>

የአርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ (ባባ) ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ (አ.ሚ.ማ)

የአርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ (ባባ) ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ

አ.ሚ.ማ

የአርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ (ባባ) ሥርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዛሬ ተፈጽሟል…!

የታሪኩ ብርሀኑ የህይወት ታሪክ

አርቲስት ታሪኩ ለብቻው መብላት የማይወድ ወገን ጓደኞቹን ሰብሳቢ ትንሽ ትልቁን አክባሪ እንደነበር በወዳጅ ዘመዶቹ ተመስክሮለታል።

የአርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ ቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴ እንዲሁም ወዳጆቹ  አርቲስቱን በሚመለከት በማህበራዊ ትስስር ገፅ ላይ የሀሰት መረጃዎችን  በማስተላለፍ ላይ ያሉ ግለሰቦች ከድርሂታቸው እንዲቆጠቡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።

በተወለደ በ38 አመቱ ትናንት ያረፈው አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበር ሲል ኢፕድ ዘግቧል።

የታሪኩ ብርሀኑ የህይወት ታሪክ

ከአባቱ አቶ ብርሃኑ አምባው ከእናቱ ወ/ሮ አባይነሽ ክብረት በአዲስ አበባ ፣ በተለምዶ ተክለሃይማኖት ጅምናዚየም ተብሎ በሚጠራው ሠፈር በ1977 ዓ.ም ተወለደ ።

ዕድሜው ለትምህርት እንደደረሰ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በባልቻ አባነፍሶ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማረ :: በመቀጠል ወደ ቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች ተክኖሎጂ ኢንስትቲዩት (ሌዘር ኤንድ ሌዘር ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት) በማምራት በሌዘር ቴክኖሎጂ ዲፕሎማውን አግኝቷል።

በትምህርት በነበረበት ወቅት በኢንስትቲዩት አስተማሪዎች ተወዳጅ ተማሪ እንደነበረ የተቋሙ መምህራኖች እና ባለሙያዎች የሚመሠክሩለት ተማሪ ነበረ ።

አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ የጥበብ ህይወት ጉዞ የጀመረው በአበቦች የትያትር ክበብ የነበረ ሲሆን ይህን ጅማሬውን እንዲያብብ እና ከፍታ ያወጣለት ዘንድ በአርቲስት ዶ/ር ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) እግር ስር ቁጭ ብሎ የቴአትርን ሀ..ሁ የቆጠረ ሲሆን ለስኬቱ ይረዳውም ዘንድ በተለያዮ ጊዜያት የፊልም እና የቲአትር ኮርሶችን ወስዷል ።

አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ /ባባ/ በፀርሀ ፅዮን ጎላ ቅዱስ ሚካኤል ሰንበት ትምህርት ቤት አባል ሆኖ ባገለገለበት ጊዜ ዋዜማ ፣መንገደኛው እና የይቅርታ ዘመን የተሠኙ የሙሉ ጊዜ መንፈሳዊ ፊልሞችን ሰርቷል ።

በአበቦች የቴአትር ክበብ ባይተዋር የተሰኘ ቴአትር ሰርቷል እንዲሁም በቀንዲል ቤተ ተውኔት በተለያዮ የጥበብ ዝግጅቶች አቅሙን አሳይቷል። ከነዚህ በኋላም ወደ ስኬት ጉዞ የወሰደውን የፊልም ህይወት በዋና ገፀባህሪ የተሣተፈበትን ላውንደሪ ቦይ የተሠኘውን ፊልም አበረከተ።

በላውንደሪ ቦይ የጀመረው የፊልም ጉዞ ባላገሩ ሕይወትና ሣቅ ወንድሜ ያዕቆብ የፍቅር ABCD እና በተለያዩ የሀገራችን ፊልሞች ላይ በድንቅ ብቃት በመተወን በተለይ ደግሞ በወጣቶች ዘንድ እጅግ የሚወደዱ ከስልሣ በላይ ፊልሞች ላይ የተወነ ሲሆን ከስራዎቹም ጥቂቶቹ እነዚህ ይገኙበታል ::

ወጣት በ97፣ ላውንድሪ ቦይ፣ ማርትሬዛ፣ ይመችሽ-የአራዳ ልጅ 2 ፣ሞኙ የአራዳ ልጅ 4፣ አንድ ሁለት ፣ብር ፣ ወደው አይሰርቁ፣ ወፌ ቆመች፣  እንደ ቀልድ ወቶ አደር ፣አባት ሀገር የሞግዚቷ ልጆች፣  ይዋጣልን ፣ዋሻው፣ ወሬ ነጋሪ እና ሌሎችም ፊልሞች ላይ ተውኗል።

በነዚህ ስራዎች እያበራ የደመቀው አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ /ባባ/ የጥበብ ህይወቱ በተለያዮ ሽልማቶች የደመቀ ነበር ከነዚህ ውስጥ አዲስ ሚውዚክ አዋርድ እና በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 የለዛ  የዓመቱ ምርጥ ተዋናይ ሆኖ የተሸለመበት እና በጉማ አዋርድ ኢንተርናሽናል የፊልም ፌስቲቫል ለእጩነት እና ለሽልማት የበቃበት የሚጠቀሱ ስኬቶቹ ነበሩ ።

ከጥበብ ህይወቱ ባሻገር በተለያዮ የማህበራዊ ሕይወት በትህትናው እና በለጋስነቱ የሚታወቀው አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ /ባባ/ የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበረ ።

አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ /ባባ/ በህይወት በነበረበት ዘመን በሀገራችን አሉ ከሚባሉ ውድ ተከፋይ የጥበብ ሰዎች ተርታ ይመደብ የነበረ ቢሆንም ከነብሱ ጋር የተጣበቀው ደግነት እና ፍፁም ቸርነት ለኔ ይድላኝ እንዳይል አድርጎት በክፍያ ያገኘውን ገንዘቦች እንኳን በበጎነት ለአካባቢው ሰዎች እየለገሠ የኖረባትን ጥቂት ዘመን በምርቃት እና በመልካም ምግባር አሳልፎ የግል ህይወቱን ለሌሎች የሠጠ ድንቅ ባህሪ የነበረው ወጣት ነበረ ።

አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ በየእለት ውሎው በተገኘበት ቦታ ሁሉ ህፃን አዋቂ ሳይል በፍቅር እና በመረዳዳት ሲያሳልፍ ኖሯል። ለጓደኞቹ እና ለሰፈሩ ሰዎች ሁሉ በችግራቸው ቀድሞ በመድረስ ይታወቃል በተጨማሪም በአካባቢው ከሚገኙ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንደ CBCDO  ሲደርታ እና ሰዋዊ የጎ አድራጎት ማህበር  ወዘተ የመሣሠሉት ላይ በበጎ ፍቃድ በመሣተፍ በነበረው እውቅና እንደ አምባሳደር በማገልገል ለላይብረሪ ከ500 በላይ መፃህፍትን በማሠባሠብ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን አቅመ ደካሞችን በመደገፍ በጎ ተግባሮች ላይ በፊት አውራሪነት ተሣትፎ ነበረው ።

በተጨማሪም አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ /ባባ/ በጎ ስራውን የጀመረው ከእውቅናው በፊት ሲሆን በ2000 ዓም በ 23 አመቱ ለኢትዮጵያ የዓይን ባንክ በሰጠው ኑዛዜ መሠረት ህይወቴ ከዚህች ዓለም ድካም ሲያርፍ ሁለቱን ዓይኖቼን በህይወት ኖረው ማየት እክል ላጋጠማቸው ወገኖቼ በነፃ እንዲወስዱ ብሎ ለግሧል።

አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ ባጋጠመው የጤና እክል በተለያዮ ጊዜያት በህክምና እና በፀበል እራሡን ሲያሳይ የነበረ ቢሆንም በ ታህሳስ  02 2015ዓም ከዚህ ዓለም ድካም አርፏል ።

Filed in: Amharic