>

በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ክስ ላይ ፍርድ ለመስጠት፤ የመከላከያ ሚኒስቴር ቃለ ጉባኤ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጠ...! (ኢትዮ ኢንሳይደር )

በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ክስ ላይ ፍርድ ለመስጠት፤ የመከላከያ ሚኒስቴር ቃለ ጉባኤ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጠ…!

ኢትዮ  ኢንሳይደር 

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ የ“ፍትሕ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ በቀረበበት ክስ ላይ ፍርድ ለመስጠት ያስችለው ዘንድ፤ “ለመከላከያ ሰራዊት አባላት ሽልማት እና ማዕረግ የተሰጠበት ቃለ ጉባኤ እንዲቀርብለት” ትዕዛዝ አስተላለፈ። ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን ያስተላለፈው “ለትክክለኛ ፍርድ እንዲረዳው” መሆኑን ዛሬ ረቡዕ ታህሳስ 12፤ 2015 በዋለው ችሎት አስታውቋል።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው በጋዜጠኛው ጉዳይ ላይ የቀረበውን ክስ መርምሮ ፍርድ ለመስጠት ነበር። ሆኖም ፍርድ ቤቱ “ብይን ለመስጠት የሚያስፈልገው” ተጨማሪ ማስረጃ መኖሩን በመጥቀስ ፍርዱን ሳይሰጥ ቀርቷል።

ፍርድ ቤቱ የጠቀሰው ማስረጃ፤ ከአንድ ዓመት በፊት ለመከላከያ ሰራዊት አባላት ከተሰጠው ሽልማት እና የማዕረግ ዕድገትን በተመለከተ የተያዘን ቃለ ጉባኤ ነው። ችሎቱ ይኸው ቃለ ጉባኤ ከመከላከያ ሚኒስቴር እንዲመጣለት በዛሬው ውሎው አዝዟል።

ጋዜጠኛ ተመስገን እንዲከላከል በፍርድ ቤት በተወሰነበት ክስ ከቀረቡት ሁለት ፍሬ ነገሮች መካከል አንደኛው፤ የመከላከያ ሰራዊት ሽልማት እና የማዕረግ አሰጣጥን አስመልክቶ “ፍትሕ” መጽሔት ላይ የጻፈው ጽሁፍን የተመለከተ ነው። ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ በ“ፍትሕ” መጽሔት የወጣው ይህ የተመስገን ጽሁፍ፤ “መከላከያ ተቋማዊ ወይስ ኔትዎርክ” በሚል ርዕስ የታተመ ነው።

ተመስገን በዚህ ጽሁፉ ለመከላከያ ሰራዊት አባላት የተሰጠውን ሽልማት እና ማዕረግ አሰጣጥ “የብሔር የበላይነት የተጫነው ነው” ሲል ተችቷል።

* * ሙሉ ዘገባውን ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፦ https://ethiopiainsider.com/2022/9002/

Filed in: Amharic