብጦች ተከስሶ ነዉ። ጋዜጠኛው መጀመሪያ በ10 ሺህ ብር፣ ቀጥሎ በ100 ሺህ ብር ዋስትና እንዲለቀቅ ፍርድ ቤት ቢወስንም ውሳኔው  እስከ ዛሬ ድረስ ተፈፃሚ አልሆነም ነበር።ትናንት አዲስ አበባ ያስቻለዉ ፍርድ ቤት ለሦስተኛ ጊዜ በ30 ሺህ ብር ዋስትና እንዲወጣ የሰጠዉ ትዕዛዝም ትናንት  ሳይፈታ ማረሚያ ቤት አድሮ ዛሬ ከቀትር በኋላ መለቀቁን ታናሽ ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ ተናግሯል።

ተመስገን ከዚሕ ቀደምም  በመጽሔት በሚያትማቸዉ ጽሑፎቹ ምክንያት በተደጋጋሚ ለእሥር ተዳርጓል። ተመስገን የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ሥልጣን ከመያዙ በፊት በነበረዉ የኢሕአዴግ የአስተዳደር ዘመንም በጋዜጠኝነት ሙያው ምክንያት ለረጅም ዓመታት ተፈርዶበት በእሥር ላይ የቆየ ጋዜጠኛ ነው።

ትናንት የዋስትና መብቱ በፍርድ ቤት ተከብሮለት ሳለ ታሥሮ የነበረበት የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እንደማይፈታው ሲያስታዉቅ ጋዜጠኛ ተመስገን “ፍርድ ቤት ፈትቶኛል፣ ከዚህ በኋላ እኔ ላይ ለሚፈጠረው ነገር ኃላፊነቱን የሚወስደው ማረሚያ ቤቱ ነው።»ማለቱን ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ ለዶቼ ቬለ ተናግሯል።

ኢትዮጵያ ዉስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፍርድ ቤቶች በዋስ ይሁን በነፃ የሚለቋቸው ተከሳሾች ወይም ተጠርጣሪዎች አንድም ፖሊስ ፣ አለያም ማረሚያ ቤቶች እንዳሰሩ ሲያቆዩቸዉ ማየት እየተለመደ ነዉ።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ትናንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ “የፍትሕ ሥርዓቱ ሥብራት ትልቅ ነው። ፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ሰፊ ችግር አለ” ብለው ነበር። “ዐቃቤ ሕግ፣ ዳኛ ፣ ፖሊስ ሆነው በገንዘብ አንሠራም የሚሉ ሰዎች አሉ ። ነገር ግን እንደነዚህ ያሉ በእውነት የሚሰሩ ሰዎች እንደ ሞኝ እየታዩ ነው።ይሰደባሉ።» ብለዋል።ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለዉም «በቴሌግራም ጭምር ቡድን ከፍተው ጉቦ የሚቀባበሉ ዳኞች አሉ። የፍትሕ ሥርዓቱ መሻሻል ካለበት ጊዜው አሁን ነው ጠንካራ ለውጥ ያስፈልጋል” ማለታቸዉን የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ሰለሞን ሙጬ ዘግቧል።

Filed in: Amharic