በ በአጸደ ስጋ…!
(በእውቀቱ ስዩም)
ሰው ሟች መሆኑን መርሳት የሚፈልግ ፍጡር ነው፤ ስልጣኔ ደግሞ ለጊዜውም ቢሆን ሞትን ያስረሳል፤ በአውሮፓ በአሜሪካ በጃፓን ኮረና እስኪመጣ ድረስ ሞትን የሚያሳስብ ነገር አልነበረም፤ የመቃብር አጸዶች እንኳ እጀግ ውበ ከመሆናቸው የተነሳ የፍርሀት እና የተስፋ መቁረጥ ስሜት አይቀሰቅሱም፤ ስልጡን ማህበረሰብ ሞትን ማስቀረት ባይችል እንኳ ማዘግይት ችሏል፤
በአገራችን የተለየ ነው፤ ሞት የማይንጸባረቅበት የኑሮ ዘርፍ የለም፤ ስንምል “ አባቴ ይሙት ፤ እናቴ ትሙት “ እንላለን፤ ስናጋብዝ “ በሞቴ ! አፈር ስሆን “ ብለን እንለማመጣለን፤ ራሳችንን ስንወቅስ “ ሞት ይርሳኝ “ እንላለን፤ ስንጸልይ ፤ “ አሟሟቴን አሳምርልኝ” እንላለን፤ አኗኗሬን አሳምርልኝ ሲባል ሰምቼ አላውቀም፤ ከልደታችን እና ከሰርጋችን ቀብራችን ይደምቃል፤ አንድ ሰው በሕይወት ያለን ሰው ካሞገሰ ወይም ካመሰገነ ድሮ “ እበላ ባይ “ ይባል ነበር፤ ዘንድሮ “ አሽቃባጭ “ የሚል ስም ይቀዳጃል፤ የሞተውን ማወደስ ግን የዜግነት ግዴታ መስሏል፤ በሕይወት መወደስ ፐርሰናሊቲ ከልት “ አሰኝቶ ያስወነጅላል፤ በሕይወት ዘመኑ ሀውልት የተሰራለት፤ መንገድ የተሰየመለት ትልቅ ሰው አይታችሁ ታውቃላችሁ? መንገደኞቻችን ረጃጅም መካነ መቃብሮች ሆነዋል፤
የፖለቲካ አስተዳደሮቻችን ለህይወት ያበረከቱት ነገር ጥቂት ነው፤ ባንጻሩ የሞት ፋብሪካ መሆናቸውን ታዝበናል፤ የመስዋአት አምልኮ ተነስራፍቷል፤ የአገረሰቡም ሆነ የብሄረሰቡ መዝሙር “ ስለ ደም ማፍሰስ እንጂ ስለ ደም መለገስ “ አይደለም፤ የሚሞት እና የሚገድል እንጂ፥ የሚኖርና የሚያኖር እንደ ጀግና አይታይም፤
በሀኪም ስተት ከሞተው ይልቅ በአስተዳደር ስህተት የሚያልቀው ይበልጣል፤ ያም ሆኖ ፥ ቆም ብሎ የመጣንበት መንገድ አያዋጣም ለማረም የሞከረ የለም፤
ባጭሩ፥ የሞት አገር ነው በውቄ! በዚህ ሁኔታ ውስጥ፥ ሕይወትህን መንዘንጋት ቀላል ነው፤ ጌታ ኢየሱስ ፥ ነቢዩ መሀመድ ሀዋርያው ጳውሎስ እንደነገሩን ከዚህ የተሻለ አለም አለ፤ ጌታ ኤፌቅሮስ እንደ ነገረን ደግሞ ይህ አለም የመጀመርያውም የመጨረሻውም እድላችን ሊሆን ይችላል ፤ እና በተቻለህ መጠን፤ ለመኖር ተፍጨርጨር፤ ለበጎ ምግባርህ ምድራዊውም ሆነ ሰማያዊ ሽልማት ሳትጠብቅ በጎ ሁን! ከቅኔ ከተረት፥ ከሙዚቃ፤ ከእውቀት ከሚገኘው ፍስሀ ተሳተፍ! ቢሰምርልህ ተቃቀፍ! እንደ ራስ አዳል እና እንደ አቤቶ ምኒልክ አብረህ ብላ! አብረህ አጭስ፥ እንደ ጌቶች ረዳና እንደ ብሬ ጁላ ፤ ከህይወት ጸጋዎች አብረህ ባትሳተፍ ከሞት እዳዎች አብረህ መሳተፍህ አይቀርም፤ ሻምበል ፍቅረስላስላሴ ወግደረስና ገለሳ ዲልቦ በህይወት ዘመናቸው የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት ያላቸው “ተጻራሪዎች “ ነበሩ፤ አሁን ስላሴ ቤተክርስትያን ጎን ለጎን ተኝተዋል ፤ እንደዚያ ነው!