>

ምኒልክ ተጉዞ የምትጠይቁኝ፣ ፊትም አላለፈ ኋላም አይገኝ...! (በለጠ ካሳ)

ምኒልክ ተጉዞ የምትጠይቁኝ፣

ፊትም አላለፈ ኋላም አይገኝ…!

በለጠ ካሳ


ጣሊያን ኮሶ ጭኖ ሸዋን ሲያጠጣው፣

ገና ሲበጠበጥ ዳኛው ቀናው፣

ባመጣው ወጨፎ በሰራው ርሳስ፣

ወቃው አመረተው ያን ባሕር ገብስ፣

ዳኛው ምኒልክ የኢትዮጵያ ንጉስ።

ቅዳሜ ተጉዞ እሁድ ተበራዬ፣

ሞስኮንም ገረመው ጣሊያንም ጉድአዬ።

ዳኛው የሰንበት ዕለት አበላ ታምር፣

ዕኛ ለሰው መስሎን ከጅሎን ነበር፣

ነጩን አሳረደው ላሞራው ግብር።

አዲስአበባ ላይ አየነ ታሪክ፣

ውሃ ሲሰግድለት ለአጤ ምኒልክ።

እንግዲህ ምኒልክ ምን ጥበብ ታመጣ፣

ውሃ በመዘውር ወደ ላይ ሲወጣ፣

ያደፈው ሲታጠብ የጠማው ሲጠጣ።

በመጨረሻም

እምዬ ምኒልክ በቅሎ ስጠኝ ብዬ እኔ አለምንህም፣

…ፈረስ ስጠኝ ብዬ እኔ አለምንህም፣

…ካባ ስጠኘ ብዬ እኔ አለምንህም፣

…ብር ስጠኘ ብዬ እኔ አለምንህም፣

አምና ነበር እንጂ ዘንድሮ የለህም።

ታህሣሥ 3/2015 ዓ.ም የታላቁ ንጉስ 109ኛ የመታሰቢያ ዕለት!

Filed in: Amharic