>

የኔ ዘመኗ ኢትዮጲያ፣ የነ አጅሬ ክልል ዐማራ ይህን ይመስላል.....! አርበኛ ዘመነ ካሴ  (ከባሕርዳር ማረሚያ ቤት)

የኔ ዘመኗ ኢትዮጲያ፣ የነ አጅሬ ክልል ዐማራ ይህን ይመስላል…..!

አርበኛ ዘመነ ካሴ 

(ከባሕርዳር ማረሚያ ቤት)

ለሚመለከተው ሁሉ… 

“…ላለፉት አስራ አንድ ዓመታት ነፃ፣ ፋትሃዊትና ደስተኛ ምድር ማየትን በልጅነቴ አልሜ በአቅሜ ከጭቆና ተራራ ጋር ግብግብ ገጥሜ ቆይቻለሁ። አሁንም ትንቅንቅ ላይ ነኝ። በሀገሩና በአድባሩ የተከበረ እና ነፃ ዐማራ፤ እንዲሁም በሁሉም ለሁሉም የሆነች ኢትዮጲያን እስካይ ድረስ ላፍታ እንኳን ረፍት ሳልሻ እቀጥላለሁ። በዚህ የተነሳም ፀረ- ዐማራና ፀረ- ኢትዮጲያ ኃይሎች ላለፉት አስራ አንድ አመታት ስምና ጃኬት ብቻ እየቀየሩ ሲያሳድዱኝ ቆይተው መስከረም 11-01-2015፧ ዓ.ም እጃቸው ላይ መውደቄ ይታወቃል። ከዚያ ዕለት ማግስት ጀምሮ ለስድስት (6) ጊዜ ፍ/ቤት ቀርቤያለሁ።

“…እውነት ለመነጋገር ከመጀመሪያው ቀን የፍ/ቤት ውሎ በኋላ ተመልሶ ችሎት ላይ የመቆም ጥፍር ታክል ፍላጎት አልነበረኝም። የመጀመሪያ ቀን የፍ/ቤት የተገኘሁትም ይህን አቋሜንና ፍላጎቴን ለመግለጽም ነበር። ይሁንና በወዳጆቼ ጉትጎታ እየተገፋሁ ሳዘግም ቆይቼ ዛሬ (16-03-2015) የመጨረሻውን የችሎት ውሎ አድርጌያለሁ። በዕለቱም በጠበቆቼ ሕጋዊ እና እውነተኛ ጥያቄ መሰረት ክሱ ውድቅ ይደረጋል ተብሎ ሲጠበቅ ተሻሽሎ እንዲቀርብ ብቻ ተወስኗል። የኔ ዘመኗ ኢትዮጲያ፣ የነ አጅሬ ክልል ዐማራ ይህን ይመስላል። ከጭቆና እና ግፍ ተራራ ጋር ግብግብ የገጠምኩት እውነተኛውን ነፃ አውጭ የናዝሬቱን እየሱስን የሰቀለች፣ ሶቅራጠስን መርዝ የጋተች፣ ጆርዳኖ ቡርኖን በሰም ለኩሳ ያቃጠለች እውነት የሚያቅራት ምድር ላይ መሆኑን ገና ድሮ ጠንቅቄ ስለማውቅ ቅንጣት ታህል አልገረመኝም።

“…የዐማራ ክልል መንግሥት በአጠቃላይ፣ የፍትሕ ሥርዓቱ በተለይ በጥቂት ግን በጥልቅ ተደራጅተው የፖለቲካ እና የመንግሥት መዋቅሩን በወረሩ ፍልፈል ኃይሎች የፊጥኝ ታስሮ ከወደቀ ቆይቷል። የክልሉ ዲፋክቶ (ውስጠ-ዘ) መሪዎችም እነዚሁ ኃይሎች ናቸው ማለት ይቻላል። ከዚህ ፍጥጥ ያለ እውነታ ላይ ተቋሙ ፍትህን መሻት ትልቅ ጅልነት ይሆናል።

“…ባለፉት አስራ አንድ ዓመታት በጎ ምኞት እውን ሆኖ ባይ ብዬ የአቅሜን ስሞክር እንኳን ወንጀል የጸጉር ስንጣቂ የምታክል ስህተት ሠርቼ አላቅውቅም። የተለየሁ ፍጥረት ሆኜ አይደለም፤ የድንግል ማርያም ልጅ ሁሌም አብሮኝ ስላለ እና ስለሚጠብቀኝ እንጂ። የሆነው ሆኖ ወንጀለኞች “ወንጀለኛ” ብለው ከሰውኝ እየተናነቀኝም ቢሆን እስከዛሬዋ ቀን ፍ/ቤት ተመላልሻለሁ። ዛሬ ግን ጨርሻለሁ። በቃኝ። ከዛሬ በኋላ ፍ/ቤት፣ ችሎት፣ ቀጠሮ ጂኒጃንካ እያልሁ የምሄድ የምመጣበት ቦታ አይኖርም። በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ምክንያት:-

(1) ዲሽቃ እና ስናይፐር ወድረው ፍ/ቤት አድርሰው የሚመልሱኝ ኃይሎች የሚታዘዙት እንድጠፋ ሌት ተቀን በሚሠሩ ግለሰቦች እና ከላይ የክልሉን ሁለንተና ተቆጣጥረዋል ባልኳቸው ቡድኖች ነው። ከነስጋቴም ቢሆን ፍ/ቤት ደርሼ የምመለሰው ከጠላት ጋር በሚዶልቱ አምስት ከማይበልጡ አባሎቻቸው ውጪ በማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች እና አስተዳደሩ ላይ እምነት ስላለኝ ብቻ ነው። ጠላቶቼ የሚያዙት ሃይል መቼ፣ የት፣ እና በምን ደቂቃ የሚያጅቡበትን ዲሽቃና ስናይፐር አፈሙዝ ወደኔ እንደሚያዞሩት እንኳን አላውቅም። ፍ/ቤት ደርሼ የምመለሰው በሞት ባቡር ተሳፍሬ ነው። ይህን የሚመለከት አቤቱታ ለከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ማቅረቤም ይታወቃል። ስጋቱ ግን እያየለ መጣ እንጂ አልቀነሰም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የማይገኝ ፍትህ ፍለጋ “ቀጠሮ” እያሉ መመላለስ የጠላት የመግደያ ወረዳ ውስጥ በገዛ ፈቃድ ሰተት እያሉ እንደመግባት በመሆኑ ከዚህ በኋላ ፍ/ ቤት አልቀርብም።

(2) የጥቂት ፍልፈል ኃይሎችና ማጅራት መቺዎች መጫወቻ እና ሸቀጥ በሆነ የፍትህ ሥርዓት ውስጥ “ፍትህ ይገኛል” ማለት የሞተ ፈረስ እየጋለቡ ሰባተኛው ሰማይ ድረስ ለመውጣት የመሞከር ያክል ቂልነት ወይንም እብደት ይሆናል። የማልክደው እና በፍ/ቤት ምልልሴ የታዘብሁት ነገር ችሎት ላይ ስቆም የዳኞችን ጭንቀት በግልጽ አይ ነበር። ሌላው ቀርቶ ከሳሽ ሆነው የሚቆሙት ዐቃቤ ሕጎች እንኳን ሲጨነቁ እና ግራ ሲጋቡ በዓይኔም በስሜቴም ታዝቤያለሁ። ግን ምን ዋጋ አለው? ዋናው ችሎት ያለው የአንዱ ካድሬ ቢሮ ውስጥ ነው። ዋናው ዳኛም ካድሬው እና የካድሬው ስልክ ነው። የታሰረው ዘመነ ብቻ አይደለም፤ በእሳት ሰንሰለት የታሰረው ዳኛውም ዐቃቤ ሕጉም ነው። ይህን ሰንሰለት መቼ? እንዴትና በምን አኳኋን እንስበረው? ይህ ዘመነ ብቻ ሳይሆን ዳኛውም ዐቃቤ ሕጉም እኩል መመለስ ያለባቸው ጥያቄ ነው። የፍትህ ሞት የህዝብና የሀገር ሞት ነውና። በኔ በኩል ሰንሰለቱ መሰበር ብቻ ሳይሆን መቅለጥ ያለበት ዛሬ ነው፤ እደግመዋለሁ ዛሬ!

“…ለማንኛውም የኔ ዘመን በድን የፍትሕ ጉዞ እና ድራማ ላይ ከዚህ በላይ ለመተወን ዝግጁ አይደለሁም። ኃጢአትም ነው። ስለዚህ ከዛሬ በኋላ የፍርድ ቤት ቀጠሮ አይመለከተኝም፤ ችሎት ላይም አልቆምም። አንድ ቀን እልቂት የታወጀበት የዐማራ ህዝብ እና ረፍት ያጣችው ሀገራችን ነፃ ሲወጡ እኔም ነፃ እወጣለሁ። ስለዚህ አሁን ሁሉም ትግሉ ላይ ብቻ ትኩረት ያድርግ።

“…ቀና አባቶቻችን እና ወንድሞቻችን ጉዳዩ ፖለቲካ ወለድ ክስ በመሆኑ በሽምግልና እንዲያልቅ ያደረጉት ጥረትም ውጤት እያመጣ አደለም። እንዲያውም ጠላቶቼ የሽምግልናውን እና የፍርድ ቤት ሂደቱን የጊዜ መግዣ እና ማዘናጊያ ሲያደርጉት ታዝቤያለሁ። ከፊሉ ሕዝብ የፍርድ ቤት ውሎ፣ ላይ ከፊሉ ደግሞ ሽምግልናው ላይ አጉል ተስፋ እንዲጥል ጆሮ ጠቢዎቻቸውን አሰማርተው በየጊዜው የዲስ ኢንፎርሜሽን ካምፔን በመክፈት አደገኛ ጊዜ እየገዙ ነው። ስለዚህ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ የምር የትግል ፍላጎትና ወኔ ያለው በሙሉ ትግሉ እና ትግሉ ላይ ብቻ ትኩረት ያድርግ። ወትሮም ቢሆን ከሞት ጋር ትከሻ ለትከሻ ስንጋፋ፣ አልፎም የሞትን አፍንጫ ለመያዝ ሳንደፍር ነፃ አንወጣም።

“…እነዚህ ሰዎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሀገሩን እሳት ጎርሶ እሳት ለሚተፋ አብዮት እያመቻቹት ነው። ይህ በእርጥብ የጭቆናና የግፍ ቆዳ የታፈነ ምድር የፈነዳ እለት የሚነሳው እሳት ፍጥረትን በሙሉ ይጠርጋል። ያገኘውን ይበላል። ያኔ እንኳን ህዝቡን የበደሉ ካድሬ መሆን፤ የካድሬ ዘመድ ሆኖ መገኘት ብቻ የተፈጠሩበትን ቀን ያስረግማል። ለማንኛውም ሁሉም ትኩረቱን ትግሉ ላይ ብቻ ያድርግ። እግሮች ሁሉ ወደ ትግሉ ሜዳ ይጓዙ። ወደ ትግሉ ሜዳ ይሩጡ። የዛሬ ህመማችን እና የውስጥ ለውስጥ እንጉርጉሯችን ነገ ህፃናት ሳይቀሩ በደስታ የሚዘምሩት የአደባባይ ብሔራዊ መዝሙር ይሆናል። እንበርታ ብቻ!!

“…በዚህ ትግል ውስጥ አስራ አንድ ዓመት ቆይቻለሁ። ለአስራ አንድ ሰከንድ እንኳን ተጠራጥሬ የማላቀው ነገር ቢኖር በመጨረሻ አሸናፊዎች እኛ መሆናችንን ነው። መንገዳችን የፍትሕ፣ የእኩልነትና የእውነት መንገድ ነው። ከእውነት ጋር እግዚአብሔር አለ። ከእግዚአብሔር ጋር ያለ ደግሞ ማሸነፉ አይቀርም። ጽናት፣ ብርታት እና ትእግስት ብቻ!!። እንበርታ! እንሰባሰብ፣ እንደብረት እንጠንክር።

• (ክፋት ለማንም በጎነት ለሁሉም)

• (አዲስ ትውልድ፣ አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ ተስፋ)

• ድል ለዐማራ ሕዝብ…!

ድል ለኢትዮጲያ ሕዝብ…! 

Filed in: Amharic