>

ስለ ወልቃይት ጉዳይ ያስገረመኝን ታሪክ ላካፍላችሁ፦ (ስንታየሁ ቸኮል)

ወልቃይት በትግራይ አንገት ላይ የተጠለቀች ገመድ ናት፤

ስንታየሁ ቸኮል

ስለ ወልቃይት ጉዳይ ያስገረመኝን ታሪክ ላካፍላችሁ፦

እኔና እስክንድር በ2013 ዓ.ም ቃሊቲ ወህኒ ቤት ዞን-1 በነበርንበት ወቅት የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ወደግቢ መጥተው ተቀላቅለውን ነበር። ከእነዚህ ውስጥ ዋናዎቹ ስብሃት ነጋን ጨምሮ አባዲ ዘሙ፣ አባይ ወልዱ፣ አዲስአለም ባሌማ፣ ቴዎድሮስ ሀጎስ፣ ፍሬወይኔ አሰፋ እና ሌሎችም ነበሩ።

ብዙም መነጋገር ባይኖርም ጦርነቱ እየተፋፋመ ባለበት ጊዜ በስሱ ተነጋገርን። መግባባት ግን ኖሮ አያውቅም። ስለወልቃይት እና ራያ አማራዊ ማንነትና ወሰን ጉዳይ ጭቅጭቅ ተፈጠረ። “አማራ የተጫነበት ሕገ- መንግሥት ተብዬ ባልተቀየረበት ሁኔታ የወልቃይትና ራያን አንገብጋቢ ጥያቄ ሕዝቡ ለድርድር አያቀርበውም” አልኳቸው። “በዚህ ጉዳይ ሕዝቡን ከማባለት እውነታዉን ለምን አትናገሩም “ በማለት አንዱን ከፍተኛ አመራር ጠየቅኳቸው።

የሰጡኝ መልስ ዛሬም ድረስ ያስገርመኛል። “በትጥቅ ትግሉ ወቅት በወልቃይት ጉዳይ በጉባኤ በማዕከላዊ ኮሚቴ ተጨቃጭቀናል። ወልቃይት የአማራ መሬቶች እንደሆኑ እናውቃለን። ነገር ግን ወልቃይትን ሳንይዝ የምናስባት ትግራይ የለችም። ትግራይ አለመኖሯ ብቻ አይደለም፤ የምግብ ዋስትናችንም ማረጋገጥ አንችልም። አማራ ለም መሬቶች አሉት። ትግራይ ግን ያለወልቃይት አንገቷ ላይ ገመድ የተጠለቀባት ናት” አሉኝ።

ከእሳቸው ይህንን እውነት መስማቴ እጅግ ገራሚ  ነበር። አማራ የሚጠይቀውን ፍትሃዊ ጥያቄ እና ትክክለኝነት በሚገባ ያውቃሉ። ክምር የታሪክ ማስረጃ ፍለጋ ሩቅ ሳልሄድ ከእኚህ አዛውት አመራር አረጋገጥኩ። የተናገሩትን በትኩሱ በማስታወሻዬ አስፍሬዋለሁ። ሙሉ ታሪኩን እንደ ፈጣሪ ፈቃድ ለመፃፍ እሞክራለሁ።  አዛዎንቱ እንዳሉት ትግራይ ያለወልቃይት አንገቷ ላይ ገመድ እንደታሰረባት ከሆነች፤ ገመዱን ስትፈልግ ጌጧ፤ ስትሻ መታነቂያዋ   ታድርገው እንጂ የሌላ ቀምቶ መኖር በምድር ወንጀል፤ በሰማይም ኩነኔ ነው። በአምባጓሮ ለመኖር መሞከር በራሱ ወልቃይት በትግራይ አንገት ላይ የጠለቀች ገመድ ያደርጋታልና ሸምቀቁን ማጥበቅ ነው። አማራ “የምትበላው ስለሌለህ እኔን በልተህ ኑር” ብሎ ራሱን ለመስዋዕትነት የሚባርክ ከመሰለህ ተሳስተሃል።

የጣልያንም ፍላጎት ከአንተ ተመሳሳይ ነበር፤ ከእርሱ ተማር። ፋሽስት ኢትዮጵያን የወረረው “ሀገሬ ከህዝቤ ቁጥርና ፍላጎት ጋር የሚመጣጠን በቂ የተፈጥሮ ሀብት ስለሌላት የኢትዮጵያን በልቼ ልኑር” ብሎ ነበር። አልተሳካለትም!

ያም ሆነ ይህ ‘ወልቃይት የማነዉ?’ አትበል እንኳን  አማሮች  ሕወሓቶቹም ያውቁታል!

Filed in: Amharic