>
5:26 pm - Friday September 17, 1334

የአ.አበባ ተማሪዎች ፈቃደኝነታቸውን ባልገለጹበት ሁኔታ የክልል ባንዲራ እንዲሰቅሉና እና መዝሙር እንዲዘመር በማስገደድ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው...! ኢ.ሰ.መ.ጉ

የአ.አበባ ተማሪዎች ፈቃደኝነታቸውን ባልገለጹበት ሁኔታ የክልል ባንዲራ እንዲሰቅሉና እና መዝሙር እንዲዘመር በማስገደድ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው…!

ኢ.ሰ.መ.ጉ

*… በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሚነሱ ሁከቶች መንግስት በቂ ትኩረት በመስጠት ጉዳዩ ከቁጥጥር ውጭ ከመውጣቱ በፊት አስቸኳይ ዘላቂ መፍትሔ ይስጥ!

ታህሳስ 04/2015 ዓ.ም

መግቢያ፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ የተለያዩ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜ ከኦሮሚያ ክልል ባንዲራ እና

ከመዝሙር ጋር ተያይዞ ሁከቶች ተነስተዋል እነዚህንም አለመግባባቶች ተከትሎ የተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በትምህርት ቤቶች

ሰላም ማጣት፣ የአካል ጉዳትና ንብረት ውድመት እንዲሁም ሌሎችም ተፈጽመወል፡፡ ባሳለፍነው ዓመት 2014 ዓ.ም በለሚ ኩራ ፣ በየካ፣

በቂርቆስ እና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማዎች ውስጥ በሚገኙ የተወሰኑ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከኦሮሚያ ክልል ባንዲራ እና መዝሙር

ጋር ተያይዞ ሁከቶች ተነስተው እንደነበር እና ይህንንም ተከትሎ የሚመለከታቸው የክፍለ ከተማ ትምህርት ቢሮ ተወካዮች፣ ወላጆች እና የትምህርት

ቤቶች አመራሮች ባደረጉት ስብሰባ እና ውይይት ጉዳዩ በጊዜያዊነት ተፈትቶ ቆይቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ይህ ጉዳይ በቂ ትኩረት ባለማግኘቱና በዘላቂነት ባለመፈታቱ በ2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ

አለመግባባቶች ሊቀጥሉ ችለዋል፡፡ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በሚገኙት የሽመልስ ሀብቴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የአብዮት ቅርስ ሁለተኛ ደረጃ

ትምህርት ቤት እና የጠመንጃ ያዥ አንደኛ ደረጃና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከኦሮሚያ ክልል ባንዲራ እና መዝሙር ጋር ተያይዞ

አለመግባባቶች የተነሱ ሲሆን በዚህም ምክንያት የተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተፈጽመዋል፡፡ እነዚህ ትምህርት ቤቶች የተፈጠረውን አለመግባባት

ለመፍታት ከወላጆች ጋር በ13/02/2015 ዓ.ም ስብሰባዎችን ያደረጉ ሲሆን የቋንቋ ትምህርቱ ላይ አለመግባባት እንደሌለ ነገር ግን ዋነኛ አለመግባባቶችን

እየፈጠረ ያለው የሰንደቅ አላማ እና የመዝሙር ጉዳይ መሆኑን እንዲሁም ልጆች የማያውቁትን መዝሙር እንዲዘምሩ መገደድ የለባቸወም የሚሉ

ሃሳቦች በስብሰባዎቹ ላይ መነሳታቸውን ኢሰመጉ የክትትል ስራን ለመስራት በአካል በስብሰባዎቹ ላይ በመገኘት ለመረዳት ችሏል፡፡ ነገር ግን በቂርቆስ

ክፍለ ከተማ ስር በሚገኘው ጠመንጃ ያዥ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ሁከቱ በድጋሚ አገርሽቶ በ29/03/2015 ዓ.ም እና በ30/03/2015 ዓ.ም ዳግም መነሳቱን

እና በዚሁ ሁከት ምክንያት በርካታ ተማሪዎች ላይ ድብደባ መፈጸሙን፣ የትምህርት ቤቱ ንብረቶች መውደማቸውን፣ በአንድ የፖሊስ አባል ላይ ድብደባ

መፈጸሙን እና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ቁጥራቸው ለጊዜው ያልታወቁ ተማሪዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች መታሰራቸው ታውቋል ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው

መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ በእንጦጦ አምባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ22/03/2015 ዓ.ም በተመሳሳይ ሁኔታ ከሰንደቅ አላማ እና መዝሙሩ ጋር ተያይዞ

በትምህርት ቤቱ ሁከት ተነስቶ ንብረት መውደሙን፣ በተማሪዎች ላይ ድብደባ እና እስራት መፈጸሙን እና በእዚህ የተነሳ የመማር ማስተማሩ ሥራ

መስተጓጎሉን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃወች ለመረዳት ችሏል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ኢሰመጉ ለትምህርት ቤቱ በደብዳቤ ቁጥር EHRCO-

C/E/011/049/15 በቀን 26/03/2015 ዓ.ም መረጃ እንዲሰጠን ጠይቆ የነበር ሲሆን በጥያቄው መሰረት ትምህርት ቤቱ የተባለው ሁከት መፈጠሩን፣

ለሁከቱም መነሻ የነበረው የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ በትምህርት ቤቱ እንዲሰቀል እና መዝሙሩ እንዲዘመር በሚፈልጉ እና በማይፈልጉ ተማሪዎች

መካከል የተፈጠረ አለመግባባት መሆኑን፣ በእዚህም ምክንያት ንብረት ላይ ጉዳት እንደደረሰ፣ ትምህርት ቤቱ የሚያውቀው ሶስት ተማሪዎች እንደታሰሩ

እና በአንድ ተማሪ ላይ የአካል ጉዳት እንደደረሰ ለኢሰመጉ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በ03/04/2015 በእንጦጦ አምባ ትምህርት ቤት ዳግም ሁከት የተነሳ

ሲሆን በዚህም ምክንያት ተማሪዎች እና መምህራን ላይ ጉዳት መድረሱን እና በጊዜያዊነት ፖሊሶችን ወደ ጊቢው በማስገባት ችግሩን ለመቆጣጠር

መቻሉን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡ በተመሳሳይ በጉለሌ ክፍለ ከተማ በ23/03/2015 ዓ.ም አምሀ ደስታ ትምህርት ቤት፣

ድል በትግል እና አዲስ ተስፋ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራንና ተማሪዎች ከሰንደቅ አላማ እና መዝሙር ጋር ተያይዞ በተፈጠረ አለመግባባት

ግቢውን ለቀው መውጣታቸወን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ከፍተኛ 12 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ26/03/2015 ዓ.ም ከሰንደቅ አላማ እና መዝመር ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ሁከት

ተነስቶ የነበረ ሲሆን በአካባቢውም የተኩስ ድመጽ ነበር፡፡ ኢሰመጉ በእለቱ በቦታው በመገኘት ባሰባሰበው መረጃ መሰረት የአንድ ተማሪ ህይወት

ማለፉንና ከአስር በላይ ተማሪዎች እና አንድ አስተማሪ ተጎድተው ሆስፒታል መግባታቸውን ለመረዳት ችሏል፡፡ በዚሁ መነሻነት በትምህርት ቤቱ

የተከሰተውን ሁኔታ በተመለከተ ተምህርት ቤቱ መረጃ እንዲሰጥ በደብዳቤ ቁጥር EHRCO-C/E/012/04715 በቀን 27/03/2015 ዓ.ም

የጠየቀ ቢሆንም ይህ መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ከትምህርት ቤቱ ምንም አይነት ምላሽ አልተገኘም፡፡ በእዚሁ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኘው

በወንድራድ ትምህርት ቤት ውስጥ በ03/04/2015 ዓ.ም በተመሳሳይ ምክንያት ሁከት የተነሳ ሲሆን በእዚህም ምክንየት በተማሪዎች እና በንብረት ላይ

ጉዳት መድረሱን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡

በተጨማሪም ህዳር 28 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከሰንደቅ አላማ እና መዝሙር ጋር ተያይዞ ሁከት

መነሳቱን እና ይህንን ተከትሎ ከተማሪዎች ሲወረወሩ በነበሩ ድንጋዮች በትምህርት ቤቱ በርና መስኮቶች ላይ ጉዳት መድረሱን እና በዚህም ምክንያት

በርካታ ተማሪዎች መታሰራቸውን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡ በተመሳሳይ በ03/04/2015 ዓ.ም በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ

ውስጥ በሚገኙት አየር ጤና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ሚሊኒየም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስት ከእዚሁ ከኦሮሚያ ክልል ባንዲራ

እና መዝሙር ጋር ተያይዞ ሁከቶች መነሳታቸውን እና በእዚህም ምክንያት በተማሪዎች ላይ ድብደባ መፈጸሙን እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን

ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡

ኢሰመጉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከኦሮሚያ ክልል ባንዲራና መዝሙር ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ስለሚፈጠሩ

ሁከቶች እና እነሱንም ተከትሎ ስለደረሱ የተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን አስመልክቶ የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ስለጉዳዩ ዝርዝር

ማብራሪያ እንዲሰጥ በደብዳቤ ቁጥር EHRCO-C/E/014/048/15 በቀን 27/03/2015 ዓ.ም የጠየቀ ቢሆንም የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ

ይህ መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ምንም አይነት ምላሽ አልሰጠም፡፡ በተጨማሪም ኢሰመጉ ከላይ በተዘረዘሩት ጉዳዮች ላይ ከአዲስ አበባ ፖሊስ

በስልክ መረጃን ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራን ቢያደርግም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ተያያዥ የህግ ድንጋጌዎች፡

የሰብዓዊ መብቶች ዓለም አቀፍ መግለጫ አንቀጽ 26 እና የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባሕለዊ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን አንቀጽ 13 ሰዎች የመማር

መብት እንዳላቸው፣ ቢያንስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ነጻና አስገዳጅ እንደሆነ፣ የተግባረዕድነና የሙያ ትምህርተ በጠቅላላ እንዲዳረስ እንደሚደረግ እና

የከፍተኛ ትምህርት ደግሞ በችሎታ ላይ ተመስርቶ ለሁሉም እኩል ዕድል እንዲሰጥ መደረግ እንዳለበት እና ወላጆች ለልጆቻቻው የሚሰጠውን

የትምህርት ዓይነት ለመምረጥ የቅድሚያ መብት እንዳላቸው እንዲሁም ትምህርት መግባባትን፣ በሕዝቦች፣ በተለያዩ ዘሮችና በሀይማኖቶች መካከል

መቻቻልንና ወንድማማችነትን ማበረታታትና የተባበሩት መንግስታት ለሰላም ጥበቃ የሚያደርገውን ጥረት የሚያራምድ መሆን እንደሚገባው

ይደነግጋሉ፡፡

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 90 ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የትምህርት ዋስትና እንዲኖረው እንደሚደረግ እና ትምህርት በማናቸውም ረገድ

ከሀይማኖት፣ ከፖለቲካ አመለካከቶች እና ከባህላዊ ተጽእኖዎች ነጻ በሆነ መንገድ መካሔድ አንዳለበት ይይነግጋል፡፡

የኢሰመጉ ጥሪ፡

 መንግስት በአዲስ አበባ ከተማ አስስዳደር ስር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በተደጋጋሚ ከኦሮሚያ ክልል ባንዲራ እና መዝሙር ጋር

ተያይዞ ለሚነሱ አለመግባባቶችና ግጭቶች ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጥ፣

 በትምህርት ቤቶች የሚሰጥ ትምህርት እና የሚከናወኑ ስርአቶች በማናቸውም ረገድ ከሀይማኖት፣ ከፖለቲካ አመለካከቶች እና ከባህላዊ

ተጽእኖዎች ነጻ በሆነ መንገድ መከወን እንዳለባቸው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት እንዲሁም ሌሎች ህጎች በግልጽ አስቀምጠዋል በተጨማሪም

ብዝሃነት እና ህብረ ብሔራዊ አንድነት በሚንጸባረቅባት እና ወደፊትም ሊንጸባረቅባት በሚገባ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የከተማው ነዋሪ

በግልጽ ፈቃደኝነቱን ባልገለጸበት ሁኔታ የአንድን ክልል ባንዲራ እና መዝሙር እንዲዘመር በማስገደድ ምክንያት በተማሪዎች፣ በመምህራን፣

በወላጆች እንዲሁም በንብረት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ምንም አይነት የህግም ሆነ የአሰራር መሰረት ስለሌለው ሊቆም እና የአዲስ አበባ

ከተማ አስተዳደር እና የሚመለከታቸው የከተማ አስተዳደሩ ቢሮዎች ይህንን ከግምት ባስገባ መልኩ እንዲሁም ህግን እና የከተማውን ነዋሪ

ፈቃድ እና ፍላጎት ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ህጋዊ የሆነ ዘላቂ መፍትሔን እንዲያበጁ እና በእዚህ ውስጥ እጃቸው ያለበት አካላት

ከእዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ፣

 በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተነሱ ሁከቶችን ተከትሎ በተማሪዎች እና በመምህራን ላይ

የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲያስቆም፣

 በአዲስ አበባ ከተማ አስስዳደር ስር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተፈጠሩ ሁከቶችን ተከትሎ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ተይዘው

በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ በመሆኑ መንግስት ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ንብረት እንዲወድም ምክንያት የሆኑትን እና ንብረት

ያወደሙ ሰዎችን በመለየት በህግ ተጠያቂ እንዲያደርግ፣

 ይህን ጉዳይ ሰላማዊ መፍትሄ እንዳያገኝና ወደተባባሰ አለመግባባት እንዲያመራ በተለያዩ መግናኛ ዘዴዎች የሚደረጉ ግጭት ቀስቃሽ

ንግግሮችን ከማድረግ ሁሉም አካል እንዲቆጠብ፣

 ትምህርት ቤቶች የእውቀት ቤት እንደመሆናቸው በእዚያ አግባብ ብቻ ከማንኛውም ፖለቲካዊ፣ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ተጽእኖዎች ነጻ

በሆነ መንገድ ስራቸውን እንዲያከናውኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

አዲስ አበባ ፤ኢትዮጵያ

Filed in: Amharic