>

በወለጋ የሚፈሰው ደም ይጣራል! (በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ)

በወለጋ የሚፈሰው ደም ይጣራል!

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

ሕዳር 22 ቀን 2015 ዓ.ም

አሻራ ሚዲያ ፣ ባህርዳር


በተደጋጋሚ ጊዜ መንግስት የንጹሓንን ጭፍጨፋ እንዲያስቆም የእኛን ፓርቲ ጨምሮ ጉዳዩ የሚያሳስባቸው ኢትዮጵያውያንና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጮኸዋል። ይኹን እንጂ መንግስት ትንሽ ግጭት በጎንደርና በሌሎች አካባቢዎች ላይ ሲደርስ ውግዘቱን፣ ዘመቻውንና ሚዲያውን ሲያጯጩህ ኹላችንም የመንግስትን አቅም፣ መቆርቆርና ጉልበት ዐይተናል። በኢሕአዴግ ድርጅቶች ጠላት ተብሎ የተፈረጀውን የአማራ ማኅበረሰብ ሕጻናትና እናቶችን መግደል በሕግም የማያስጠይቅ፣ በሚዲያም የማይወገዝ አልፎም በፈጣሪም ፊት የማያስቀጣቸው እስኪመስላቸው ድረስ ጭፍጨፋው በተለይ ላለፉት አራት ዓመታት ያለማቋረጥ ቀጥሏል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሚዳቋና ጥንቸል ማደን በሕግ የሚያስቀጣ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕጻናትንና እናቶችን መግደል እንደመብት የሚታይበት ሀገር ሆኗል። አንድ አርቲስት ሲሞት መሪዎች ሀዘናቸውን የሚገልጹበት እንጉርጉሮ በመገናኛ ብዙኃን በሚሰራጭበት ሀገር የሕጻናትና እናቶች አሰቃቂ ግድያና ጭፍጨፋ ግን በቅጡ “አዝነናል” እንኳን የማይባልበት ሀገር እየሆነ ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ “እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን?” እንዳለው መንግስትም “እኔ በወለጋ የሚታረዱ ንጹሓን ጠባቂ ነኝን?” የሚል ይመስላል።

ከሰሞኑ በምሥራቅ ወለጋ በጊዳአያና፣ ኪረሙና ሐሮ ቀበሌዎች በየቀኑ በሚባል ደረጃ የሚፈሰው ደም ብቻ የኢትዮጵያ ምድር ይህን ያህል ደም ተጠምቷልን? ያሰኛል፡፡ እሥረኞች ተገድለዋል፣ ንጹሓን በእምነት ቦታዎች ጭምር ተጨፍጭፈዋል፣ ብዙ ሺዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ስለዚህ

፩. መንግስት ለአካባቢው ልዩ ትኩርት በማድረግና በቂ የመከላከያ ኃይል በማሰማራት የንጹሓንን እልቂት በአፋጣኝ እንዲያስቆምና የአካባቢው ዘላቂ ሰላም እስከሚረጋገጥ ድረስ በኮማንድ ፖስት እንዲተዳደር በአጽንዖት እናሳስባለን፡፡

፪. ግጭቱ ከጊዜ ወደጊዜ መልኩን እየቀየረ የእርስ በእርስ ወደመሆን ከመሄዱ በፊት ያገባኛል የሚሉ አካላት በሙሉ ርብርብ እንዲያደርጉ አበክረን እንጠይቃለን፡፡

፫. እልቂቱን በዘላቂነት ለመፍታት ከአድሏዊነት በጸዳ መልኩ የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማወያየትና ችግሩን በጥልቀት በመረዳት የመፍትሔ ሀሳብ እንዲፈለግ እንጠይቃለን፡፡

በመጨረሻም ኢትዮጵያዊ ነኝ፣ የንጹሓንን መታረድ ዝም ብሎ ማየት ኃጢያትም ወንጀልም ነው ብሎ የሚያስብ ኢትዮጵያዊ ኹሉ የእነዚህን በየቀኑ የሚታረዱ ኢትዮጵያውያን ወገኖቹን ለመታደግ በሕሊናም በፈጣሪም ፊት ከተጠያቂነት ለመዳን በመወያየትና መፍትሔ እንዲፈልጉ፤ በኦሮምያ ክልላዊ መንግስትና በፌዴራል መንግስት ላይ ጫና እንዲያደርጉ፤ ድርጊቱንም እንዲቃወሙ እየጠየቅን የንጹሓን ደም በከንቱ መፍሰስን ማስቆም የሚችለው ሕሊና ያለው ሕዝብና ፈጣሪ ብቻ መሆኑን ተረድተን ኹላችንም የምንችለውን እንድናደርግ እናት ፓርቲ ጥሪውን ያስተላልፋል። በድጋሚ ፓርቲያችን በንጹሓን ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልጻል፤ ለሟች ቤተሰቦችም መጽናናትን ይመኛል፡፡

ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ

እናት ፓርቲ

ሕዳር ፳፪ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

Filed in: Amharic