ከመልካም ዜናው ባሻግር
የፍትሕ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሪክተር እውቁ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከስድስት ወር እስር በኋላ ከማረሚያ ቤት እስር ህዳር 7 ቀን 2015 ዓ.ም. መፈታቱን ከማህበራዊ ድረገጽ አንብቤአለሁ ፡፡ በእውነቱ ለመናገር ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ለሚያሳስባቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ መ ልካም ዜና ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ተመስገን ከእስር ከተፈታ በኋላ ሌላ ተግዳሮት ይገጥመዋል ብዬ በብርቱ እሰጋለሁ፡፡ ይሀውም የህትመት ዋጋ ሰማይ መንካቱ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ተግዳሮት የተመስገን ብቻ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ምድር በህትመት ሚዲያ ላይ ለተሰማሩ ጋዜጠኞች ሁሉ ራስ ምታት ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ የፍትሕ መጽሔት፣የሓበሻ ገጽ መጽሔት፣ጊዮን መጽሔት፣ አዲስ ግዜ መጽሔት መታተም ካቆሙ ወር ሊሞላቸው ነው፡፡ ከወር በፊትም ቢሆን ህተመታቸው ወጣ ገባ ነው፡፡ መጽሔቶቹ መታተም ያቆሙት ደግሞ በህትመት ዋጋ ንረት ነው፡፡
ዳቦ ለብዙሃኑ ብርቅ በሆነበት ሀገር መጽሔት በ50 ብር ገዝቶ ለማንበብ የማይታሰብ ነው፡፡ የመጽሔቶቹ አዘጋጆች ከፍተኛ ጥረት አድረገው፣ እንዲሁም ተቸግረው፣ መጽሔት አዟሪዎች ከአንዲት መጽሔት 2 ብር ትርፍ እያገኙ በ40 ብር ዋጋ ሲሸጥ የነበሩት መጽሔቶች ወደ ሃምሳ ብር ሊገቡ ነው በሚል መጽሐየቶቹ መታተም አቁመዋል፡፡ በእውነቱ ያሳዝናል፡፡ የታደሉት በየቀኑ በመቶ የሚቆጠሩ መጽሔቶችን በሚያነቡበት አለም ኢትዮጵያውያን በሳምንት ሶስት በነጻነት የተጻፉና የታተሙ መጽሔቶችን ለማንበብ አለመቻላችን ሲታሰብ አድላችንን አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡
ነገሩ ሂድ አትበለው እንዲሄድ ግን ሁኔታዎችን አመቻችለት እንዲሉ መሆኑ ነው፡፡ ለማናቸውም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የሚያሳስባችሁ ባለወረቶች እና አንባቢዎች፣ እንደ አሽን የፈሉት የሲቪል ማህበራት የየበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ በዚህ አጋጣሚ አስታውሳለሁ፡፡ ከዚህ ባሻግር ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዲከበር ሁነኛ ሚና ያለው መንግስት የሕትመት ዋጋ እንዲቀንስ ሃላፊነት ስላለበት ሚናውን እንዲወጣ እማጸናለሁ፡፡ በመጨረሻም የነጻው ፕሬስ የሕትመት ባለቤቶች የተናጥል እሩጫችሁን ገታ በማድረግ ቢያንስ የሕትመት ዋጋ ስለሚቀንስበት መንገድ ቁጭ ብላችሁ እንድትመክሩ በማሳሰብ እሰናበታለሁ፡፡