>

በመንግስት ስምሪት የሚሰጠው ኃይል በኪረሞ  ለ4ኛ ጊዜ የአማራ ተወላጆች ላይ  የግድያና  የማቁሰል አደጋ አደረሰ...! አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ 

በመንግስት ስምሪት የሚሰጠው ኃይል በኪረሞ  ለ4ኛ ጊዜ የአማራ ተወላጆች ላይ  የግድያና  የማቁሰል አደጋ አደረሰ…!

አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ

የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ከሚሊሾች፣ ከወጣቶች እና ከኦነግ ሸኔ አባላት ጋር በመሆን በኪረሞ ከተማ ለ4ኛ ጊዜ በአማራ አርሶ አደሮችና ሚሊሾች ላይ ሙሉቀን ጦርነት ከፍቶ መዋሉ እንዲሁም በርካቶችን መግደሉ እና ማቁሰሉ ተገለጸ።

የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ከአሸባሪው ኦነግ ሸኔ፣ ከሚሊሾችና ከወጣቶች ጋር በመሆን በኪረሞ ከተማ በታገቱ እና በአካባቢው ባሉ አማራዎች ላይ የተደራጀ ጦርነት ከፍቶ ውሏል፤ በርካታ ሰላማዊ አማራዎችን በማንነታቸው ብቻ እየገደለ እና እያሳደደ ውሏል ተብሏል።

የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ህዳር 9፣10 እና 11/2015 በኪረሞ እና አካባቢው ባሉ አማራዎች ላይ የተደራጀ ጦርነት በመክፈት ነዋሪዎች እንደሚሉት በትንሹ ከ50 በላይ አማራዎችን መግደሉ እንዲሁም ከ52 ሽህ በላይ የሚሆኑትን ወደ ሀሮ ማፈናቀሉ ይታወሳል።

ህዳር 13/2015 ከኦዳቡልቅ የተነሳው የኦሮሚያ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻና ወጣቶች በጃርዴጋ ጃርቴ ወረዳ ከጃርዴጋ በቅርብ ርቀት ሹልኬ አካባቢ ኬላ ሲጠብቁ በነበሩ አማራዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ከ5 በላይ ሲገደሉ 3 መቁሰላቸውም ይታወሳል።

በኦሮሚያ ልዩ ኃይል በኪረሞ በግፍ ከተገደሉት መካከል መሀመድ ከማል አንዱ ሲሆን ቤተሰቦችን በሙሉ አግተው ማስቀረታቸውን፣አቶ እስሌማን ይመር ከእነ ልጁ፣ አቶ አስናቀው ካሳው፣ አቶ ተመስገን መልክነውን እንዲሁም ህጻናትንና ሴቶችን ጨምሮ ከ280 በላይ አማራዎች ከህዳር 9/2015 ጀምሮ በኦሮሚያ ልዩ ኃይል እገታ ስር እንደሚገኙ ተገልጧል።

ህዳር 20/2015 ከጠዋቱ 2 ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ 12 ሰዓት ድረስ በገበሬው ላይ በከፈቱት ጦርነት በርካታ አማራዎችን መግደሉ እየተነገረ ነው።

ህዳር 20/2015 በኦሮሚያ ልዩ ኃይል ከተገደሉት በርካታ አማራዎች መካከል:_

1) ሙላቴ ብርሃን፣

2) ኡመር ካሳው፣

3) እባቡ ፈንታው የተባሉ እና ሌሎችም ይገኙበታል።

ህዳር 20/2015 ከቆሰሉት ከ10 በላይ አማራዎች መካከልም:_

1) የሚያምረው መልኬ፣

2) መሀመድ ሙስጠፋ፣

3) ሞገስ ተላይሁን፣

4) ታዴ የተባለ ነዋሪ እና ሌሎችም ይገኙበታል።

በተመሳሳይ 8 ተሽከርካሪ ሙሉ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ከነቀምት በአንገር ጉትን አልፎ ወደ ኪረሞ እና  ጊዳ አያና ወረዳ አንዶዴ ዲቾ ህዳር 20/2015 ሲጓጓዝ ማምሸቱን የአሚማ ምንጮች ተናግረዋል።

በኪረሞ፣ በአንዶዴ ዲቾ እና አካባቢው ባሉ አማራዎች ላይ ጥቃት ሊከፍት ስለሚችል አስፈላጊው ጥንቃቄ ሁሉ እንዲደረግ ጥሪ ቀርቧል።

ይህ በመንግስት ስምሪት የሚሰጠው ኃይል በሀሮ አዲስ ዓለም ተሻግሮ በንጽሁን ተፈናቃዮች ላይ ጥቃት ሊፈጽም ስለሚችል በአስቸኳይ የፌደራል ኃይል እንዲገባ፣ ጥንቃቄም እንዲደረግ ተጠይቋል።

Filed in: Amharic